በ2011 ኃይል ያመነጫል የተባለው ፕሮጀክት ሥራ አልጀመረም

0
1005

በ2011 በጀት ዓመት ተጠናቆ ወደ ስራ ይገባል የተባለው የአይሻ ኹለት የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ስድስት ተርባይኖች ተከላ ተጠናቆ የሙከራ ኃይል ለማመንጨት እየተሰራ ቢሆን በአሁን ወቅት ወደ ሥራ አለመግባቱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ።

ፕሮጀክቱ በአጠቃላይ 48 ተርባይኖች ያሉት ሲሆን እያንዳንዳቸው 2 ነጥብ 5 ሜጋ ዋት የሚያመነጩ ሲሆኑ በአሁኑ ወቅት ስድስቱ ተርባይኖች በሙከራ ስርጭት ወይም ምን ዓይነት ችግር እንዳለባቸው በፍተሻ ስራ ላይ ይገኛሉ ሲሉ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ሞገስ መኮንን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

ፕሮጀክቱ በ2011 በጀት ዓመት መጨረሻ አካባቢ ይጠናቀቃል ተብሎ የነበረ ቢሆንም ፕሮጀክቱ እንዲዘገይ በውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ በኮቪድ 19 ምክንያት በተለያዩ አገራት ላይ እንቅስቃሴ የተገደቡ በመሆናው ለተርባይን ማመንጫ የሚሆኑ መሳሪያች ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ ማስተጓጓሉ፣ የቻይና ተቋራጮች በጥር ወር ላይ የአዲስ ዓመት በዓላቸውን ለማክር ወደ አገራቸው መሄዳቸው እንዲሁም አለመመለሳቸው፣ የቻይናው ተቋራጭ ድርጅት ዶንግፋንግ ኤሌክትሪክ ከአገር ውስጥ ተቋራጮች ጋር ተናቦ ያለመስራት፣በሚገነባበት ቦታ የከርሰ ምድር ውሃ ተቆፍሮ አለመገኘት የውሃ እጥረት እንዲገጥም ማድረጉ፣ አካባቢው ላይ ባሉ አርብቶ አደሮች ምክንያት የወሰን ማስከበር ጥያቄዎች ተጠቃሾቹ ምክንያት ናቸው ብለዋል ዳይሬክተሩ።

ፕሮጅክቱን ለማጠናቀቅም በ2013 የበጀት ዓመት ለመጨረስ እቅድ መያዙን እና የውሃ ችግሩን ለመቅርፍ ወደ ጅቡቲ የሚሄድ የውሃ መስመር በመኖሩ እና እሱን ለመጠቀም ጥረት መደረጉን እንዲሁም የአገር ውስጥ ተቋራጮች ተናቦ ለመስራት ችግሮች ተለይተው እየተሰራ እንደሆነም ሞገስ ገልጸዋል።

ሞገስ የወሰን ማስከበር ችግሮች በተለያዩ ጊዜ የሚያስቸግር በመሆኑ ችግሩን ለመቅረፍም ከሶማሌ ክልል ጋር በመነጋገር እየተፈታ እንደሆነም አስታውቀዋል፡፡
ሞገስ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት ከሆነም ፤ በአሁን ወቅት የአይሻ ኹለት የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት አጠቃላይ አፈፃፀሙ 64 ነጥብ 3 በመቶ መድረሱን የተገለጸ ሲሆን ፕሮጅክቱ ሲጠናቀቅም 120 ሜጋ ዋት ኃይል ያመነጫል ተብሎም እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።

የአይሻ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት በሱማሌ ክልል ሽንሌ ዞን አይሻ ደወሌ ወረዳ በመገንባት ላይ የሚገኝ ሲሆን ለፕሮጀክቱ 257 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዶላር እንደተመደበለት ተገልጿል።

ግንባታውን ለማከናወን 85 በመቶ የሚሆነው ወጪው በቻይናው ኤግዚም ባንክ እንደሚሸፈን የተነገረ ሲሆን ቀሪው 15 በመቶው ደግሞ በኢትዮጵያ መንግስት የሚሸፈን እንደሚሆንም ተነግሯል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በተጠናቀቀው የ2012 በጀት ዓመት 15ሺ192 ነጥብ 11 ጊጋ ዋት ሰዓት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት የቻለ ሲሆን በጽ/ቤቱ የኃይል ማመንጫዎች ኦፕሬሽን ቴክኒካል ድጋፍ እና አገልግሎት ዳይሬክተር ሰናይ ገብረጊዮርጊስ እንዳስታወቁት ከሆነም በበጀት ዓመቱ 16ሺ165 ነጥብ 48 ጊጋ ዋት ሰዓት የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት ዕቅድ ተይዞ 15ሺ192 ነጥብ 11 ጊጋ ዋት ሰዓት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ተችሏል ብለዋል።
አፈፃፀሙም የእቅዱ 94 በመቶ መሆኑን ከፅህፈት ቤቱ የተገኘ መረጃ ያመለከትታል።

በኢትዮጵያ በአሁኑ ሰዓት 21 የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች የሚገኙ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ ጣና በለስ፣ ግልገል ግቤ I፣ ግቤ II፣ መልካ ዋከና፣ ጢስ ዓባይ II፣ ቆቃ ፣ አዋሽ 2፣ አመርቲ ነሼ እና ረጲ የደረቅ ቆሻሻ ጣቢያ ከታቀደላቸዉ በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት መቻላቸው ተጠቁሟል።

እንደ ሰናይ ገለፃ በበጀት ዓመቱ የተጠበቀውን ያህል የኃይል ጥያቄ አለመቅረቡ እና የደንበኞች የሌሊት የኃይል አጠቃቀም ዝቅተኛ መሆኑ ለእቅዱ አለመሳካት ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል።

ቅጽ 2 ቁጥር 94 ነሐሴ 16 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here