የፌደራል ስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ሀብታቸውን ለማስመዝገብ ፈቃደኛ ያልሆኑ 184 የፌደራል እና የአዲስ አበባ አበባ ከተማ አስተዳደር ባለሰልጣናትን ለጠቅላይ አቃቢ ህግና ለፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ጉዳያቸውን እንዲጣራና ክስ እንዲመሰረትባቸው አስተላለፈ፡፡
ኮሚሽኑ ከዚህ ቀደም ለአዲስ ማለዳ በሰጠው ጥቆማ ባለስልጣቱ በተደጋጋሚ ሀብታቸውን እንዲያስመዘግቡ ቢጠየቁም ፈቃደኛ ባለመሆናቸው በህጉ መሰረት ተጠያቂ ለማድረግ እየሰራ መሆኑንና ሀብታቸውን ያላስመዘገቡ ባለስልጣናት ለፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ሊተላለፉ መሆኑን አዲስ ማለዳ መዘገቧ የሚታወስ ሲሆን አሁን ላይ ኮሚሽኑ የተሰጠውን ኃላፊነት መወጣቱን ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል።
በመሆኑም የባለስልጣናቱን ጉዳይ በፌደራል ጠቅላይ አቃቢ ህግና በፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ስር የሚከናወን መሆኑም ተመላክቷል።አዲስ ማለዳ ከፌደራል ስነ ምግባር እና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ያገነችው መረጃ እንደሚያመለክተው ወደ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ እና ፌደራ ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ስማቸው የተላለፈው የስራ ኃላፊዎች በአሁኑ ሰዓት የመንግስት ስራ ኃላፊነት ላይ እንዳለሙ ታውቋል።
ባለስልጣናቱ ኮሚሽኑ ባስቀመጠው የሀብት ማስመዝገብ ጊዜ ገድብ ሀብታቸውን ባለማስመዝገባቸው ወደ ቀጣዩ የህግ አስራር መታላለፋቸውን ለአዲስ ማለዳ የጠቆሙትየፌደራል ስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን የሀብት ምዝገባና ማሳወቅ ዳይሬክተር መስፍን በላይነህ የግል ሀብትና የመንግስት ሀብት በግልጽ ተለይተው ከብክነት መጠበቅ አለባቸው ብለዋል።
ሀብትን ከማስመዝገብ ግዴታ ጋር ተያዞ ፈቃደኛ ሆኖ ያልተገኘ ሀብት የማስመዝገብ ግዴታ ያለበት አካል በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጠባቂነት ሙስናን እና ብልሹ አስራርን ለመከላከል በወጣው የሀብት ማሳወቅና ማስመዝገብ አዋጅ ቁጥር 668/2002 መሰረት በህግ ተጠያቂ እንደሚደርግ ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡
ኮሚሽኑ ባለስልጣናቱን በተደጋጋሚ ሀብታቸውን እንዳስመዘግቡ ያደረገው የልመና ጥሪ ጭምር ባለመቀበላቸው ኮሚሽኑ ህግን የማስከበር ግደታ ስላለበት ግደታውን ለመወጣት በሀብት ምዝገባ አዋጅ መሰረት ኃላፊነቱን እንደተወጣ የተጠቆመ ሲሆን፣ በአዋጁ መሰረት በህግ አግባብ ሀብታቸውን ያላስመዘገቡ አካላት ላይ በኹለት መንገድ ተገቢውን እርምጃ እንደሚወሰድ ኮሚሽኑ ለአዲስ ማለዳ መግለጹ የሚታወስ ነው።በአዋጁ ከተቀመጡ አስራሮች ውስጥ አንደኛው አስተዳደራዊ እርምጃ ሲሆን፣ ኹለተኛው ደግሞ ወንጀልን የሚስከትል እርምጃ መሆኑን የፌደራል ስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን የሀብት ምዝገባና ማሳወቅ ዳይሬክተር መስፍን በላይነህ ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ በአዋጁ መሰረት ሀብታቸውን ለማስመዝገብ ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተው የተሰጣቸው ጊዜ ገደብ በመጠናቀቁ አስፈላጊው እርምጃ ተወስዶ አንድ ሺህ(1000) ብር ተቀጥተው ሀብታቸውን እንዲያስመዘግቡ የሚደረግበት የህግ አግባብ መኖሩን አመላክተዋል። ኮሚሽኑ ሀብታቸውን ለማስመዝገብ ፈቃደኛ ያልሆኑ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትን ኃላፊነቱን ለመወጣት በተደጋጋሚ በደብዳቤ፣ በስልክ፣ በአጭር የጽሑፍ መልዕክት፣ በአካልና በሚቀርቧቸው የስራ ባልደረቦች ጭምር ቢጠየቁም ፈቃደኛ አይደሉም እንዳልነበሩ አስታውቋል።በኮሚሽኑ በኩል ከሚጠበቅበት በላይ እስከመለመን ድረስ ቢደርስም ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ማረጋገጡን ለአዲስ ማለዳ አረጋግጧል።ሀብታቸውን ለማስመዝገብ ፈቃደኛ ያልሆኑ ባለስልጣናት ከሚመሩት መስሪያ ቤትና ተቋም ጋር ምንም አይነት ግንኙነት የሌለው መሆኑንና የግለሰብ ጉዳይ መሆኑን ኮሚሽኑ አሳስቧል።በመሆኑም ጉዳያቸው የሚታየው በግለሰብ ደረጃ እንደሚሆን ተመላክቷል፡፡
ኮሚሽኑ ባለስልጣናቱ ሀብታቸውን እንዲያስመዘግቡ ያስቀመጠው ቀነ ገድብ ባለፈው ሀምሌ 30 ለሁለተኛ ጊዜ በማለፉ ምክንያት ተጠያቂ እንዲሆኑ ማድርጉን ገልጿል።አዲስ ማለዳ በተደጋጋሚ በስራቻቸው ዘገባዎች ጉዳዩን በጥብቅ በመከታተል ለአንባቢዎቿ ባደረሰቻቸው ዘገባዎች ላይ የሀብት ምዝገባ ጊዜ ገደብ የተራዘመው አሁንም ድረስ ፈቃደኛ ያልሆኑ ባለስልጣት ፍቃደኛ ሆነው ይቀርባሉ ተብሎ በመታሰቡ መሆኑ ይሚታወስ ነው፡፡
ቅጽ 2 ቁጥር 95 ነሐሴ 23 2012



