…ከንግግር ይፈረዳል

0
768

ንግግር የሰው ልጅ መግባቢያውና ዓለምን በየመልኩ ይዞ እንዲያቆያት የረዳው ትልቁ መሣሪያ ነው። በሥራ የሚገለጥ እንዳለበት እሙን ሆኖ፣ በራሱ ንግግርና አንደበትን መግራት ወሳኝና ተገቢ መሆኑም አያጠያይቅም። መቅደው ቹቹ ይህን ጉዳይ አንስተው ትዝብታቸውንና ጽሑፎችን አጣቅሰው እንዲህ አቅርበዋል።

አንደበት የሰላ መሣሪያ ነው። ከንግግር ጋር በተገናኘ ያሉ ብሂሎቻችንን ስንመለከትም ለንግግር ትልቅ ቦታ ይሰጣሉ። በተያያዘም አንደበትን ቁጥብ ማድረግና መጠንቀቅን ያበረታታሉ። እንደውም በርካታ ሃይማኖት ያለው ሕዝብ ይገኝባታል በምትባል አገር፣ ‹ወደአፍ የሚገባ ሳይሆን ከአፍ የሚወጣ ነው የሚያስኮንነው› በሚል ጾምን የተመለከተ ሙግት ሳይቀር ይቀርባል። ግን እንጠይቅ፤ አንደበታችን ምን ያህል የተገራ ነው? በየስፍራው የምንሰማውስ ምንድን ነው?
መልካም ምላስ ቁጣን ታበርዳለች፣ ከአያያዝ ይቀደዳል ከንግግር ይፈረዳል፣ ዝም ባለ አፍ ዝንብ አይገባም፣ አፍ ሲከፈት ጭንቅላት ይታያል፣ ካለመናገር ደጃዝማችነት ይቀራል፣ በለፈለፉ በአፍ ይጠፉ፣ የምላስ ወለምታ በቂቤ አይታሽም፣ ወዘተ መደበኛ እንዲሁም መደበኛ ያልሆኑ ብሂሎችና ጥቅሶችን ማንሳት እንችላለን። ስለንግግርም በዚህና በብዙ መልክ በስፋት ተነስቷል።

በዚህ ሁሉ የምንረዳው ነገር ቢኖር ንግግር ምን ያህል ኃይል እንዳለው እናም ግን ደኅና ነገር መናገር ካልተቻለ አለመናገርና ዝም ማለት እንደሚመረጥ ነው። እስቲ በተወሰኑ አባባሎች መሠረት እውነታችንንና ዙሪያችንን እንመልከት።

‹መልካም ምላስ ቁጣን ታበርዳለች›
በትዳር፣ በማኅበራዊ ግንኙነት፣ በሥራ ቦታ፣ በሥልጣን ላይ ባለ መሪና ተመሪ መካከል ንግግር ትልቅ ስፍራ ይይዛል። እርግጥ ነው ሥራም ወሳኝ ነው። አብሮት የሚሄድ ንግግርም ታድያ የሚናቅ አይደለም። የተናደደን የትዳር አጋር፣ የተከፋን ጓደኛ፣ የተቆጣን ሕዝብ ለማብረድ ንግግር ወሳኝ ናት።

ገጥሟችሁ ያውቃል ብዬ አምናለሁ። መንገድ ላይ ከሰው ተጋጭታችሁ፣ የሰው እግር ሳታስቡት ረግጣችሁ፣ ወይ በትከሻ ተመታታችሁ፣ ውሃ አልያም ትኩስ መጠጥ አስደፍታችሁም ቢሆን የተጊጆው ሰው ግብረ መልስ በእናንተ አንደበት የሚወሰን ነው። ‹‹ወይ ወንድሜ! በጣም ይቅርታ….ይቅርታ የኔ እህት…ሳላይ ነው የእኔ እናት ይቅርታ›› ካላችሁ የተገፋው፣ የተመታው ወይም የተደፋበትና የተረገጠው ሰው ‹ችግር የለም!› ነው መልሱ።

በአንጻሩ እንዳልሰማ ብታልፉት ግን ስድብና ቁጣ ይከተላችኋል። ይህ በሌሎች የምንታዘበው እኛም ልናደርገው የምንችለው እውነትና ክስተት ነው።

‹ከአያያዝ ይቀደዳል ከአነጋገር ይፈረዳል›
ክቡር ዶክተር አርቲስት ጥላሁን ገሠሠ ከሠራቸው አይረሴና ምርጥ ሙዚቃዎች መካከል አንዱን ላውሳ፤ እንዲህ ይላል፤
‹‹ያም ሲያማህ ያም ሲያማህ
ወገኔ ለእኔ ብለህ ስማ፤›› ይላል።

ይህ በተለይ ለእለት እለት ማኅበራዊ ሕይወታችን ውስጥ የምናየውን መተማማት ወይም ሐሜት የሚያነሳ ነው። ‹ነግ በእኔ› አልያም ሲብራራ ‹ነገም በእኔ ሊደርስ/ሊሆን ይችላል› ብሎ ማሰብን የሚያስታውስ ነው። በዚህ ሙዚቃ ‹እንዲህ ብለው አሙህ ቢሉህ አትስማቸው፣ ለወሬ ፍሬ የለውምና። ደግሞም አይጎዳህም› ይላል።
ይህ ለሚታማ ሰው ምክር ይሁን እንጂ ሰዎች በንግግራቸው ምን ያህል እንደሚመዘኑ የሚያሳይ ነው። ‹እገሌኮ እንዲህ ነው› ብሎ ሌላን ሰው ያማልህ፣ ነገ አንተኑ ወይም አንቺኑ ለሌላ እንደማያማ ምን ዋስትና አለህ/አለሽ? በጸባዩ ሐሜተኛ የሆነ ሰው ዛሬ አንዱን አምቶልን ነገ እኛም ለሌላ ላያማን አይችልም፣ ጸባዩ ስለሆነ።
እናም ከንግግር ይፈረዳል። ንግግርና አነጋገር ወደድንም ጠላን ያስፈርዳል። የጥላሁን ገሠሠን ሙዚቃ አንስተን የቅርብ ማኅበራዊ ኹነታችንን ጠቀስን እንጂ፣ ‹አፍ ሲከፈት ጭንቅላት ይታያል› የሚለው ብሂል ከዚህ ጋ ተቀራራቢና ተያይዚ ሊነሳ የሚችል ጉዳይ ነው።

ሰዎች መናገር ሲጀምሩ፣ ሐሳባቸውን ሲያካፍሉና ምን እንደሚያስቡ ሲገልጹ በጭንቅላታቸው ያለውን መገመትና ማወቅ ይቻላል። ሐሰተኛ ከሆኑም በኋላ ላይ ድርጊታቸው ማሳበቁ አይቀርም። እናም እንደ አያያዛችን ሁኔታ የያዝነው እቃ ደኅንነት እንደሚጠበቅ ሁሉ፣ እንደ አነጋገራችንም ማንነታችን ይታያል።

‹የአፍ ወለምታ በቂቤ አይታሽም›
ምላስ አጥንት ባይኖራትም አጥንት ትሰብራለች ይባላል። እውነት ነው! አንድ ነገር ከተናገርን አልያም አምልጦን ‹የግራ ጎን› ሐሳባችን ያቀበለንን ነገር ከተናገርን ወዲህ፣ መመለስ የማይታሰብ ነው። ሰሚዎች ሁሉ የመርሳት ችግር እንዲያጋጥማቸው መጸለይ ካልሆነ በቀር!

እንዲህ ባለ ዘመናዊና ታሪክና ኹነት ከአፍ አልፎ በቴክኖሎጂ ተከትቦ ከትውልድ ትውልድ በሚሸጋገርበት ጊዜም፣ የአፍ ወለምታ በቂቤ ያለመታሸቱ ነገር ይጸናል። በእርግጥ በይቅርታ የማይጸዳ ነገር እንደሌለ እሙን ነው።

እነዚህን እንደማሳያ ጠቅለል ያሉ ሐሳቦችን እንዲሰበስቡልን አነሳን እንጂ በጉዳዩ ላይ ብዙ ማለት ይቻላል። ታድያ ይህን ጉዳይ እንዳነሳ ምክንያት ወደ ሆነኝ ጉዳይ ልዝለቅ። አዲስ ማለዳ በነሐሴ 9 ቀን 2012 በወጣው 93ኛ እትሟ ርዕሰ አንቀጽ ላይ ‹ተናጋሪዎች ዝም በሉ፤ ዝም ያላችሁ ተናገሩ› የሚል አቋሟ የተገለጠበትን ጽሑፍ አስነብባለች።

አዲስ ማለዳ ስትጀምር ስለተከሰቱ ኹከቶችና አለመረጋጋቶች፣ እነሱን ተከትሎም ስለተፈጠሩ የንጹሐን ዜጎች ሞት ጠቅሳለች። ይህንንም ወደ ለውጥ በሚደረግ ጉዞ አንጻር ይህ ዓይነቱ ክስተት የሚጠበቅ ቢሆንም፣ ከመንግሥት ቅርብ በሆኑ አካላት የሚወጡ ዲስኩሮች የሚያደርሱትን ጥፋት አውስታለች። የጥቃት መነሻዎችም እነዛ ከአንደበት የሚወጡ ‹ያልተኖረባቸው ታሪኮች› ናቸው ስትል ትጠቅሳለች።

ከንግግር ተነስቶ አገርን አዳርሶ ወደማበጣበጥ የደረሰው ድርጊት በእንቁላሉ ጊዜ ያልተገታው ነው። ይህም ነው በርካቶችን ለሞት፣ ለንብረት መውደም እና ከቤት ንብረት ለመፈናቀል የዳረገው። ጋዜጣዋ የቅርብ ጊዜው ድምጻዊ ሀጫሉ ሁንዴሳ ሕልፈት አስታውሳ፣ ያንን ተከትሎና በዛ ሳይበቃ አሰቃቂ፣ ለሰው መናገር የማይመች፤ ማሰብም የማያስፈልግ ድርጊት ተፈጽሟል።

የሥራ ኃላፊዎችና የመንግሥት ባለሥልጣናት ይህን ተከትለውና ከዚህ ክስተት በኋላ የተለያዩ ንግግሮችን አድርገዋል። በአንድ ጎን ማኅበራዊ ሚድያ ላይ ያለውን የጥላቻ ንግግር እንቆጣጠር እየተባለ በሌላ በኩል ራሳቸው ባለሥልጣናቱ የሚናገሩትን አግባብ ያልሆነ፣ ያልተቆጠበ፣ ጭንቅላታቸውን የሚያሳይና በዛም ዝቅ የሚያደርጋቸው ንግግር ከልካይ ያጣ ይመስላል።

በዚህ ዓይነት ሰው ፊት የሚያወሩትና ዝግ ባደረጉት መድረክና ስብሰባ ‹ከወገኔ ጋር› ብለው የሚዘረግፉት ሐሳብ የተለያየ መሆኑ ግልጽ ይሆናል።
እዚህ ላይ አዲስ ማለዳ የተጠቀመችውን ሐሳብ ቀጥታ እንደወረደ ባሰፍር ወደድኩ። እንዲህ ስትል ትገልጻለችም፤ ‹‹እነዚህ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ሆነው በማን አለብኝነት ሲናገሩ እና በአመራር ላይ ላለው ለራሳቸው መንግሥት ጸር የሆኑ ከፍተኛ መንግሥት ኃላዎቸችም ሀይ ሊባሉ የሚገባው ከአሁኑ ሰዓት ጀምሮ ሊሆን ይገባል። ከሰሞኑ ኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ የኦሮሞ ልሒቃንን ከሰባት ወር በፊት ሰብስበው ተናግረዋል የተባለው መረጃ በማኅበራዊ ትስስር ገጾች ሲዘዋወር እና በርካቶችን እንዳስከፋ መታዘብ ተችሏል።

ከዚህም ባሻገር ነሐሴ 5/2012 ጀምሮ በነሐሴ 6/2012 የተደመደመው የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ውይይትም በዚህ ዙሪያ ሰፊ ውይይት ማድረጉ ተሰምቷል። በውይይቱ ማጠቃለያ ላይም የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ በባህር ዳር ከተማ በመገኘት የተባለው ነገር ብልጽግናን ወይም ኦሮሚያን ብልጽግናን የማይወክል ከመሆኑንም በላይ ርዕሰ መስተዳደሩ ማለትም ሽመልስ አብዲሳ የሚገመገሙበት ጉዳይ መሆኑንም ይፋ ማድረጋቸው ይታወቃል።

የለውጡ ዋና አቀንቃኝ ናቸው ከሚባሉት የብልጽግና ዋና አመራር የሚባሉት ሽመልስ አብዲሳ በግልጽ ቋንቋን መሰረት ባደረገ እና ‹አማርኛን ገድለነዋል፤ ኦሮምኛን እያሳደግን ነው› በሚል የተናገሩት ሕዝብ እና ሕዝብን ከማቃቃር ባለፈ ሕዝብ በመንግሥት ላይ ከፍተኛ የሆነ አመኔታ እንዳይኖረው የሚያደርግ ድርጊት በመሆኑ ሊታረም ይገባል።

ሽመልስ አብዲሳ በ2012 መስቀል አደባባይ ላይ ኢሬቻ በዓል በሚከበርበት ወቅትም አንድን ቡድን በሚያጥላላ መልኩ ያደረጉት ንግግር በርካቶችን ሲያስቆጣ መቆየቱ የሚታወስ ነው። በዚህም ዝም ተብሎ በመታለፉ ወይም ጠንከር ያሉ ድርጅታዊ እርምጃዎች ባለመወሰዱ ዘፈቀደ ንግግሮች አሁንም ወደ ሕዝብ መድረሳቸው ሕዝብን የሚያቃቅር በመሆኑ ዝም ተብሎ ሊታለፍ አይገባም።›› ስትልም አሳስባለች።

ለዚህ ነው አንደበት ሊገራ ይገባል የምንለው። በተለይ ደግሞ ኃላፊነት ቦታ ላይ ያሉ ሰዎች በአደባባይም ሆነ በጓዳ ሆነው የሚያወሩት ነገር ላይ ሊጠነቀቁ ይገባል። ቢያንስ ቆሻሻና አግባብ ያልሆነ፣ በብዙኀን ተቀባይነት የሌለው የጥፋትና ግለኛ የሆነ ሐሳብ ቢኖራቸው፣ ለራሳቸው ለመያዝ የሚያስችል ‹ችሎታ› ቢኖራቸው ይመረጣል። አለበለዚያ ዝም ማለት ይሻላል።

እርግጥ ነው! የሚናገሩት ነገር ውሃ የማያነሳ ከሆነ፣ የማይጠቅምና ጭራሽ ግጭትና ብጥብጥ የሚፈጥር ከሆነ፣ ዝም ማለቱ ይበልጣል። ‹ዝም ባለ አፍ ዝንብ አይገባም› የሚባለው ለዚህ ነው። በአንጻሩ ደግሞ መናገርም አስፈላጊ የሚሆንበት ጊዜ አለ።

‹ዝምታ ያለቦታው›
አጥፊ ሐሳብ ካላቸው ሰዎች የበለጠ በጎ ሐሳብ ያላቸው ብዙ ናቸው። ‹እናፍርስ› የሚሉ ሰዎች ድምጽ ጎልቶ ይሰማ እንጂ ‹እንገንባ› የሚሉት እልፍ ናቸው። ግን በአገራችን ብቻ ሳይሆን በዓለም ደረጃ አሸናፊነታቸው በተደጋጋሚ የሚታይ አይደለም። ምክንያቱም ዝም ይላሉ። ለዚህ ይመስለኛል አዲስ ማለዳም ‹ተናጋሪዎች› ዝም በሉ ብላ፣ ዝም ያሉት እንዲናገሩ የጋበዘችው።

ዝም ማለት የሌሎችን ጩኸት ያጎላል እንጂ አያደበዝዝም። የተሻለ የሰላም ሐሳብ ያለው ሰውም ዝም ማለት የለበትም። ይህም ቤቱን ሌባ እየዘረፈው ሳለ መሣሪያና መከላከያ እንደሌለው ዝም ብሎ ሲቃጠልበትና ሲዘረፍበት እንደሚያይ ሰው ያስቆጥራል።

በሌላ በኩል ሀብት እያለን እንደማንጠቀምበት ነው፣ መልካም ሐሳብ እያለን ዝም ማለታችን። እንደውም ሲከፋም ከአጥፊዎች በላይ ለማልማት ያለውን መሣሪያ አለመጠቀም ያስኮንናል። አዲስ ማለዳ ይህን በሚመለከት በዛው ርዕሰ አንቀጽ ያለችውን ላውሳ፤

‹‹በአራቱም ኢትዮጵያ ማእዘን አንድነትን ጠብቀው፤ በአገር እና በሕዝብ ላይ ተስፋ ሳይቆርጡ የቆዩ ‹ብንናገር ሰሚ አናገኝም› በሚል ምጡቅ ሐሳባቸውን የሰበሰቡ ግለሰቦች ወደ አደባባይ መምጣት እንደሚኖርባቸው እሙን ነው። ጽንፍ የወጣን ጉዳይ በሌላ ጽንፍ በያዘ እና ‹እኛ እና እነሱ› በሚል ጎራ ተለይቶ በመጠዛጠዝ ሳይሆን በበሰለ አገራዊ ስሜት በመሸፈን እያቆጠቆጠ ያለውን ጽንፈኝነት ጎምርቶ ፍሬ ሳያፈራ ከወዲሁ የሚቀጭበት መንገድ ሊፈጠር ይገባል።››
ወዲህ ደግሞ በሃይማኖት መጽሐፍት የሚነሳውን አንድ ታሪክ ላነሳ ወደድኩ፤ እንዲህ ይላል።

አንድ ባለመሬት የእርሻ ቦታ ያለው ለተለያዩ ሰዎች ሠርተው እንዲለወጡበት ሀብት ሰጣቸው። ለአንደኛውም በተለየ አንድ ብቻ ሲሰጠው ለተቀሩት ዘገን አድርጎ አስረከባቸው። እናም ሲመለስ የሰጣቸውን እንዲመልሱለት አላቸው። ከዛም ሲመለስ በብዛት የሰጣጨው በተሰጣቸው ሠርተውና አትርፈው ሲጠብቁት አንድ የተሰጠው ግን ቀብሮ ያቆየውን ሀብት አውጥቶ መለሰ። ይሄኔ ባለሀብቱ ተቆጣ። ይህ ሰው በተሰጠው አላተረፈም፣ አልሠራበትምና።

ነገሩ እኔን በገባኝ ልክ የተገናኘላችሁ ከሆነ፣ እንደዚህ የተሰጠውን እንቁ እንደቀበረ ሰው በዝምታ ውስት መልካም ሐሳብን መቅበር ዋጋ ያስከፍላል። ሽልማትም አያሰጥም። እናም ዝም ያለ ይናገር። አስተዋይ የሆነ ባለአእምሮ ምላሱ ቁጣን ታበርዳለች። ዝም በማለቱ ለራሱ ደጃዝማችነት ከማስቀረቱ በላይ የአገር ሰላምም ጎድሎ እንዲቆይ ያደርጋል። ንግግራችንን በዚህ መልክ ልብ እንበል! እንጠይቅም፤ አንደበታችን ምን ይመስላል?

ቅጽ 2 ቁጥር 94 ነሐሴ 16 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here