በኦሮሚያ ክልል ከ12 ሺህ በላይ ሰዎች በጎርፍ ምክንያት ተፈናቀሉ

0
478

በኦሮሚያ ከሐምሌ ወር ጀምሮ ከ12 ሺህ በላይ ሰዎች በጎርፍ አደጋ ምክንያት ከአካባቢያቸው መፈናቀላቸውን የክልሉ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ገለጸ።
በክልሉ የበልግ ዝናብ መጣል ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ከ100 ሺህ በላይ ሰዎች በጎርፍ ምክንያት ለጉዳት መዳረጋቸውም የተገለጸ ሲሆን በተለያዩ ጊዜያት በተከሰቱ የጎርፍ አደጋዎች በሰው ህይወት ላይ ጉዳት እንዳይደርስ አፋጣኝ ምላሽ ሲሰጥ ቆይቷል ሲሉ የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር ገረመው ኦሊቃ ገልጸዋል።

“ለተጎጂዎች የምግብ እና የአልባሳት ድጋፍ ከማድረግ በተጨማሪ ጀልባ ጭምር በመጠቀም ሰዎችን ከውሃ ውስጥ የማውጣት ሥራዎች ተሰርቷል” ብለዋል።
በአዋሽ ወንዝ ዳርቻዎች አካባቢ ከ47 ኪሎ ሜትር በላይ የቦይ ማውጣትና የእርከን ሥራዎች ቢሰሩም በዚህ ዓመት የዘነበው ዝናብ ከፍተኛ በመሆኑ በህብረተሰቡ ላይ ጉዳት ማድረሱን ምክትል ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።

በአዋሽ ወንዝ ብቻ በ16 የክልሉ ወረዳዎች ባሉ 56 ቀበሌዎች በሚኖሩ ሰዎች ላይ ጉዳት ማድረሱን ነው የገለጹት።

በክልሉ ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ ለሆኑ አካባቢዎች ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በጎርፍ አደጋ ጉዳት እንዳይደርስባቸው የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥራዎች ተሰርተዋል ።
ገረመው እንደተናሩት ከሆነም “ጉዳት በደረሰባችው አካባቢዎች ህብረተሰቡ እርስ በርስ እንዲረዳዳና ከመንግስት የእህል ክምችት በማውጣት ለተጎጂዎች ድጋፍ ተደርጓል” ብለዋል ።
በኮሮናቫይረስ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች አንድ ላይ ማስቀመጥ ባለመቻሉ የተለያዩ አማራጮችን በመጠቀም እንዲጠለሉ ተደርጓል ተብሏል።
“በጎርፉ የጠፋውን ሰብል ለማካካስ የውሃ ሙላት መቀነስን ተከትሎ አርሶአደሩ ቶሎ የሚደርሱ ሰብሎችን እንዲያለማ ይደረጋል” ብለዋል።

በብሔራዊ ሚትዮሮሎጂ ኤጀንሲ ትንበያ መሰረት የክረምቱ ዝናብ እስከ መስከረም የሚዘልቅ መሆኑን የገለጹት ምክትል ኮሚሽነሩ፤ ህብረተሰቡ አሁንም ጥንቃቄ እንዲያደርግ ጥሪ ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ቅጽ 2 ቁጥር 95 ነሐሴ 23 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here