የከርሰ ምድር እና ገጸ ምድር ውሃን ለአገልግሎት ለማዋል እየተሠራ ነው

0
988

ኢትዮጵያ ያላት እምቅ የከርሰ ምድር እና ገጸ ምድር ውኃ ለሕዝቦቿ እድገት እንዲውሉ ልዩ አቅጣጫ ተቀምጦ እየተሠራ መሆኑን የመስኖ ልማት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ሳሙኤል ንጉሤ (ኢ/ር ) አስታወቁ።

ከ493 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ እና ከ125 ሺህ ሔክታር መሬት የሚያለሙ የመስኖ ፕሮጀክቶች በኢትዮጵያ መገንባታቸውንም ገልፀዋል።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በሦስት ክልሎች ግንባታቸው እየተካሄዱ የነበሩ ግድቦች ለአገልግሎት መብቃታቸውን የገለፁት ምክትል ኮሚሽነሩ “ባለፈው በጀት ዓመት በኦሮሚያ ክልል የሚገኙት የጊዳቦ እና የአዳአበቹ፣ በአማራ ክልል የሚገኘው የርብ ግድብን ጨምሮ በደቡብ ክልል የሚገኘውን የዝዋይ ግድብ በማጠናቀቅ ማስመረቅ ተችሏል” ብለዋል።

“የተጠናቀቁት ፕሮጀክቶች ከ125 ሺህ ሔክታር መሬት በላይ በማልማት በየአካባቢው የሚገኙ ከ493 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ያደርጋሉ” በማለት ተናግረዋል።

ከእነዚህም መካከል በኦሮሚያ ክልል የአርጆ ደዴሳ መስኖ ግድብ ፕሮጀክት 80 ከመቶው በመፈጸም፣ ከግድቡ ተጓዳኝ የሆኑ ሥራዎችን በማከናወን በቀጣይ ዓመት ለማጠናቀቅ እየተሠራ ነው” ብለዋል።

የአርጆ ደዴሳ መስኖ ግድብ ግንባታ ሲጠናቀቅ እስከ 80 ሺህ ሔክታር መሬት እንደሚያለማም ያስረዱት ምክትል ኮሚሽነሩ በአማራ ክልል የመገጭ ግድብ ግንባታ 68 ከመቶ፣ የዛሪማ ግድብ ግንባታ ደግሞ 92 በመቶ የደረሰ ሲሆን ፕሮጀክቶቹን በቀጣይ ዓመት ለማጠናቀቅ ሰፊ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

እነዚህ ፕሮጀክቶች ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቁ ከ61 ሺህ ሔክታር መሬት በላይ በማልማት በርካታ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ማድረግ ያስችላሉ” ሲሉም አስታውቀዋል።
ኢትዮጵያ ከ30 እስከ 40 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር የሚገመት የከርሰ ምድር ውኃ እንዳላት እና በክረምት ወራት መጠኑ ከ124 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውኃ በላይ እንደሚደርስ መረጃዎች ያመለክታሉ።

በአገሪቱ በመስኖ ለመልማት የሚችል ከ5 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሔክታር መሬት እንደሚገኝ መረጃዎች ያሳያሉ ተብሏል።

ቅጽ 2 ቁጥር 94 ነሐሴ 16 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here