ማን ይጠቀማል?

0
499

የጠቅላይ ሚኒስት ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን መምጣት ተከትሎ ሴቶች ወደ ሹመት ሲመጡ ታዝበናል። በበቂ ደረጃ ነው ወይ የሚለው አጠያያቂ ሆኖ ይቀጥል እንጂ፣ ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታዎች ሴት አመራሮች እንዲይዙ ተደርጓል። ጠቅላይ ሚኒስትሩም ለጉዳዩ የሚሰጡትን ትኩረትና መንግሥታቸው የያዘውን አቅጣጫ ሲያስረዱ ተሰምቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያንን የለውጥ መንገድ ከከፈቱ ከኹለት ዓመት በኋላ አሁን ምን ደረጃ ላይ ይገኛል የሚለውን ነጥብ እናንሳ። እንደ አዳነች አቤቤ ጠንካራና ተጨባጭ ለውጥ ያሳዩና ያመጡ፣ ጾታም ሆነ ብሔርን አስረስተው ሥራቸው ላይ እንድናተኩር የጋበዙ ሰዎችን አለማንሳት አይቻልም። ለዘመናት ወንዶች በኃላፊነት በመሯቸው ተቋማት ሴቶችም የተሻለ ለውጥ ሊያመጡ እንደሚችሉ ምስክር ነው።

አሁን ላይ አዳነች አቤቤ ወደ አዲስ አበባ አስተዳደር መምጣታቸውን ተከትሎ ብዙ ለውጦችን ተስፋ ያደረጉ ሰዎች አሉ። ሴት ስለሆኑ ብቻም ሳይሆን አስቀድሞ በሠሩባቸው መሥሪያ ቤቶች ያሳዩትን ለውጥ በመመልከት ነው። የእኔ ስጋት ግን ይህም ሳይሆን በሥልጣን ላይ ወዲያ ወዲህ የሚቀያየሩት ጥቂት ሴቶች የመሆናቸው ጉዳይ ነው። አዲስ ተሿሚዎች ውስጥ ሴቶችን አናገኝም።

በእርግጥ አስቀድሞ ነገር የሹም ሽረቱ ሂደት ያልተስማማቸው አሉ። ምክንያቱ በግልጽ ያልታወቀና ግልጽ ያልሆነ ሲሉ የሚኮንኑትም ጥቂት አይደሉም። በተጓዳኝ አለመረጋጋት የሰፈነበት ወቅት በመሆኑ ለሿሚና ሻሪ አመራሩም ነገሮች ውስብስብና ከባድ ሊሆኑ እንደሚችሉ መገመት አይከብድም።

ነገራችን ግን ወዲህ ሥልጣን ላይ ሴቶች የመቀመጣቸው ነገር ብቻ ሳይሆን በማኅበረሰብ ውስጥ ያለው ድርሻቸውንም የሚመለከት ነው። ይህም ሿሚና ሻሪ የሌለው የወላጅነት፣ የአሳዳጊነትና የቤተሰብነት ሚና ነው። ሻሸመኔ ላይ ከአርሲ፣ አርሲ ላይ ከሌላ ስፍራ፣ ሌላው ስፍራ ላይ ከሻሸመኔ የሚሄዱ ወጣቶች ጥፋት ሲያጠፉ ስናይ፣ ምን ዓይነት ወላጅ ወይም ቤተሰብ ቢያሳድጋቸው ነው ብለን መጠየቅ ያለብን ይመስለኛል።

ተንጋዶ ያደገን ዛፍ ውሃ በማጠጣት ማቃናት አይቻልም። ይልቁንም ውሃ ማጠጣቱ እንደተጣመመ እንዲያድግ ነው የሚያግዘው። እናም መንግሥት ስላልወሰደው እርምጃ ከማንሳት በፊት ቤተሰብ በእንቁላሉ ጊዜ ያልቀጣው ሰው እንዳለ ማሰብ አስፈላጊ ነው ብዬ አምናለሁ። በዚህም የሴቶች ድርሻ ትልቅ ነው።

እንደሚታየው በብዙ ጥፋት ውስጥ ተሳትፈው የሚታዩ ወንዶች ናቸው። ወንድ ልጅ ደግሞ ለእናቱ ቅርብ እንደሚሆንና እንደሆነ ነው የሥነ ልቦና ባለሞያዎች የሚናገሩት። ታድያ እናቶች ይህንን ኃይል እንዳይጠቀሙና ልጆቻቸውን ለአገር የሚጠቅሙ አድርገው እንዳያሳድጉ እንቅፋት የሆነባቸው ምንድን ነው?
የብሔርና የተጠቃሚነት ጥያቄ የተነሳ እንደሆነ ከማንምና ከምንም በላይ ድርብ ፈተና እና ጉዳት የደረሰባቸው ሴቶች ናቸው። ግጭት ቢነሳ ተጎጂ፣ ወገኔ በሚሉትም ሆነ ከሌላ በመጣ አጥፊ የሚደፈሩና ስቃይ የሚያዩት እነርሱ። ከሴቶች የበለጠ አመጽም ሆነ ጩኸት የሚያምርበት ይኖራል? አይመስለኝም።

ነገር ግን ከዚህ መፍትሔ እንደማይገኝ ባለ አእምሮ ወንዶች እንዲሁም ሴቶች በሚገባ ይረዳሉ። ለዚህም አገር ማጥፋትንም ሆነ አገር ሲጠፋ ዝም ብሎ ማየት ውስጥ አይሳተፉም። በአንጻሩ ሰላምን ለማምጣት ልጆቻቸውን ይይዛሉ፣ የትዳር አጋሮቻቸውን ያርቃሉ። ይህ ድርሻ ሴቶች ላይ የሚወድቀው በተለየ ሴቶች ስለሆኑም ነው። በእናትነት ውስጥ ፈተናውንና የነገሩን ክብደት ከሚገባው በላይ ይረዱታልና።

እናስ ማን ይጠቀማል? ሴቶችም ወደ ሥልጣን በማምጣት አገር እንዴት ልትጠቀም እንደምትችል ታይቷል። ይህም ተጨማሪ ኃይልና ጉልበት ስለሚሆን እንጂ ሴቶች ብቻ ሁሉን ይቆናጠጡ በማለት አይደለም። ሴቶች ቤተሰባቸውን፣ ልጆቻቸውን በማረቅና በመቆጣት፣ በቤት ውስጥ ያላቸውን ሥልጣን በሚገባ በመጠቀምም አገራዊ ሰላምን ሊያመጡ እድል አላቸው።
ሊድያ ተስፋዬ

ቅጽ 2 ቁጥር 94 ነሐሴ 16 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here