ኢትዮጵያ ባቀረበችው አዲስ የውሃ ሙሌት ሰነድ ላይ ለመምከር ድርድሩ ለሌላ ጊዜ ተሸጋገረ

0
605

በሳለፍነው ሳምንት ሐምሌ 27/2012 ዳግም የተጀመረው የሦስትዮሽ ድርድር ግብጽና ሱዳን ኢትዮጰያ ባቀረበችው አዲስ የውሃ ሙሌትንና አስተዳደር የተመለከተ የመደራደሪያ ረቂቅ ሰነድ ላይ ለመምከር ተጨማሪ ጊዜ ይሰጠን በማለታቸው፣ ድርድሩ ተቋርጦ የፊታችን ሰኞ ነሐሴ 4/2012 እንዲካሄድ መወሰኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ የድርድሩ ለነሐሴ 4/2012 መሸጋገር ዋነኛ ምክንያት ግብጽና ሱዳን ኢትዮጵያ ያቀረበችውን አዲስ የውሃ ሙሌትና አስተዳደር የመደራደሪያ ሰነድ በተመለከተ የውስጥ ምክክር አድርገን የቀረበውን ሰነድ ማጤን አለብን በማለታቸው መሆኑን ጠቁመዋል። ኢትዮጵያ ያቀረበችው አዲስ የመደራደሪያ ሰነድ የውሃ ሙሌትና አስተዳደርን የሚመለከት መሆኑን አምባሳደር ተናግረዋል።

ቃል አቀባዩ እንደሚሉት ግብጽና ሱዳን ኢትዮጵያ ያቀረበችውን አዲስ ሰነድ አጢነው ሲመለሱ ምናልባትም አዲስ አማራጭ ሰነድ አዘጋጅተው ወይ ደግሞ በኢትዮጵያ ሰነድ ሊስማሙ እንደሚችሉ አመላክተዋል። አምባሳደሩ ኢትዮጵያ አዲስ ባዘጋጀችው ሰነድ ላይ ያላትን አቋም ግብጽና ሱዳን በቀጣዩ ድርድር ይዘው የሚመጡትን ሐሳብ መሰረት አድረጎ በቀጣዩ ድርድር የሚወሰን መሆኑን ጠቁመዋል።

ሦስቱ አገራት በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ የሚያደርጉት ድርድር በሐምሌ 20/2012 ከተጀመረ በኋላ ወደ ሐምሌ 27/2012 መሸጋገሩ የሚታወስ ነው።
በዚሁ መሰረት የአገራቱ ድርድር ለፊታችን ሰኞ ነሐሴ 4/2012 ቀጠሮ እንደተያዘለት አምባሳደር ዲና ገልጸዋል። የሦስቱ አገራት ተደራዳሪዎች ሰኞ ሐምሌ 27/2012 በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካኝነት ተገናኝተው በመከሩበት ጊዜ የግድቡ የውሃ ሙሌትና አስተዳደር የተመለከተው ድርድር የሚካሄድበት ሁኔታ ላይ ተወያይተው ስምምነት ላይ መድረሳቸውን የኢትዮጵያ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ከሳምንት በፊት ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ ግብጽ የምታነሳው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅምና የወደፊት ተጠቃሚነት ላይ ጥላ የሚያጠላ ማንኛውንም አይነት ሐሳብ እንደማትቀበል እና በወደፊት ጥቅሟ ላይ ጽኑ አቋም እንዳላት ገልጸው ነበር። አምባሳደሩ አክለውም ወደፊትም ቢሆን ግብጽ የፈለገችውን ነገር ብታመጣ ኢትዮጵያ ተጠቃሚነቷን አደጋ ላይ የሚጥል ስምምነት እንደማታደርግ ጠቁመዋል።

በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን ስምምነት ላይ ካልደረሱባቸው ነጥቦች ውስጥ ዋና ዋናዎቹ የግድቡን የውሃ ሙሌትና አስተዳደርን በተመለከተ በሚደረግ ስምምነት አፈጻጸም ላይ አለመግባበት ቢከሰት የሚፈታበት መንገድ አስገዳጅ ሊሆን አይገባም የሚለው አንደኛው ነው። ሌላው የኢትዮጵያን የወደፊት የውሃ አጠቃቀም ከግድቡ የውሃ ሙሌት ጋር መጣመር አለበት የሚለውና ወደፊት የዓባይ ውሃ አጠቃቀም በማንም መልካም ፈቃድ ላይ ሊመሰረት አይችልም የሚለው የኢትዮጵያ የልዩነት አቋም ነው።

በሦስቱ አገራት መካከል እስከ አሁን የተደረጉት ድርድሮች በግብጽ በኩል ይታይ በነበረው የከረረ ኢ-ምክንያታዊ የተጎጅነት እንዲሁም በዓባይ ላይ አዛዥ ካልሆንኩ አሻፈረኝ ስትል በመቆየቷ የድርድር ሂደቱ ያለ መቋጫ እስከ አሁን ደርሷል። ይሁንና ኢትዮጵያ ግብጽ የምታቀርበውን ውል አልባ ጥያቄ ባለመቀበሏ የኢትዮጵያውያንን የወደፊት የዓባይ ውሃ ተጠቃሚነት እውን ለማድረግ የመጀመሪያ ፈር ቀዳጅ መንገድ ጀምራለች። ይሄውም ኢትዮጵያ የመጀመሪያ ዓመት የውሃ ሙሌት መድል ማጠናቀቋ ነው፤ እንደ አምባሳደሩ ገለጻ።

ቅጽ 2 ቁጥር 92 ነሐሴ 2 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here