የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ በ2012 በጀት ዓመት 381 ሚሊዮን ብር ገቢ ሰበሰበ

0
1063

• የኦሮምያ ክልል የተሽከርካሪ እንቅስቃሴን ማገዱ በገቢው ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል

የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ በ2012 በጀት ዓመት ከ381 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰብ መቻሉን አስታወቀ።
ኢንተርፕራይዙ ገቢውን የሰበሰበው ከአዲስ አበባ አዳማ እና ከድሬድዋ ደዋሌ የፍጥነት መንገድ የአገልግሎት ክፍያ እና ከማስታወቂያና ሌሎች አገልግሎቶች መሆኑ ተገልጿል። በበጀት ዓመቱ ከአዲስ አዳማ እና ከድሬድዋ ደዋሌ የክፍያ መንገዶች በድምሩ ከ8 ሚሊዮን በላይ የትራፊክ ፍሰት በማስተናገድ ከክፍያ መንገድ አገልግሎት ከ350 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰብ ችሏል።
በተጨማሪም ከልዩ ልዩ ገቢዎች፣ ከማስታወቂያ ቦታዎች ኪራይ፣ ከተሽከርካሪ ማንሻና መጎተቻ መሰል አገልግሎቶች 31 ሚሊዮን ብር በመሰብሰብ በጥቅሉ 381 ሚሊዮን ብር መሰብሰብ መቻሉን የኢንተርፕራይዙ ሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ ሮቤል አያሌው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ኢንተርፕራይዙ በበጀት ዓመቱ ማጠቃለያ ያገኘው ዓመታዊ ገቢ ከባለፈው በጀት ዓመት አጠቃላይ ዓመታዊ ገቢ ጋር ሲነፃፀር የ106 ሚሊዮን ብር ብልጫ ማሳየቱን ሮቤል አክለው ገልጸዋል። ኢንተርፕራይዙ በ2011 በጀት ዓመት አጠቃላይ የሰበሰበው ገቢ 275 ሚሊዮን ብር መሆኑን ሮቤል አስታውሰዋል። ኢንተርፕራይዙ ያስመዘገበው ገቢ በኮቪድ-19 የታወጀውን የእንቅስቀሴ ገደብ ተቋቁሞ መሆኑም ተመላክቷል።

እንደ ሕዝብ ግንኙነት ባለሙያው ገለጻ ኢንርፕራይዙ በ2012 ገቢውን ማሳደግ የቻለው የአገልግሎት አሰጣጡን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሳደገ በመምጣቱ እና ለኅብረተሰቡ ግንዛቤ በመፍጠር የፍጥነት መንገዶችን በመጠቀሙ የጊዜ፣ የነዳጅና የጥገና ወጭ ማስቀረት እንደሚችል በማመኑ የክፍያ መንገዶች ተጠቃሚ ከጊዜ ወደ ጊዜ በመጨመሩ ነው ብለዋል። እንዲሁም ኢንተርፕራይዙ የድሬድዋ ደዋሌ የፍጥነት መንገድን በበጀት ዓመቱ ወደ ሥራ በማስገባቱ መሆኑም ተጠቁሟል።

በአንጻሩ ኢንተርፕራይዙ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የመጨረሻዎቹ ሦስት ወራት ኮቪድ-19 በመከሰቱ ማግኘት የሚችለውን ገቢ እንዳያገኝ ተጽዕኖ መፍጠሩን ሮቤል ጠቁመዋል። በኮቪድ-19 መከሰት የኅብረተሰቡ እንቅስቃሴ መገደቡ እና የኦሮምያ ክልላዊ መንግሥት የተሽከርካሪ እንቅስቃሴን ማገዱ፣ በኢተርፕራይዙ ገቢ ላይ ተጽዕኖ ያሳደሩ ኹነቶች መሆናቸውን ሮቤል አስታውሰዋል።
ኢንተርፕራይዙ በ2012 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት ውስጥ 192 ሚሊዮን ብር በመሰብሰብ እቅዱን 93 በመቶ ማሳካት ችሎ የነበረ መሆኑና በበጀት ዓመቱ ማጠቃለያ ስድስት ወራት ውስጥ ያስመዘገበው የእቅድ አፈጻጸም ወደ 89 በመቶ መቀነስ፣ ኮቪድ-19 በሚገኘው ገቢ ላይ ተጽዕኖ እንዳሳደረበት ማሳያ ሆኗል።

ኢንተርፕራይዙ ገቢ ከመሰብሰብ ባሻገር በሚያስተዳድራቸው የክፍያ መንገዶች ላይ የሚከሰቱ የትራፊክ አደጋና ሞትን ከመቀነስ አንፃር ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ በመሥራቱ፣ ከባለፈው ዓመት ከደረሰው የትራፊክ አደጋ 50 በመቶ መቀነስ መቻሉን ሮቤል አመልክተዋል። በዚህም በ2011 ዓመት 12 ወራት ውስጥ በአዲስ አዳማ የፍጥነት መንገድ ተከስቶ የነበረውን የ25 ሰዎች ሕይወት መጥፋት፣ በ2012 አጠቃላይ በጀት ዓመት 11 የሞት አደጋ በማስተናገድ በግማሽ መቀነስ መቻሉ ተጠቅሷል።

በተጨማሪም ኢንተርፕራይዙ የጥገና አቅሙን በማሳደግ በኹለቱም አቅጣጫ ከ10 ኪ.ሜ በላይ የመንገድ መስመሮችን ቀለም በመቀባት እንዲሁም በአገልግሎት እድሜ ማብቃት እና በአደጋ ምክንያት በመንገድ ንብረቶች ላይ የሚደርሱ ጉዳቶችን በመጠገን የመንገዱን ምቾት እና ደኅንነት እንዳይጓደል መሥራቱ ተጠቅሷል።

የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ዐስር ስትራቴጂካዊ ግቦች እንዲሁም ዘጠኝ የማስፈጸሚያ ፕሮጀክቶችን ነድፎ ሲተገብር የቆየ ሲሆን፣ ዕቅዱንም በየደረጃው መግባባት ላይ በመድረስ፤ እስከ ፈጻሚ ድረስ በማውረድ መተግበር መቻሉን ሮቤል ጠቁመዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 89 ሐምሌ 11 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here