የመንግስት የልማት ድርጅቶችን ዕቃ ግዥ በፌደራል የመንግስት ንብረት ግዥና ማስወገድ አገልግሎት ስር ለማካተት አዲስ ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መላኩን የኢፌደሪ መንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ አስታወቀ።
የፌደራል መንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ የመንግስት የልማት ድርጅቶችን ግዥ በፌደራል መንግስት ንብረት ግዥና ማስወገድ አገልግሎት ለማካተት በ2001 “የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት የግዥና የንብረት አስተዳደር አዋጅ” በሚል በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጠባቂነት የወጣውን የመንግስት የግዥና የንብረት አስተዳደር አዋጅ በማሻሻል የመንግስት የልማት ድርጅቶች ግዥ ለማካተት ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መላኩን የፌደራል መንገስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል።
በ2001 በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጸድቆ እስካሁን በስራ ላይ የቆየው አዋጅ የመንግስት ልማት ድርጅቶችን ግዥ ያካተተ ባለመሆኑ፣ የመንግስት ልማት ድርጅቶች በራሳቸው ግዥ ስርዓት ግዥ በሚፈጽሙበት ወቅት የሚፈጠረውን የመንግስት ሀብት ብክነት ለማስቀረት አዲስ በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ መካተቱን ኤጀንሲው አመላክቷል።
ኤጀንሲው ለአዲስ ማለዳ እንደገለጸው የአዋጁ መሻሻል ዋና አላማ የመንግሰት ልማት ድርጅቶች የመንግስት ግዥ እና የንብረት አስተዳደር ወጥ በሆነ መንገድ የሚመራበት ስልት ለመቀየስ፣ የኤሌክትሮኒክስ መንግስት ግዥ ስርዓትን በአዋጁ በማካተት ዘመናዊ የግዥና ንብረት አስተዳደር ስርዓት እንዲኖር ለማድርግ፣ የአገር ውስጥ ተወዳዳሪዎችን ተሳትፎ ለማበረታታት፣ አዋጁን የተሟላ የሚያደርጉ ተጨማሪ ድንጋጌዎችን ማካተት፣ በአፈጻጸም ሲያጋጥሙ የነበሩ እና ለመልካም አስተዳደር ችግር ምክንያት የሆኑ የአሰራር ጉድለቶችን ለማረም፣ በግዥ ሂደት ላይ የሚነሱ አቤቱታዎችን ማጣራት እና ውሳኔ መስጠት ሂደት ላይ ገለልተኛ እና ተዓማኒነት እንዲኖረው ለማስቻልና የአዋጁን አወቃቀር በማስተካከል ለአፈጻጸም ምቹ ለማድረግ መሆኑ ተጠቁሟል።
በረቂቅ አዋጁ ከተደረጉ ዋና ዋና ማሻያዎች ውስጥ አንደኛው የመንግስት የልማት ድርጅቶችን የተመለከተ ሲሆን፣ ከድርጅቶቹ ጋር በተያያዘ ከተካተቱ አሰራሮች ውስጥ የመንግስት የልማት ድርጅቶች በመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር አዋጅ ውስጥ እንዲካተቱና የተለየ ባሕሪያቸውን ለማስተናገድ እንዲቻል የተለየ የግዥ አፈፃፀም መመሪያ እንዲወጣላቸው ተደርጓል።
በዚህም የመንግስት የልማት ድርጅቶች ተጠሪ ተቋማት ተጠሪ የሆኑላቸው መስሪያ ቤቶች ግዥዎች ላይ እንዳይሳተፉ ተከልክሏል። በተጨማሪም የተረፈ መርቶችና የመጠቀሚያ ጊዜያቸው አጭር የሆኑ ንብረቶችን በማዕቀፍ ውል ስምምነት ማስወገድ እንዲቻል መደንገጉ ተጠቁሟል።
በሌላ በኩል የጨረታ ሰነድ ሽያጭ ማስቀረት ሲሆን፣ የጨረታ ሰነድ ሽያጭ በማስቀረት የመንግስት መስሪያ ቤቶች ለማንኛውም ጨረታ የሚያዘጋጀውን የጨረታ ሰነድ በየመስሪያ ቤታቸው እና በኤጀንሲዎች ድረ-ገፅ የመጫን ግዴታ እንዳለባቸው የሚደነግጉ ድንጋጌ በአዋጁ ተካቷል። ሌላኛው የአገር ውስጥ አምራቾችን ማበረታታት ሲሆን፣ የልዩ አስተያየት ተጠቃሚ ለመሆን ዓላማ የአገር ውስጥ ምርት ለመባል መሟላት የሚገባውን የ35 በመቶ በአገር ውስጥ የታከለ እሴት ምጣኔ ቅድመ ሁኔታ ዝቅ እንዲል ተደርጓል ተብሏል።
በተጨማሪም አዲስ የግዥ ዘዴ ስራ ላይ ማዋል ሲሆን፣ “ኤሌክትሮኒክ ልውጥ ጨረታ(Electronic Reverse Auction) የግዥ ዘዴ በአዋጅ ውስጥ ተካቷል። በመንገስት ግዥ አፈፃፀም እና ንብረት አወጋግድ ሂደት ለአካባቢ ጥበቃ ትኩረት መስጠት ሲሆን፣ በዚህም ማንኛውም የመንገስት ግዥ በሚፈጸምበትና ንብረት በሚወገድበት ወቅት የአካባቢ ብክልትን የሚስከትል መሆኑን በመንግስት መስሪያ ቤቶች የሚፈፀሙ ግዥዎችን አስመልክቶ የሚዘጋጁ የፍላጎት መግለጫዎች ከአካባቢያዊ ብክለትን የማያስከትሉ ግዥዎችን መፈጸም እንደሚገባቸው።
ከዚህ በፊት የመስሪያ ቤት ሰራተኛ የነበረ ሰው እስከ አንድ ዓመት ድረስ ይሰራበት የነበረ መስሪያ ቤት ግዥ ላይ ከአንድ ዓመት በላይ እንዳይሳተፍ የሚከለክል ድንጋጌ ተካቷል። እንዲሁም የውል አስተዳደርን በተመለከተ በየግዥው ዓይነት የውል አስተዳደር አጠቃላይ ገፅታ ምን መምሰል እንዳለበት የሚመላክቱ ድንጋጌዎች በአዋጂ ረቂቅ ላይ መካተታቸውነ ኤጀንሲው ገልጿል።
ቅጽ 2 ቁጥር 94 ነሐሴ 16 2012



