የደብረዘይት ግብርና ምርምር ስምንት ዓመታትን በፈጀው ምርምሩ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ አዲስ የተሻሻለ የዶሮ ዝርያ ማግኘቱን አስታወቀ።
አዲስ የተገኘው ዶሮ ዝርያ ከዚህ በፊት ከነበሩ የተሻለ ዝርያ ሲሆን በስጋ መጠን እና በእንቁላል መጠን በኩል ያለው ለውጥ ከፍተኛ መሆኑንም የግብርና ምርምሩ ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል።
አዲስ የተገኘው የዶሮ ዝርያ ከዚህ በፊት ከነበሩ የዶሮ ዝርያዎች ከሚሰጡት የእንቁላል እና ስጋ መጠን በእጅጉ የተሻሻለ መሆኑን የደብረዘይት ግብርና ምርምር ማእከል ዶሮ ዝርያ ተመራማሪ ሚስማህ አለዊ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ምርምሩ የተገኘው ሦስት የተለያዩ ከውጭ የመጡ ዝርያዎችን በማዳቀል ሲሆን፣ ዝርያው ጥምር (ለእንቁላል እና ለስጋ) ጠቀሜታ ያለው መሆኑን ተመራማሪው ገልጸዋል። በምርምሩ የተዳቀሉ ዝርያዎች ከደቡብ አፍሪካ፣ ከአሜሪካ እና ከጀርመን የተውጣጡ እንደሆኑም ተጠቁሟል።
እንደ ተመራማሪው ገለጻ አዲሱ የዶሮ ዝርያ ጥምር ጠቀሜታ ያለው ከመሆኑ በላይ፣ ለአርሶ አደር ዶሮ እርባታ በእጅጉ ጠቃሚ መሆኑ ከዚህ በፊት ከነበሩት ዝርያዎች ልዩ ያደርገዋል ብለዋል። አዲሱ ዝርያ እንደ እንቁላል ዶሮዎች እና እንደ ስጋ ዶሮዎች ልዩ እንክብካቤና ዘመናዊ መኖ ሳያስፈልጋቸው ለአርሶ አደሩ የተሻለ የእንቁላል እና ስጋ ምርት ኹለቱንም በተሻለ መጠን እንደሚሰጡ ተመራማሪው ተናግረዋል።
አዲሱ የዶሮ ዝርያ አርሶ አደሩ ከዚህ በፊት ለእንቁላል እና ለስጋ ምርት ከሚጠቀምባቸው የሀበሻ ዶሮዎች በእንቁላል ምርታቸው በሦስት እጥፍ እንደሚሻል ተመራማሪው ተናግረዋል። ተመራማሪው እንደሚሉት አርሶ አደሩ የሚጠቀማቸው ጥምር ጥቅም (እንቁላል እና ስጋ) የሚሰጡ ዶሮች በዓመት የሚጥሉት አንቁላል ከ60 እንደማይበልጥ ሲሆን፣ አዲሱ ዝርያ በዓመት ከ150 እስከ 180 እንቁላል እንደሚያስገኝ ሚስማህ ጠቁመዋል።
በተጨማሪም አርሶ አደሩ ከዚህ ቀደም የሚጠቀማቸው የሀበሻ ሴት ዶሮዎች እንቁላል ለመጣል ከተፈለፈሉ ቢያንስ ስድስት ወር እንደሚቆዩ የተገለጸ ሲሆን፣ አዲሱ ዝርያ ከዚህ በፈጠነ ጊዜ እንቁላል እንደሚጥሉ ተመላክቷል። እንዲሁም አርሶ አደሩ የሚጠቀማቸው ወንድ ዶሮዎች ለስጋ ገበያ የሚደርሱት በሰባት ወር ሲሆን፣ አዲሱ ዝርያ ወንድ ዶሮዎች በአራት ወር ለገበያ እንደሚደርሱ ተመራማሪው ገልጸዋል። አዲስ ዝርያ አዲስ የተፈለፈሉ ዶሮዎች በኹለት ወር ውስጥ ከኹለት ኪሎ በላይ ስጋ እንደሚኖራቸውም ተረጋግጧል።
የዶሮ በሽታ በአርሶ አደሩ የዶሮ እርባታ ሥራ ላይ ከፍተኛ ችግር እንደሆነ የገለጹት ተመራማሪው፣ አሁን የተገኘው አዲስ ዝርያ በከፍተኛ ደረጃ በበሽታ ያለ መጠቃት እና በሽታን የመቋቋም አቅሙ የተሻለ በመሆኑ ከዚህ በፊት የነበረውን የዶሮ በሽታ ችግር እንደሚቀርፍ ተጠቅሷል።
የምርምር ሥራው ስምንት ዓመት የፈጀ ሲሆን፣ የዝርያውን ወጤታማነት እና የሚፈለገውን ቀጣይነት ተመሳሳይ ዝርያ ውጤታማነት ለመለካት ዝርያው ለዘጠኝ ትውልድ መሞከሩን እና የሚፈለገው ደረጃ ላይ መድረሱን ማረጋገጣቸውን ተመራማሪው አስታውሰዋል። የዘጠኝ ትውልድ ምዘናው አስተማማኝ በመሆኑ፣ በአሁኑ ጊዜ በደጋ፣ በወይና ደጋ እና ቆላማ ቦታዎች ላይ ለየአንዳንዳቸው ቦታዎች ለ15 አርሶ አደረሮች ተሰራጭቶ የቦታ ተስማሚነት እየተመዘነ ይገኛል ተብሏል።
በሦስቱም አየር ንብረት ቦታዎች ላይ የሙከራ ሥራው በዘጠኝ ቦታዎች፣ ማለትም በቆላ ሦስት፣ በደጋ ሦስት እና በወይና ደጋ ሦስት ቦታዎች ላይ እየተከናወነ የሚገኘው ቦታ ተስማሚነት በእጅጉ አመርቂ ውጤት እያመጣ መሆኑን ማረጋገጣቸውን ሚስማህ አመላክተዋል። የምርምር ግኝቱ ዋና ዓላማ አርሶ አደሩን ይበልጥ ተጠቃሚ ለማድረግ ያለመ እንደሆነ ተመራማሪው ሚስማህ ተናግረዋል። የአዲሱ የተሻሻለ ዝርያ የመጨረሻ ምዘና ተጠናቆ በ2014 በመላው አገሪቱ ለአርሶ አደሩ ተደራሽ እንዲሚሆንም ተመራማሪው ጠቁመዋል።
ቅጽ 2 ቁጥር 88 ሐምሌ 4 2012



