የታላቁን የህዳሴ ግድብ ግንባታ ሙሉ በሙሉ ለማጠናቀቅ 160 ቢሊዮን ብር እንደሚፈጅ ተጠቆመ፡፡ የግድቡ ግንባታ ወጪ ለግድቡ በኮንትራት ደረጃ የተያዘው አጠቃላይ በጀት 78.3 ቢሊዮን ብር ቢሆንም፣ እስካሁን ድረስ ለግድቡ ግንባታ 120 ቢሊዮን ብር ወጪ መደረጉን የግድቡ ግንባታ ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጅነር ክፍሌ ሆሮ አስታውቀዋል።
የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ባሳለፍነው ሳምንት ሀሙስ ነሀሴ 14/2012 ከህዳሴው ግድብ የቦርድ አመራሮች እና ከሚመለከታቸው የፌዴራል መንግስት ከፍተኛ አመራሮች ጋር ውይይት አድርገዋል። በዚሁ መድረክ ላይ እንደተገለጸው የግድቡ አጠቃላይ ግንባታ 75 በመቶ የደረሰ ሲሆን፣ የአሌሌክትሮ ሜካኒካል ስራው 46.5 በመቶ፣ የሲቪል ስራው ደግሞ 88.8 በመቶ መድረሱ ተጠቅሷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፣ ግድቡ በመጪው ዓመት አስፈላጊው ድጋፍና ክትትል ሁሉ ተደርጎለት ነሀሴ 2013 ላይ 18.4 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ እንዲይዝ ይደረጋል፡፡ በዚህ አግባብ መስራት ከተቻለ “በ2015 ዓ.ም የግደቡን የምረቃ ሪባን እንቆርጣለን” ማለታቸውንም የዘገበው የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ነው።
ቅጽ 2 ቁጥር 94 ነሐሴ 16 2012



