ሔሎ ታክሲ የትራንስፖርት እና የቱሪዝም ዘርፍን ለማሳደግ እና ለማዘመን ይረዳ ዘንድ ከተለያዩ አገራት ወደ አገራችን የሚገቡ ቱሪስቶች ከቦታ ቦታ የሚያመላልሱ አውሮፕላኖችን አስገብቶ በአይነቱ የመጀመሪያ የሆነውን የጎብኚዎች የአውሮፕላን ትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት እየሠራ እንደሚገኝ አስታወቀ።
ሔሎ ታክሲ ከውጪ ኢንቬስተሮች ጋር በጋራ በመሆን የኢትዮጵያን የትራንስፖርት እና የቱሪዝም ዘርፍ ለማሳደግ በመሥራት ላይ እንደሚገኝ አስታውቆ፣ ከተለያዩ አገራት ወደ አገራችን የሚገቡ ጎብኚዎች ከቦታ ቦታ የሚመላለሱበት ዘመናዊ አውሮፕላኖችን በማስገባት በአይነቱ የመጀመሪያ የሆነውን የቱሪስቶች የሔሊኮፕተር ትራንስፖርት አገልግሎት በቅርቡ ለመጀመር ከ50% በላይ ሥራዎቹን ማጠናቀቁንም ገልጿል።
ጎብኚዎችን በሔሊኮፕተር የማመላለስ ሥራም በቅርብ ጊዜ ውስጥ እንደሚጀመር የሄሎ ታክሲ ባለቤትና ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዳንኤል ዮሐንስ አስታውቀዋል።
ይህም ባሳለፍነው ሐሙስ ኦክሎክ ጄነራል ትሬዲንግ ከሄሎ ታክሲ ጋር በመሆን በአገራችን የመጀመሪያ የሆነውን የጎብኚዎች ታክሲ አገልግሎት መጀመሩን ባስታወቀበት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነው የተነገረው።
ኦክሎክ ጄነራል ትሬዲንግ ሥራውን በይፋ የሚያስተዋውቅበት እንዲሁም ተቋማዊ ግብረ ኃይልን በግልፅ የማስተሳሰር መርሃ ግብር በሚል በሸራተን አዲስ ባዘጋጀው የጋዜጣዊ መግለጫ ላይ፣ የኢፌዴሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ሂሩት ካሳ (ዶ/ር)፣ እንዲሁም በቱሪዝም ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ቡዜን አልከድርን ጨምሮ የታክሲ ማኅበር አባላት ተገኝተዋል።
በመርሀ ግብሩም የኢፌዴሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር እና ከኦክሎክ ጄነራል ትሬዲንግ አጋር የማኅበራት ጥምረት ከሆነው ከሄሎ ታክሲ ጋር የጋራ የመግባቢያ ሰነድ ተፈርሟል።
በእለቱ ኦክሎክ ጄነራል ትሬዲንግ ለቱሪዝም ዘርፍ የሚውሉ ተሽከርካሪዎችን በአገር ውስጥ በመገጣጠም ከሄሎ ታክሲ ጋር በትብብር ለተጠቃሚዎች ማቅረብ መጀመሩን ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ መንግሥት ዘርፉን ለማሳደግ ባደረገው የቀረጥ ነፃ እድል መሰረት 2020 ሞዴል አውቶሞቲክና ማንዋል ተሽከርካሪዎችን በ25 በመቶ ቅድመ ክፍያና ቀሪውን በአምስት ዓመታት እንዲከፈል የሚደረግ የብድር ሁኔታን በማመቻቸት ለተጠቃሚዎች ማቅረቡን አስታውቋል።
በዚህም መሰረት ሄሎ ታክሲ 1.5፣ ባለሰባት የፋብሪካ የቆዳ መቀመጫ፣ ባለ አራት ሲሊንደር አውቶማቲክ እና ማኑዋል መኪናዎችን ከአንድ መቶ ሰባ ኹለት ሺሕ አምስት መቶ ብር ቅድመ ክፍያ ጀምሮ ለተጠቃሚዎች መቅረብ መጀመሩን አስታውቋል።
በተጨማሪም ኦክሎክ ጄነራል ትሬዲንግ ለ110 ሥራ አጥ ወጣቶች ለቱሪዝም አገልግሎት የሚውሉ ታክሲዎችን ያለምንም ወለድ በሙሉ የብድር አገልግሎት ለቱሪዝም መሥሪያ ቤቱ እንደሚያቀርብ የገለፀ ሲሆን፣ 10 አንፑላንሶችን እንዲሁም 50 የ59 አገራትን ቋንቋ መተርጎም የሚችሉ እና የአንዱ ዋጋ 25 ሺሕ ብር ሆኖ 1.5 ሚሊዮን ብር የሚገመት ማሽኖችን ለባህል እና ቱሪዝም መሥሪያ ቤት በስጦታ መልክ ማበርከቱን የድርጅቱ የሥራ እድል ፈጠራ እና የተቋም ትስስር አማካሪ ሰለሞን ሙሉጌታ ገልፀዋል።
ሄሎ ታክሲ በታክሲ ሥራ ተሰማርተው ኅብረተሰቡን ሲያገለግሉ ለቆዩና ከድህነት አረንቋ ለመላቀቅ ላልቻሉ 250 ግለሰቦች አሮጌ መኪናቸውን እንደቅድመ ክፍያ ዋጋ ተቀብሎ አዲስ መኪና ለመስጠት ዝግጅቱን ማጠናቀቁን አስታውቋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የኢፌዴሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ሂሩት ካሳ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ እንዲህ አይነት የጋራ ስምምነቶችና ትብብሮች መፍጠር የአገርን ገፅታን ከመገንባቱም በተጨማሪ ለምጣኔ ሀብት ትልቅ ድጋፍን የሚያደርጉ መሆናቸውን በመረዳት ዘርፉን ለማዘመን እና ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት ለመስጠት ተቋማቱ እየሠሩ ያሉትን ሥራ አድንቀው በእውቀት እና በህግ የየተመራ አሰራርን ከተከተልን የቱሪስት ትራንስፖርት ዘርፉ በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳደሪ ለማድረግ እንደሚቻልም አሳስበዋል፡፡
በቀጣይም የቱሪዝም ትራንስፖርቱን ለማሳደግ እና ለማዘመን ለሚሰሩ ስራዎች ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ቃል ገብተዋል፡፡
ቅጽ 2 ቁጥር 89 ሐምሌ 11 2012



