ኢትዮጵያ ከምታገኘው የውጪ ንግድ ገቢ ውስጥ ዋነኛው ድርሻ በሚወስደው የወርቅ ምርት ላይ እየታየ የሚገኘውን የገቢ እና የምርት እጥረት ለመቅረፍ የኢትዮያ ብሄራዊ ባንክ ከዚህ በፊት ወርቅ ይገዛበት የነበረውን ዋጋ ከ5 በመቶ እስከ 30 በመቶ የሚደርስ ማሻሻያ ማድረጉ ተገለጸ።
የአትዮጵያ የወርቅ የወጪ ንግድ በ2003 ከነበረበት 420 ሚሊየን ዶላር በከፍተኛ ሁኔታ በማሽቆልቆል በባለፈው 2011 ወደ 27 ሚሊየን ዶላር የደረሰ ሲሆን ይሄም የሆነው አብዛኛው የአገሪቱ የወርቅ ምርት በህገ ወጥ መንገድ በድንበር ወጥቶ ወደ ዱባይ፣ ህንድ እና ሌሎች አገራት እንዲላክ በመደረጉ እንደሆነ የብሔራዊ ባንክ ገዢ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) በባንኩ ዋና መስሪያቤት በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።
ከዚህ በፊት ህገ ወጥ የወርቅ አውጪዎች እና ደላሎች ወርቅ የሚገዙበት ዋጋ ከብሄራዊ ባንክ የወርቅ መግዣ ዋጋ ቢያንስ በ8 ብር በግራም ይበልጥ የነበረ ሲሆን ይህም ከህገ ወጥ ወርቅ አውጪዎች እና ደላሎች በተጨማሪ በህጋዊ መንገድ ወርቅ በማውጣት ለብሄራዊ ባንክ ያቀርቡ የነበሩ መአድን አውጪዎችን ጭምር ወደ ህገ ወጡ ገበያው እንዲሳቡ ያደረገ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል።
ይህም ሁኔታ የአገር ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ የሚባል ጉዳት እያስከተለ በመሆኑ ብሄራዊ ባንክ የወርቅ መግዣ ዋጋውን ከህገወጥ የወርቅ ዋጋ እኩል እንዲያስተካክል አስገድዶታል።
ከቅርብ አመታት ወዲህ የውጪ ምንዛሬ እጥረትን ለማቅለል የሚያስችሉና ከውጪ ንግድ ጋር የተያያዙ እርምጃዎች እየተወሰዱ ናቸው ያሉት የብሄራዊ ባንክ ገዢ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) የወርቅ የውጪ ንግድም እንደሌሎች የውጪ ንግድ ዘርፎቻችን በከፍተኛ ሁኔታ እያሽቆለቆለ የመጣና የውጪ ምንዛሬችንን በከፍተኛ መጠን እየቀነሰው መሆኑን ባለፉት አመታት ስናስተውል ቆይተናል ብለዋል።
ነገር ግን ብዙ ጥናቶችን አድርገን በጎረቤት አገራት እና በምንዋሰንባቸው ድንበሮች አካባቢ በተለይም በህገ ወጥ ንግድ (ኮንትሮባንድ) ላይ የተሰማሩ ግለሰቦች ወርቅን በምንያህል ዋጋ ገዝተው በምን ያህል ዋጋ እንደሚሸጡ ሰፊ ጥናቶችን በማጥናት እንደዚሁም በሌሎች አገራት ያለውን የወርቅ መግዣ ዋጋ ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት ብሄራዊ ባንክ ወርቅ የሚገዛበትን የመግዣ ዋጋ በከፍተኛ መጠን እንዲያሻሽል ተደርገዋል ሲሉም አስታውቀዋል፡፡
ይሄንን እርምጃ ከተወሰደ በኋላ በአማካኝ የ60 ሚሊየን ዶላር ገቢ በየወሩ ከወጪ የወርቅ ንግድ መገኘት መጀመሩን ይናገር ገልፀው ይህም በአንድ የፖሊሲ ማሻሻያ ምክያት የተገኘ ለውጥ መሆኑንም ነው ገዢው የተናገሩት፡፡
ይህ የወርቅ ግብይት መጠን ከጊዜ ወደጊዜ እያደገ እንደሚሄድ በመገመቱ፣ በመጪዎቹ ወራትም ከወርቅ የሚገኘው ገቢ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ እንደሚሄድ ይጠበቃል፡፡ ከማሻሻያው ቀድሞ ከዓለም የወርቅ ዕለታዊ ዋጋ መሰረት የአምስት በመቶ ብልጫ የሚታሰብበት ዋጋ ለአቅራቢዎች ይሰጣቸው ነበር፡፡ ይህ ተስተካክሎ አብልጫ ባለው ዋጋ ብሔራዊ ባንክ እስከ 30 በመቶ ጭማሪ በማድረግ ወርቅ እየገዛ እንደሚገኝም ለማወቅ ተችሏል።
ይህም ወደ ባንክ የሚመጣውን የወርቅ ማዕድን መጠን ማሻሻል በመቻሉ ወደፊት ከወርቅ የሚገኘው የወጪ ንግድ ገቢ ለማሳደግ ያግዛል ያሉት ይናገር ማሻሻያውን ተከትሎ ብሄራዊ ባንክ በየወሩ የሚገዛውን የወርቅ መጠን በከፍተኛ መጠን መጨመሩን በማንሳት እንደምሳሌም በሀምሌ ወር ብቻ የ72 ሚሊየን ዶላር የሚደርስ ወርቅ ግዢ መፈፀሙን ገልፀዋል፡፡
የመግዣ ዋጋው ማሻሻያ ከተደረገበት ወቅት ወዲህ በየወሩ በአማካኝ እስከ 30 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት የወርቅ ምርት ወደ ባንኩ መቅረብ መጀመሩንም ገዢው ተናግረዋል።
ቅጽ 2 ቁጥር 94 ነሐሴ 16 2012



