በ2012 በጀት ዓመት በኮንትሮባንድ መከላከል 27.4 ቢሊዮን ብር ማዳን ተችሏል

0
771

• ካለፈው አመት ጋር ሲነፃፀር 49 በመቶ ጭማሪ አለው

ባለፈው 2012 በጀት አመት በኮንትሮባንድ መከላከል እንዲሁም በክትትል ሒደት 27 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ማዳን እንደተቻለ ተገለጸ፡፡
የገቢዎች ሚኒስቴር ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቀው ኮንትሮባንድን እና የንግድ ማጭበርበርን ለመቆጣጠር በተደረገው ድንገተኛ ፍተሻዎችና የክትትል ስራዎች አገር ልታጣው የነበረ 27ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ማዳን መቻሉን የተገለፀ ሲሆን የተገልጋይ እርካታንም 74 በመቶ ደርሷል ተብሏል፡፡

የኦዲት ስራዎች ግኝትን በሚመለከት ከታክስ ኦዲት 65.9 ቢሊየን ብር፣ ከምርመራ ኦዲት 11.8 ቢሊየን ብር እንዲሁም ከድህረ እቃ አወጣጥ ኦዲት 5.3 ቢሊየን ብር በግኝት የተወሰነ ሲሆን ሀሰተኛ ደረሰኞችን የማቅረብ፣ ወጪን ማናርና ገቢን የማሳነስ ችግሮች እያጋጠሙ በመሆኑ ተቋሙ በቀጣይ የደረሰኞችን ህጋዊነት የማረጋገጥ ስራ እንደሚሰራ ተገልፀዋል፡፡

በጉምሩክ የሚካሄዱ ዋና ዋና የቀረጥ እና የታክስ ማጭበርበር ወንጀሎች የተገኙ ሲሆን ፤ ከኮንትሮባንድ ቁጥጥር 2 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ፣ በክትትል ስራዎች 1.1 ቢሊዮን ብር የተገኘ ሲሆን ፣ ክፍተኛ ስጋት ያላቸውን በመለየት 17.6 ቢሊዮን ፣ ከጎብኚዎች ተሸከርካሪ ቁጥጥር ደግሞ 203.2 ሚሊዮን ብር ፣ በድንገተኛ ፍተሻ 211.3 ሚሊዮን ብር የተገኘ ሲሆን ፣ የውጭ ንግድ ማበረታቻ መብት ቁጥጥር 20.4 ሚሊዮን የተገኘ መሆኑ ተመላክቷል። በዚህም በህገ ወጥ መንገድ ማጭበርበር እና በኮንትሮባንድ መከላከል ሒደት 27.4 ቢሊዮን ብር ተገኝቷል ተብሏል፡፡

ከዛም በተጨማሪ በበጀት አመቱ ሪፖርት ላይ የተመላከተው ካለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር የኮንትሮባንድ ቁጥጥሩ ሲነፃፀር የ49 በመቶ ጭማሪ እንዳለውም ነው የተጠቀሰው ፡፡

በተያያዘም ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ ከእዳ ምህረት እስከ የተለያዩ ቁሳቁሶች ድጋፍ የሚሆን 39.8 ቢሊየን ብር በላይ የታክስ እዳ ምህረት ማድረጉን ተናግረዋል፡፡

ከዛም በተጨማሪ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በ2013 በጀት አመት 290 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ማቀዱን ያስታወቀ ሲሆን የኮሮና ቫይረስ በተከሰተበት 2012 በጀት አመት 233.7 ቢሊዮን ብር ገቢ የሰበሰበው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በ2013 በጀት አመት 290 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ማቀዱን አስታውቋል፡፡
ከዚህም ውስጥ 56.65 በመቶ ያክሉን ከአገረ ውስጥ ገቢ፣43.28 በመቶ ከውጭ ንግድ ቀረጥና ታክስ እንዲሁም 0.07 በመቶ ከሎቶሪ ሽያጭ ለመሰብስብ የተያዘ እቅድ መሆኑን በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡

በዚህም መሰረት በበጀት አመቱ የመጀመሪያ በሐምሌ ወር 19.5 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ 21.6ቢሊዮን ብር ወይም 110 በመቶ በመሰብሰብ ከእቅድ በላይ በማሳካት የበጀት አመቱን በስኬት መጀመሩን አስታውቋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ የገቢዎች እና ጉምሩክ ባለስልጣን የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሆኑት ኡሚ አባጀማል ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት ከሆኑ በቴክኖሎጂ ማሻሻያዎች በዋነኝነት ኢታክስን፣ (የአንድ መስኮት) ወይንም የኤሌክትሮኒክስ አገልግሎትን እና የጉምሩክ ስራ አመራርን (ECMS) ተግባራዊ በማድረግ ከመስከረም 2013 ጀምሮ የጉምሩክ አገልግሎትን ሙሉ በሙሉ በኤሌክትሮኒክስ ተግባራዊ የሚያደርጉ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

የአሰራር ስርዓቱን በማዘመን በተገልጋዮች ዘንድ ያለውን ከአገልግሎት ጋር የተያያዘ ቅሬታን በሚመለከት በቀጣዩ ለማስቀረት እና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን ግብር ከፋዩን ቁጥር በሚገባ ለማስተናገድ ዝግጅት ማድረግ መጀመሩንም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ለአዲስ ማለዳ በላከው መረጃ ተመላክቷል።

ቅጽ 2 ቁጥር 94 ነሐሴ 16 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here