ሴት እና አገር

0
507

በኢትዮጵያ ለእናት የተለየ ፍቅር አለ። በየአገሩም እያንዳንዱ ማኅበረሰብ በተለየ የሚያከብረውና ቅድሚያ የሚሰጠው አገልግሎት እንዳለው ሁሉ ነው፣ በኢትዮጵያም እናትነት ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው የሆነው። በተጓዳኝ በአንዳንድ አገራት ለአባትነት፣ በአንዳንዶቹ ለእህትነት ወይም ለወንድምነት ትልቅ ስፍራ ይሰጣል።

ይህ የሚታወቀው እንዴት ነው? የተለያዩ ማሳያዎች ይኖራሉ። አንደኛውና እዚህ ላይ ማንሳት የወደድኩት ከአገር ጋር የሚገናኘውን ነው። አገራችንን የምንጠራት በሴት አንቀጽ ነው። በኢትዮጵያውያን አንደበት አገር እናት ትባላለች። አገርን እምዬ ይሏታል፣ አገልግሎቷን፣ አቃፊነትና ሆደ ሰፊነቷን፣ ዥንጉርጉር መውለዷን ወዘተ በእናት ይመስላሉ።
እናትና አገር በዚህ ሲገናኙ፣ በሰውነት እናትነትን የተቀናጁ ሴቶችም አገርን በሰፊው ያገለግላሉ። ፖለቲካውንና መደገፍ መቃወሙን ወዲያ ብለን፣ አሁን በሥልጣን ላይ ያሉትን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን እንመልከት። በእኚህ 40ዎቹን ባላጋመሱ የአገር መሪ ውስጥ የእናታቸው ሚና ቀላል የሚባል እንዳልሆነ ከንግግራቸው መረዳት ቀላል ነው። የጠቅላይ ሚኒስትሩ እናት ለአገር ትልቅ ሰው አበርክተዋል።

ውብ የሆነ የሕንጻ ግንባታ ሥራ በንድፍ ሠሪው ሐሳብ ተጀምሮ በወረቀት ይነደፋል። ሠሪው ደምና ስጋውን እንዲሰጥ፣ ወርዶ እንዲቆፍር፣ ሲሚንቶ እንዲያቦካና እንዲለስን አይጠበቅበትም። ሥራው በወረቀት ያልቃል። ያም ንድፍ ጊዜው ሲደርስ ከሲሚንቶና ከብሎኬት ቅርጽ ይይዛል። የእናቶችም ሥራ እንዲያ ነው፣ መሪነት ወንበር ላይ አይቀመጡም፣ የሥልጣን መጠሪያን አያገኙም፣ በዛም እውቅና አይሰጣቸውም፣ ንድፉን ግን በልጆቻቸው ውስጥ ይሠራሉ። ያም ቆይቶ የብዙዎች መጠለያ ቤት ይሠራበታል።
ታድያ እኩይ ምግባር ላይ የሚገኝ ሰው ምነው በእናቶች መላ ውስጥ እርማት ያላገኘ የተባለ እንደሆነ፣ እዚህ ላይ በማኅበረሰብ ውስጥ የቤተሰብን ድርሻ እንረዳለን። ትዳር በጭቅጭቅ ውስጥ ሲሆን፣ ሲፈርስና ሁኔታዎች የልጆችን መንፈስ ሲረብሹ፣ በቤት ውስጥ የእናት ድምጽ ሰሚ ሲያጣ ወዘተ በመካከል ልጅ አልባሌ ቦታ ይገኛል። ይህም ለእኩይ ሥራዎች የተመቸ ያደርገዋል።
ዛሬ ላይ በተለይ በአገራችን የሚታዩ የጥፋት ተግባራትና ጥፋቱን የሚፈጽሙ ወጣቶችን ስንመለከት ‹ኢትዮጵያዊ› መሆናቸው የሚያጠራጥረን ለዚህ ነው። የእናትን ቁጣ እና ተግሳጽ የማይሰማ ሰው እንኳ ቢሆን ቢያንስ ‹በእናትህ!› ሲባል መለስ እንደሚል የምናምን ጥቂት አይደለንም።

ሴቶች ወይም እናቶች ከፖለቲካው ወይም ከብሔር ንትርክና ክርክር ገለልተኛና የማይመለከታቸው ስለሆኑ አይደለም። እንደዛ አይደሉም። በኢትዮጵያ ታሪክ ብዙ እናቶች ልጆቻቸው በከንቱ ደማቸው ሲፈስ ያዩ፣ ልባቸው የተሰበረና ያዘነ ናቸውና፣ ገለልተኛ ተመልካችና የእርቅ ሽማግሌዎች ሊሆኑም አይችሉም። ግን ልጅን የማጣትን ነገር፣ የሰውነትን ክብደትና ዋጋ፣ ትልቅነትና ምን ዓይነት ጸጋ እንደሆነም በሚገባ ያውቃሉ።

ስለዚህም የእናቶችን ድርሻ በቤተሰብ ውስጥ በተገቢው መንገድ መቃኘት፣ ከሥነ ልቦና አንጻርም ልጆች ላይ ሊፈጥር የሚችለውን ልዩነት በትኩረት ማየት አስፈላጊ ይመስለኛል። በቤት ውስጥ ተደማጭነታቸው ካደገ፣ ልጅ እንደ አባቱ ቁጣ ሁሉ የእናቱንም ምክር ይሰማል። እናት በልጇ ውስጥ የምታየው ትልቅነት ለልጅም ሊታየው ከቻለ፣ ብዙ የተሻሉ ሰዎችን ማፍራት ይቻላል።
ይህን ሁሉ ስል የአባቶችን ድርሻ ማቅለሌ ወይም መዘንጋቴ እንዳይደለ ልብ በሉልኝ። በቤተሰብ ውስጥ የእናትና የአባት ድርሻ አንዱ በሌላው የሚተካም አይደለም። የእናቶችን ብልሃት መገመት ግን አይከብድም። እናም የእናትነት ድርሻን፣ የራስን ፍላጎት ገትቶ የቤት እመቤት ሆኖ ልጆችና ቤተሰብን ማገልገልን እንዳንንቀው። ለአገር የሚጠቅሙ ሰዎች ከእናቶች ማህጸን የሚወለዱ ሁሉ አይደሉም፣ ለአገርም፣ ለራሳቸውም እንዲጠቅሙ ተደርገው የተሠሩም ጭምር እንጂ።
ሊድያ ተስፋዬ

ቅጽ 2 ቁጥር 89 ሐምሌ 11 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here