መንግሥት የጥቃቱን ብሔር እና ኃይማኖት ተኮርነት በግልጽ ሊያምን ይገባል!

0
616

ባለፉት ኹለት ዓመታት ውስጥ በኢትዮጵያ ከፍተኛ ያለመረጋጋት እና ግጭት ተስተውሏል። የተለየ ሰላማዊ የሚባል ክልል በሌለበት ሁኔታ በክልሎች ውስጥ አናሳ ቁጥር ያላቸው ብሔሮች አባላት ሲገደሉ፣ ሲፈናቀሉ እንዲሁም ንብረታቸው ሲወድም ታይቷል። የእነዚህ ግጭቶች መነሻም ፖለቲካዊ፣ ኃይማኖታዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም ታሪካዊ እየተደረገ ቢቀርብም በዋነኛነት የችግሮቹ ሁሉ መነሻ አክራሪ ብሔርተኝነት እንደሆነ እሙን ነው።

ይህ አገራዊ የሆነ የግጭቶች ስብጥር እስከ አሁን ድረስ አስጊ ሆኖ ከሚገኝባቸው ክልሎች ውስጥ ደግሞ ኦሮሚያ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስ ነው። በአሁን ጊዜ እንኳን በኦሮሚያ ቁጥራቸው በሺዎች የሚቆጠሩ የሌሎች ብሔሮች አባላት እና የክርስትና እምነት ተከታይ ኦሮሞዎች በመንግሥት መዋቅር ስር ከሚገኙ ሰዎችም ሆነ የጥፋቱ ዋነኛ ተዋናይ ከሆነው የወጣቶች ስብስብ ማስፈራሪያ እየደረሰባቸው ይገኛል። በሐረርጌ፣ አርሲ እና ባሌ የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ በተከሰተው ከኹለት መቶ በላይ ሰዎችን ሕይወት ያጠፋ ጥቃት ሰለባ ሆነው ሀብትና ንብረታቸው ተቃጥሎ በተለያየ ቦታ ተጠልለው የሚገኙት ሰዎች አሁንም ማስፈራሪያ እንዳልቆመ እየገለፁ ናቸው። በኦሮሚያ መንግሥት መዋቅር ውስጥ የሚገኙትም ሰዎች ከወንጀለኞቹ ጋር ያላቸው ትስስር እንዳልተበጠሰ እነዚሁ ሰዎች የተለያዩ ገጠመኞቻቸውን እያነሱ ያስረዳሉ።

የመንግሥት መዋቅርም ሆነ የፖሊስ ኃይል እየተገደለ እና እየተሳደደ ያለውን ሕዝብ ከጥቃት ከመከላከል ይልቅ ወሯ የገባ ሴትን የሌላ ብሔር ልጅ በኦሮሚያ ምድር አትወልድም በሚል የሚያርደውን በደም የሰከረ የወጣት ቡድን ሥራ ላለማደናቀፍ በሚጨነቅባት ኦሮሚያ ነገሮችን መልሶ ማስተካከል ከፍተኛ ሥራ እንደሚጠይቅ ግልፅ ነው። በዚህ ዓመት በክልሉ የታዩ ጥቃቶች እንደሚጠቁሙት በክልሉ የሚኖሩ የኦሮሞ ተወላጆችም ሆኑ ሌሎች ዜጎች ሕይወት እና ንብረት ዋስትና ያለው አይደለም።

የፌዴራል መንግሥት የታየውን መረን የለቀቀ ሕገ ወጥነት ለመቆጣጠር ከዚህ በፊት ከነበረው በተሻለ ሁኔታ የተንቀሳቀሰ ቢሆንም ሕይወታችን አሁንም ስጋት ውስጥ ነው፤ ማስፈራሪያ ይደርስብናል የሚሉ ዜጎች አሁንም በስፋት አሉ። በተለይ መንግሥት አቅሙ የተዳከመ መስሎ ቆይቶ ቢነኩ ሥሩን ሊነቀንቁ ይችላሉ የተባሉ ሰዎችም በቁጥጥር ስር መዋላቸው ሲታሰብ የመንግሥት እርምጃ ጠንከር ማለቱ በቀላሉ የሚታይ ነው።

ነገር ግን በፌዴራሉም ሆነ በክልሉ መንግሥታት የነበረው ጥቃት በብሔር እና በኃይማኖት ላይ ያነጣጠረ መሆኑን በግልጽ የማመን ችግር ይታያል። የመንግሥት መዋቅር ውስጥ ያሉ ሰዎች ከተደራጁ ወጣቶች ጋር ሆነው ጥቃቱን እንዳደረሱ በሚያምኑት መጠን ጥቃቱ የብሔር እና የኃይማኖት ቅርፅ ነበረው ለማለት ይቸገራሉ። ይህም የተግባሩን አሸማቃቂነት እና አፀያፊነት ጥቃቱን ያደረሱት ቡድኖች እንዳይሰማቸው በትንሹም ቢሆን ይከላከላል። ሰውን ያረዱ፣ ቤተሰብ ያቃጠሉ እንዲሁም የተለያዩ ለመስማት የሚሰቀጥጡ ነገሮችን ያደረጉ ሰዎች የሕዝብ መብት ታጋይ ነን ብለው መቆም እንዳይችሉ ሊያደርጋቸው የሚችለው ነገር ሥራቸው በአደባባይ መነገሩ ነው። የሰው ሕይወትን የሚያጠፉ ዘረኞችን በተለያዩ የቁልምጫ ስሞች መጥራቱ ከፍተኛ አደጋ አለው።

የተደረጉት ዘግናኝ ተግባራት በግልጽ ተነግሮ መወገዙ የኦሮሞ ሕዝብ የሚታይበት መንገድ ላይ ተጽዕኖ የሚፈጥር አይደለም። ምክንያቱም መላው የኢትዮጵያ ሕዝብም ሆነ የዓለም ሕዝብ ተግባሩን የፈፀሙት ጥቂት ዘረኞች መሆናቸውን ሰለሚያውቅ። ለኦሮሞነት የኃይማኖት መስፈርት አውጥተው በዚሁ መስፈርት ኦሮሞዎችን እንደ ባዕድ ከመቁጠር በዘለለ የሚያጠቁ የተደራጁ ጥቂት ሰዎች ለማንም ሊበጁ እንደማይችሉ ግልጽ ነው።

የአንድ ብሔር አባላት ብቻ ያለመጠቃታቸው ወይም የተጠቁት ኦሮሞን ጨምሮ ከተለያዩ ብሔሮች የተውጣጡ ሰዎች መሆናቸው ብሔር ላይ ያነጣጠረ ጥቃት እንዳልነበር ማሳያ ሊሆን አይችልም። በሩዋንዳው የዘር ማጥፋት ወንጀል ቱትሲዎች ብቻ ሳይሆኑ ሁቱዎችም ተገድለዋል። ነገር ግን ወንጀሉ ዘር ላይ ያነጣጠረ እንደነበር ዓለም የሚያውቀው ሐቅ ነው። ከዚህ በተጨማሪ ክርስቲያን የሆኑ የሌሎች ብሔሮች አባላትም ሆኑ ኦሮሞዎች መጠቃታቸው ደግሞ የኃይማኖት መስመርን የተከተለ ጥቃት እንደነበረ የሚያሳይ ነው። በመሆኑም የክልሉም ሆነ የፌዴራሉ መንግሥት የነበረው ጥቃት የኃይማኖት እና የብሔር ቅርጽ እንደነበረው በግልጽ ሊያሳውቁ እንደሚገባ አዲስ ማለዳ ታምናለች።

በመስከረም 2011 በቡራዩ ከተማ ብሔር ላይ የተመሰረተ ጥቃት ሲከሰት ጉዳዩ ለወደፊት የሚኖረው አደጋ ግምት ውስጥ ሳይገባ ለማለባበስ የተኬደው ርቀት እና ሳይወሰድ የቀረው የማያዳግም እርምጃ በመንግሥት መዋቅር ውስጥም ሆነ በውጪ የጽንፈኝነት ስሜት እንዲደራጅ በር ከፍቷል። ከዚያም በመቀጠል በጥቅምት 2012 የዚያን ጊዜው አክቲቪስት እና የአሁኑ ፖለቲከኛ ጃዋር መሐመድ ተከብቤያለሁ ማለቱን ተከትሎ በኦሮሚያ ክልል ጉዳዩ የማይመለከታቸው ሰዎች ላይ በተከሰተው ጥቃት እንደ ፖሊስ ሪፖርት 97 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።

ይህንንም ጥቃት ተከትሎ መንግሥት ላይ ከፍተኛ ተቃውሞ በኦሮሚያ የተለያዩ ቦታዎች የታየ ሲሆን መንግሥትም ይህንን ለማረጋጋት አክቲቪስቱ ወንድም እንደሆነ እና አብሮ እንደሚሰራ በመግለጽ ሕዝቡ እንዲረጋጋ ሲወተውት ነበር። ይህ መሆኑ ሰላምን ለማምጣት እና ሁኔታዎችን ለማረጋጋት የሚያግዝ ስለሆነ የሚያስወቅስ ባይሆንም ጥቃት የደረሰባቸው ጎን መሆንን ሳያሳዩ እና በበቂ ሁኔታ ጥቃቱን ፈጻሚዎችን ለፍርድ ባለማቅረብ ሲሆን ግን ዜጎች መንግሥት ላይ ያላቸውን እምነት የሚሸረሽር ነው። በሌላ መልኩ ደግሞ ጥቃቱን ያደረሱ ሰዎች ተገቢውን ቅጣት ያለማግኘታቸው የልብ ልብ እንዲሰማቸው እንዲሁም <እሽ አትበሉኝ የሹም ዶሮ ነኝ> ዓይነት ስሜት እንዲላበሱ ያደረገ ነበር።

በመሆኑም በመጠኑም ሆነ በይዘቱ ሰፋ ያለ ጥቃት ለመፈፀም የሚያስችሉት ሁኔታዎች በፊት በተከሰቱት አሰቃቂ ወንጀሎች ፍትህ ማጣት ውስጥ ተመቻችተው ነበር። የሃጫሉን መገደል ነፍሰ ገዳዮቹ የተመቻቸውን ሁኔታ በስፋት ለመጠቀም እንደ ጥሩ አጋጣሚ ተጠቅመው ከኹለት መቶ በላይ ሰዎችን ሕይወት አጥፍተው ከተሞችን በከፊል አውድመዋል።

አሁንም የማያዳግም እርምጃ ተወስዶ እንዲህ ዓይነቱን ወንጀል የፈፀሙ ሰዎች እና ቡድኖች ሙሉ በሙሉ ለፍርድ ካልቀረቡ ሌላ ጥቃት ለመፈፀም የሚያስችሉት ሁኔታዎች እንደተመቻቹ ይቀጥላሉ። በመንግሥታዊ አካላት ጥቃቱን ያደረሱትን ሰዎች ጠቁሙን በመባላቸው የወንጀሉን ተዋናዮች ስም የሰጡትን ተበዳዮች የመንግሥትም ሰዎች ሆኑ ስማቸው የተጠቆመው ወንጀለኞች የሚያስፈራሩበት ሁኔታ ካለ ችግሩ ለመቀረፍ ገና ብዙ ይቀረዋል ማለት ነው። እነዚህ ዓይነት የተበዳዮች አቤቱታዎች ሲሰሙ መንግሥት ተገቢውን ትኩረት ሰጥቶ በፍጥነት ነገሮችን ለመቀየር መንቀሳቀስ ይገባዋል።

የሃጫሉን ግድያ ተከትሎ መንግሥት የከፈተው መጠነ ሰፊ ሕግን የማስከበር እና ወንጀለኞችን ለፍርድ የማቅረብ እርምጃ ዜጎች በመንግሥት ጥንካሬ ላይ ያላቸውን ጥያቄ በአብዛኛው የቀረፈ ቢሆንም ክፍተቶች አሁንም ቢሆን ይታያሉ። በመንግሥት መዋቅር ውስጥም ሆነ ውጭ የተገነባው የጽንፈኞች ሰንሰለት በሒደት የተጠናከረ እንደመሆኑ ሙሉ በሙሉ ለማጥፋትም የሚደረገው ጥረት ጊዜ እንደሚወስድ እሙን ነው። ሒደቱ ግን ግልጽ በሆነ መንገድ የወንጀለኞችን ብሔር እና ኃይማኖት ተኮር አሳፋሪ ተግባራት ከማደባበስ ይልቅ አጋልጦ ለቀጣይ ምቹ ሁኔታዎች እንዳይኖሩ የሚያደርግ መሆን እንዳለበት አዲስ ማለዳ ታምናለች።

ቅጽ 2 ቁጥር 92 ነሐሴ 2 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here