በሕውሓት የሚመራው የኢሕአዴግ ጦር ግንቦት 20 1983 ደርግን ከሥልጣን አስወግዶ ወደ ሥልጣን ከመጣ ጊዜ ጀምሮ አገራዊ ብሔርተኝነት እየደበዘዘ ሔዶ በንዑስ ብሔርተኝነት በሰፊው ተተክቷል፡፡ ከባለፉት ኹለት ዓመታት በፊት ኢትዮጵያዊ ነኝ ብሎ በኩራት መናገር ለአደጋ የሚያጋልጥ ነበር፡፡ ለውጡ እንደመጣ ጠ/ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ (ዶ/ር) እና አጠቃላይ ቲም ለማ የሚባለው ቡድን እጅግ ከፍተኛ ተቀባይነት እንዲያገኙ ያደረጋቸው ዋነኛው ምክንያት ይህ ታፍኖ የቆየውን አገራዊ ማንነት በግልጽ ማቆለጳጰሳቸው ነበር፡፡
አዲሱ ቡድን ሥልጣን ላይ ወጥቶ ፈጣን ለውጦችን በማሳየት ዜጎችን በሀሴት ማዕበል ሲያንሳፍፋቸው ንዑስ ብሔርተኝነት ተቀዛቅዞ አገራዊ ብሔርተኝነት የበላይ ሊሆን ይመስል ነበር፡፡ ከስድስት ወር በኋላ ግን ብሔርተኝነት በቀላሉ እንደማይበገር እና እንደመውም ተጠናክሮ በመምጣት የበላይነቱን እንደሚያስጠብቅ የሚገልፁ ክስተቶች መፈጠር ጀመሩ፡፡
ንዑስ ብሔርተኝነት ማንሰራራቱን ያወጀው ደግሞ እጅግ ዘግናኝ ጎኑ የሆነውን ጽንፈኝነትን በማሳየት ነበር፡፡ በአዲስ አበባ ለጠ/ሚኒስትሩ ድጋፍ የወጣው ሕዝብን የጎዳው የቦንብ ጥቃት የሚታወስ ሲሆን በተለያዩ ክልሎች ደግሞ ብሔር ተኮር ጥቃቶች እና ማፈናቀሎች መከሰታቸው የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡ ባለፉት ኹለት ዓመታት ውስጥ በርካታ እጅግ ዘግናኝ የሆኑ ከብሔር ማንነት ጋር የተያያዙ ጥቃቶች በአገሪቱ አራቱም አቅጣጫዎች ተከናውነዋል፡፡
ታዋቂው የኦሮሚኛ ዘፋኝ ሐጫሉ ሁንዴሳ ሰኔ 22 2012 መገደሉን ተከትሎ በዋናነት በኦሮሚያ ክልል እና በመጠኑም ቢሆን በአማራ ክልል የታየው የሰዎች ሞት እና ሰፊ የሆነ የንብረት ውድመት ከንዑስ ብሔርተኝነት ጋር የተገናኘ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ የዘፋኙን መሞት ተከትሎ በተወሰኑ የመገናኛ ብዙኋን ሲሰራጩ የነበሩት አንድን ብሔር በሌላው ላይ የሚያነሳሱ መልዕክቶች የእኔ የሚሉት ብሔር በጠላትነት የፈረጁት ብሔር(ዎች) ላይ ጥቃት አንዲፈፅም የሚያደፋፍሩ ነበሩ፡፡
የዘፋኙን ግድያ ተከትሎ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ 166 ሰዎች እንደሞቱ እና 239 ሰዎች እንደቆሰሉ ፌዴራል ፖሊስ በቅርቡ ለመገናኛ ብዙኋን መግለጹ ይታወቃል፡፡ በዚህ ዘግናኝ ጭፍጨፋ ዋነኛ ተሳታፊ የነበሩትም ጽንፈኞች እንደሆኑ መንግሥት ለሕዝብ ይፋ አድርጓል፡፡ ይህም በንዑስ ብሔርተኝነት ዙሪያ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ለሌሎች ብሔሮች ያላቸውን ጥላቻ በስሜት ደረጃ ከማንፀባረቅ ዘለው ጭፍንነታቸውን በተግባር እየኖሩት እንደሆነ የሚያረጋግጥ ነው፡፡
ተወልደው ባደጉበትም ሆነ ለዓመታት በኖሩበት አካባቢ በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደሉት እና የቆሰሉት ኢትዮጵያዊያን ወገኖቻችን የደረሰባቸውን ግፍ አደባብሶ ለማለፍ መሞከር ጥቃቱን የፈፀመው አካል ነገም ተነስቶ ተመሳሳይ እብሪት እንዲከውን ፈቃድ መስጠት ነው፡፡ ዜጎች ቤታቸው ተዘግቶባቸው እንዲቃጠሉ መደረጉ እንዲሁም በቀን ከቤታቸው ወጥተው በዘግናኝ ሁኔታ ሲገደሉ ይህ ነው የሚባል የማስቆም እርምጃ በአካባቢ አስተዳደሮች ያለመወሰዱ የአክራሪ ብሔርተኝነቱ ስሜት በመንግሥት መዋቅርም ውስጥ ሊኖር እንደሚችል የሚጠቁም ነው፡፡
ንዑስ ብሔርተኝነት የአንድ ብሔርን ጥቅም ለማስጠበቅ በሚል የዛን ብሔር አባላት የተበዳይነት ስሜት በመፍጠር አንዳንድ ብሔሮችን እንደበዳይ እንዲያዩ እና ልዩነታቸውን አጽንኦት ሰጥተው እንዲንቀሳቀሱ የሚያደርግ አስተሳሰብ ነው፡፡ በመሆኑም እንደ ኢትዮጵያ ያሉ በርከት ያሉ ብሔሮች ያለባቸው አገሮች ላይ ንዑስ ብሔርተኝነት ሲገን ሁሉም ብሔር የራሱን ጥቅም ለማስከበር አጋር ከሚላቸው ብሔሮች ጋር እንዲተባበር እና ጠላት የሆኑትን በጥርጣሬ እንዲያይ፣ ዘለል ሲልም እንዲያጠቃ ምቹ ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ ከማንነት ጋር ባለው ጥብቅ ቁርኝትም የተነሳ ሰዎችን በቀላሉ ማነሳሳት፣ ስሜት ውስጥ መክተት እና ተበድለናል በሚሉት ጉዳይ ሰበብ ለጥቃት እንዲነሳሱ ማድረግ ቀላል ነው፡፡ ይህም በብዙ ብሔሮች በሚከወንበት ጊዜ ለአገር ህልውና እጅጉን ፈታኝ ጉዳይ ይሆናል፡፡
በመሆኑም ብሔርን እንደሚያመለክቱ የሚታወቁ ቃላትን በመጠቀም ስለሌላ ብሔር ጥላቻ የሚሰብኩ የገዢው ፓርቲም ሆነ የተቃዋሚ ፖለቲከኞች ያለጠያቂ የሚንቀሳቀሱበት ጊዜ እንዲያበቃ አዲስ ማለዳ ጥሪ ታቀርባለች፡፡
በውዱ የሰው ልጅ ሕይወት ላይ ከደረሰው መጠነ ሰፊ ሕልፈት በተጨማሪ ባለፈው ሳምንት በኦሮሚያ የነበረው ጥቃት በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰ ነው፡፡ አዲስ ዘመን እንደዘገበው በባቱ (ዝዋይ) ከተማ ብቻ 100 የመኖሪያ ቤቶች፣ 24 ሆቴሎችና በርካታ የንግድ ቤቶች ሲቃጠሉና ሲፈርሱ፤ 34 የጉዳት ሰለባ ሆነዋል፡፡ የባቱ ከተማ ከንቲባ አቶ አለሙ ደዋና በተለይ በከተማዋ ሆቴሎች እና ንግድ ተቋማት ላይ የተፈፀመው ውድመት የከተማዋን እድገት ለ20 እና 30 ዓመታት ወደ ኋላ የሚጎትት መሆኑን ለአዲስ ዘመን ገልፀው ከኦሮሞ ባህል ያፈነገጠና ሊወገዝ የሚገባው መሆኑን አክለዋል፡፡
በከፍተኛ ደረጃ የንብረት ጉዳት ከደረሰባቸው ከተሞች መካከል የምትጠቀሰው ሻሸመኔም 200 የንግድ ቤቶች እንደወደሙባት እና 56 የመኖሪያ ቤቶች እንደተቃጠሉ ኢሳት ዘግቧል፡፡ በከተማዋ 28 ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች እንደወደሙ ሪፖርቱ ይገልጻል፡፡ በሻሸመኔ በጥቃቱ ከወደሙ ንብረቶች መካከል ትምህርት ቤቶች ይገኙበታል፡፡
በድህነቷ ከዓለም አገራት ግርጌ በምትገኝ አገር ውስጥ ትምህርት ቤት ለመሥራት ግለሰቦች፣ የእርዳታ ድርጅቶች እና መንግሥት ደፋ ቀና ማለታቸው የሚጠበቅ ነው፡፡ ከዚህ ሁሉ ጥረት በኋላም የትምህርት ቤቶች ብዛት ከትምህርት ፍላጎት ጋር ባልተጣጣመ መንገድ ዝቅተኛ ነው፡፡ በአንድ ክፍል የሚማሩ ተማሪዎች ቁጥር አሁንም ከሚፈለገው በላይ መሆኑ የትምህርት ጥራት ላይ እና የወደፊት አገር ተረካቢ ሕጻናት ሕይወት ላይ የሚኖረው ጫና አሉታዊ ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ የሁሉም ብሔሮች ልጆች የሚማሩበትን ትምህርት ቤት ማውደም የራስንም መጻኢ እድል ማጨለም እንደመሆነ ግልጽ ነው፡፡ ነገር ግን የንዑስ ብሔርተኝነት አክራሪ ለሆኑ ሰዎች እንዲህ ዓይነቱ አመለካከት ቦታ የለውም፡፡
በስምጥ ሸለቆ ውስጥ የሚገኙ የኦሮሚያ ከተሞች ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየደመቁ እና የንግድ ማዕከልነታቸው እየሰፋ ሔዷል፡፡ ለዚህም በከተሞቹ የነበረው ኢንቬስትመንት መጨመር በዋነኛ ምክንያትነት የሚጠቀስ ነው፡፡ የከተሞቹ ነዋሪዎችም ሆኑ ከሌሎች ቦታዎች ወደ ከተሞቹ የመጡ ሰዎች ልማቱን እውን ለማድረግ የበኩላቸውን አድርገዋል፡፡
ከላይ እንደተጠቀሱት ሻሸመኔ እና ባቱ ያሉ ከተሞች በደረሰው የንብረት ውድመት ምክንያት እድገታቸው እጅጉን መጓተቱ እሙን ነው፡፡ በዚህም ዋነኛ ተጎጂ የከተሞቹ ነዋሪ ነው፡፡ በውድመቱ የተነሳ ሥራቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥር ትንሽ የሚባል አይደለም፡፡ የንግድ ተቋማቱ በመውደማቸው የተነሳም በከተማዋ የሚንቀሳቀሰው ገንዘብ እጅጉን ይቀንሳል፡፡ ይህም ነዋሪዎች በተለያየ መንገድ ሊያገኙ የሚችሉትን ገቢ የሚያስቀር ነው፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ውድመቱ በከተሞቹም ሆነ በኦሮሚያ ክልል ለወደፊት ሊደረጉ ይችሉ የነበሩ ኢንቬስትመንቶችን ጥያቄ ውስጥ የሚከት ነው፡፡ ሰላም እና ደህንነት ለኢንቬስትመንት ቅድመ ሁኔታ ተደርገው ከሚወሰዱ ነገሮች መካከል በመሆናቸው እንዲህ ዓይነቱ ውድመት በአጠቃላይ ኢንቬስትመንት ላይ የሚያጠላ ነው፡፡
ውድመቱ ከተሞቹ ከቱሪዝም የሚያገኙትን ገቢም የሚፈታተን ነው፡፡ በተለይ የሆቴሎች እና ሌሎች የመስተንግዶ አገልግሎት መስጫ ተቋማት መውደም አካባቢዎቹ ከውድመቱ ጋር ተያይዞ ከሚሰጣቸው ጥሩ ያልሆነ ስም ጋር ተዳምሮ ቱሪዝሙን ሊያዳክመው ይችላል፡፡
ይህ ሁሉ የሕይወት መጥፋት እና የንብረት መውደም የተከሰተው ንዑስ ብሔርተኝነትን በማክረር መሆኑ ሲታሰብ እና የጥፋቱ መጠን እየጨመረ መምጣቱ ግምት ውስጥ ሲገባ አክራሪነት ላይ ልጓም ማጥበቅ እንደሚያስፈልግ መገንዘብ ይቻላል፡፡ አዲስ ማለዳም መንግሥት ንዑስ ብሔርተኝነትን የሚያከሩ ኃይሎች እንደፈለጋቸው የማይፈነጩበት ሁኔታ እንዳይፈጠር ጠንክሮ እንዲሰራ ጥሪ ታቀርባለች፡፡
ቅጽ 2 ቁጥር 88 ሐምሌ 4 2012


