ኢንተርኔት በመቋረጡ የግል የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ችግር ውስጥ ገብተዋል

0
564

በኢትዮጵያ የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ በተፈጠሩ ኹከቶች ምክንያት የኢንተርኔት አገልግሎት በመቋረጡ የንግድ (የግል) ቴሌቪዥን ጣቢያዎች አዳዲስ እና ወቅታዊ ፕሮግራሞችን ለተመልካቾቻቸው ማስተላለፍ ባለመቻላቸው ችግር ውስጥ እንደገቡ የብሮድካስተሮች ማኅበር አስታወቀ።

በኢትዮጵያ የሚሰራጩ አብዛኛዎቹ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ፕሮግራሞቻቸውን የሚያስተላልፉት ከአገር ውጭ በሚገኙ ሳተላይቶች አማካኝነት በመሆኑ ፕሮግራሞቹን ለመላክ ኢንተርኔት የሚያስፈልግ ሲሆን፣ አሁን ላይ ጣቢያዎቹ የኢንተርኔት አገልግሎት ማግኘት ባለመቻላቸው ኢንተርኔት ከተቋረጠ ጊዜ ጀምሮ አዲስ ፕሮግራሞችን መላክ ሳይችሉ ቀርተዋል። ይህንንም ተከትሎ ቀድመው የተሠሩ ፕሮግራሞችን እና ወደ ሕዝብ የደረሱ መረጃዎችን ደግመው እያስተላለፉ መሆኑን የኢትዮጵያ ብሮድካስተሮች ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ እንዳሻው ወልደሚካኤል ለአዲስ ማለደ ተናግረዋል።

የተፈጠረውን ችግር ተከትሎም አንዳንድ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች አዳዲስ ፕሮግራሞችን ሠርተው ወደ ሳተላይት ለመላክ በ‹‹ሀርድ ዲስክ›› ይዘው ወደ ሌሎች ጎረቤት አገራት እያቀኑ መሆኑም ተጠቁሟል። ነገር ግን ፕሮግራሞችን ሠርቶ ወደ ውጭ አገራት ልኮ ወይም ሄዶ ለመላክ አቅሙ የሌላቸው ጣቢያዎች አዲስ ወቅታዊ ጉዳዮችን እና ፕሮግራሞችን ማስተላለፍ አለመቻላቸውን እንዳሻው ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

ፕሮግራሞችን በ‹‹ሀርድ ዲስክ›› ለሰዎች ለመላክ ወይም ወደ ሌሎች አገራት ሄዶ ወደ ሳተላይት ለመላክ የመረጃውን ደኅንነት ለማረጋገጥ እና መረጃው ሙሉ ለመድረሱ አስተማማኝ ነገር ስለሌለ፣ ወደ ውጭ አገራት የተሠሩ ፕሮግራሞችን መላኩ አስተማማኝ አለመሆኑን የማኅበሩ ዋና ሥራ አስኪያጅ ተናግረዋል። ወደ ሕዝብ የሚደርሱ መረጃዎች ጥብቅ እና ኃላፊነት ሊወስድ በሚችሉ ሰዎች እጅ ብቻ መግባት ቢኖርባቸውም፣ ጥንቃቄ በጎደለው መንገድ እና ለተለያዩ ጉዳዮች ተጋላጭ በሆነ መንገድ ከአገር ወጥተው ወደ ሳተላይት እንደሚላኩም ታውቋል።

ዋና ሥራ አስኪያጁ አክለውም ሁኔታው የመረጃ ሽግግሩን ወደ ባህላዊ የግንኙነት መንገድ የከተተ አስራር መሆኑን ገልጸው፣ በሚላኩት መረጃዎች ላይ ያልተጠበቀ ችግር ሊፈጥር የሚችል መሆኑን ጠቁመዋል።

ችግሩን ለመፍታት እና የችግሩ አሳሳቢነት ታይቶ አስቸኳይ መፍትሔ ለማፈላለግ የኢትዮጵያ ብሮድካስተሮች ማኅበር ለኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን፣ ለኢትዮ ቴሌኮም፣ ለሰላም ሚኒስቴር፣ ለጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት እንዲሁም ለሚመለከታቸው ሁሉ ችግሩን አሳሳቢነት በደብዳቤ ገልጾ በልዩ ሁኔታ ምላሽ እንዲሰጠው መጠየቁን የማኅበሩ ዋና ሥራ አስኪያጅ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ሆኖም ማኅበሩ ከላይ ለተጠቀሱት ተቋማት ያስተላለፈው ጥያቄ እስከ አሁን ምላሽ አለማግኘቱን የማኅበሩ ዋና ሥራ አስኪያጅ አመላክተዋል። የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጡ እስከ መቼ እንደሚቆይ አለመታወቁ ደግሞ የቴሌቪዥን ጣቢያዎቹ ሠራተኞቻቸውን በቤታቸው እንዲቆዩ ለማድረግ አለማስቻሉን እና ጣቢያዎቹ ሠራተኞቻቸውን የሥራ አቅጣጫ እንዳይሰጡ አድርጓል ተብሏል።

አሁን ያለው አገራዊ ችግር እንደተጠበቀ ሆኖ፣ መንግሥት ከዚህ በፊት ሥራቸውን በኃላፊነት የሚሠሩ እና በሠሩት ሥራ ላይ ሕጋዊ ተጠያቂነት የሚወስዱ ጣቢዎችን በልዩ ሁኔታ አይቶ የኢንተርኔት አገልግሎታቸውን ማስቀጠል እንደሚገባ እንዳሻው ጠቁመዋል። ጣቢያዎቹ ሥርጭታቸው ላይ ቀድመው የተላለፉ ፕሮግራሞችን ደግመው ማስተላለፋቸው እና አዲስ ወቅታዊ መረጃዎችን እንዲሁም ፕሮግራሞችን ለአድማጮቻቸው ማሰራጨት አለመቻላቸው ኅብረተሰቡ አዲስ መረጃ እንዳያገኝ እና በሚደገሙ ፕሮግራሞች እንዲሰላች ሊያደርጉት እንደሚችሉ ተመላክቷል።
ጣቢያዎቹ በኮቪድ-19 መከሰት በደረሰባቸው ከባድ የገንዘብ እጥረት ጫና በተጨማሪ በኢንተርኔት መጥፋት የፕሮግራም መቋረጥ በማጋጠሙ በጫና ላይ ጫና እንደፈጠረባቸው እንዳሻው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ብሮድካስተሮች ማኅበር የማኅበሩ አባላት ሚዲያዎች በኮቪድ 19 ኮሮና ቫይረስ መከሰት ምክንያት ከመጋቢት 4/2012 እስከ ሚያዚያ 19/2012 ድረስ ባለው ጊዜ ብቻ ያገኙት የነበረውን 156 ሚሊዮን ብር የአየር ሰዓት ሽያጭ ገቢ ማጣታቸውን የኢትዮጵያ ብሮድካስተሮች ማስታወቁን አዲስ ማለዳ መዘገቧ ይታወሳል።

ቅጽ 2 ቁጥር 88 ሐምሌ 4 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here