በስድስት ወረዳዎች በተከሰተ የተፈጥሮ አደጋ ጉዳት ደረሰ

0
513

በሰሜን ሸዋ ዞን ስድስት ወረዳዎች ከክረምቱ ጋር ተያይዞ በተከሰተ የተፈጥሮ አደጋ በሰዎች ሕይወት እና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን የዞኑ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽሕፈት ቤት አስታቀ።

በተለይ ባለፉት ሁለት ቀናት ውስጥ ከፍተኛ የጎርፍ አደጋ፣ በረዶ፣ ከፍተኛ ነፋስ የቀላቀለ ዝናብ፣ የመሬት መንሸራተት እና ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ ነው የተከሰተው ሰሉ የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ ቻለው ምንዳ ለአብመድ ገልጸዋል።

አደጋው የተከሰተውም በእንሳሮ፣ በአንኮበር፣ በበረኸት፣ ሀገረ ማርያም፣ በጣርማበር እና በኤፍራታና ሌሎች ወረዳዎች በሚገኙ አካባቢዎች እንደሆነም ተጠቅሷል።
በእንሳሮ ወረዳ ከባድ ዝናብ መጣሉን ተከትሎ በተከሰተ ጎርፍ የአንድ ቤተሰብ አባላት የሆኑ ሦስት ሕፃናት ሕይወት ያለፈ ሲሆን በወረዳው በሚገኙ ሁለት ቀበሌዎች ከ 500 በላይ አባወራዎች በመኖሪያ ቤታቸው ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰም ታውቋል።

ሰብላቸው ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ መውደሙንም የገለጹት በአንኮበር ወረዳም ከፍተኛ ነፋስ የቀላቀለ ዝናብ መጣሉን ተከትሎ በመንግሥት ተቋማት፣ በሰብል፣ በመሠረተ ልማት እና በግለሰቦች መኖሪያ ቤት ላይ ከፍተኛ መጠን ያለው ጉዳት መድረሱን አረጋግጠዋል።

በበረኸት፣ ሀገረ ማርያም፣ ጣርማበር እና ኤፍራታና ግድም ወረዳዎች በአንዳንድ አካባቢዎቻቸው ላይ ተመሳሳይ ችግር እንደተፈጠረ የተገለጸ ሲሆን የአካባቢው ነዋሪዎችም ለከፍተኛ ችግር መጋለጣቸውን ቻለው ጠቅሰዋል።

ችግሩን ለመፍታት ኅብረተሰቡ ቅድመ ዝግጅት እንዲያደርግ ግንዛቤ እየተፈጠረ ቢሆን በችግሩ መጠን ምላሽ እየተሰጠው እንዳልሆነ አብመድ ተገንዝቤያለሁ ብሏል።
የጽህፈት ቤት ኃላፊውም የተሠራው ሥራ በቂ አለመሆኑን በማረጋገጥ በቀጣይ ግን የሰው ሕይወት እንዳይጠፋ እና በንብረት ላይ ተጨማሪ ጉዳት እንዳይደርስ ከማድረግ ጎን ለጎን ለጉዳቱ የሚመጥን አፋጣኝ እርዳታ እንደሚደረግ አስታውቀዋል።

ከነሐሴ 22/2012 ጀምሮ የዞን ግብረኃይል ችግሩ ወደ ተፈጠረባቸው ወረዳዎች በማቅናት ችግሩን እንደሚያጠና እና ጥናቱን ተከትሎም የምግብ፣ የመጠለያ፣ የአልባሳት እና ሌሎች አስፈላጊ ድጋፎች በአስቸኳይ እንደሚደደረጉም ገልጸዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 95 ነሐሴ 23 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here