• በግንባታው የሚፈናቀሉ ነዋሪዎች የሉም
ባለፈው ሳምንት ይፋ የተደረገው የገርጂ የቤት ልማት ፕሮጀክት በሚቀጥለው ሳምንት እንደሚጀመር የመንግስት ቤቶች ኮርፖሬሽን ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ፡፡
ኮሮፖሬሽኑ ለአዲስ ማለዳ እንደገለፀው ከሆነ ቤቶቹ የሚገነቡት በቦሌ ክፍለ ከተማ ገርጂ ሮባ ዳቦ ቤት አካባቢ ሲሆን ለስራውም ተብሎ ተነሺ የህብረተሰብ ክፍሎች እንደማይኖሩ ጠቁሟል፡፡
የግንባታው ስፍራ በጠቅላላ 3 ሄክታር ላይ የሚያርፍ ሲሆን ለግምባታው የሚሆን የራሱ ቦታ እንዳለ በመጥቀስ አሁን ወደ ግንባታ ለመግባት ቅደመ ስራዎች ተጠናቀው መጪው ሳምንት ስራው እንደሚጀመር ኮርፖሬሽኑ ለአዲስ ማለዳ ተናግሯል፡፡
ከዛም በተጨማሪ ባለው በጀት አመት ለመገንባት በዕቅድ የተያዙ ስምንት የሚሆኑ ሳይቶች እንዳሉ የተጠቀሰ ሲሆን በአምስቱ ሳይቶች ላይ የግንባታ ስራው ተጀምሯል። በግንባታ ላይ የሚገኙት መኖሪያዎች የሚገኙበት አካባቢም ያሉት መካኒሳ ( ጀርመን አደባባየው ላይ)፣ ሃያ ሁለት ፣ቦሌ ፣ጦር ሃይሎች ፣ ቀበና አካባቢ ፣ በቅሎ ቤት እነዚህ አምስቱ በአንድ ተመሳሳይ ወቅት ዕቅድ ተይዞ እየሄዱ ያሉ ሲሆን ቀጥሎ ደግሞ ሶስት ፕሮጀክቶች የገርጂ ፕሮጀክትን ጨምሮ ሶስት መኖራቸውን ጠቅሰዋል፡፡
ቤቶቹን ለማጠናቀቅ ይፈጃል ተብሎ የተያዘላቸው ጊዜ እንደሚለያይ የገለፁት የመንግስት ቤቶች ኮርፖሬሽን የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው ክብሮም ገብረ ማርያም ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት እንደስፋታቸው እና እንደ ያዙት ቦታ ልክ ይወሰናል ብለዋል፡፡
እርሳቸው እደሚሉት እንዳንዱ ፕሮጀትክቶች ሃያ አራት ወራቶች የተሰጣቸው ያሉ ሲሆን፣ አንዳንዱ ደግሞ 20 ወራት ነው የተያዘላቸው ብለዋል፡፡
ኮርፖሬሽኑ ያለፉትን 44 ዓመታት በተለያዩ አደረጃጀቶችና ስያሜዎች አገልግሎት ሲሰጥ የቆየው የመንግሥት ቤቶች ኮርፖሬሽን ግንባታቸው በ2013 የሚጀመሩ 510 ዘመናዊ መኖሪያ ቤቶችን በሦስት ቢሊዮን ብር ለማስገንባት የኮንትራት ውል ነሐሴ 15 ቀን 2012 መፈራረሙ የሚታወስ ነው፡፡
በአጭር ጊዜ ይጠናቀቃል የተባለውን ዘመናዊ የሕንፃ ግንባታ (የገርጂ የመኖርያ ቤት ) ኮርፖሬሽኑ ውል የፈረመው ኦቪድ ኮንስትራክሽን (Ovid Constriction) ከሚባል አገር በቀል ተቋራጭ ጋር ሲሆን፣ ግንባታውም 18 ወራት እንደሚፈጅ ተገልፀዋል፡፡
በተያያዘም የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ረሻድ እንደገለጹት፣ ግንባታው ከፍተኛ ቴክኖሎጂን በመጠቀም በከፍተኛ ጥራት፣ በአጭር ጊዜና በተመጣጣኝ ዋጋ የሚገነባ መሆኑ ውሉን ከተፈራረሙ በኋላ ገልጸው ነበር፡፡
በአዲሱ ቴክኖሎጂ የሚገነቡት 510 ቤቶችን የያዙ 16 ባለ አሥር ፎቅ ሕንፃዎች ሲሆኑ፣ ተቋራጩ በ18 ወራት ውስጥ በማጠናቀቅ ለኮርፖሬሽኑ እንደሚያስረክብ ተናግረዋል፡፡ በሦስት ሔክታር ላይ የሚሠሩት ሕንፃዎች ባለ አምስት፣ ባለ አራትና ባለ ሦስት መኝታ ቤቶች ሲሆኑ፣ በአጠቃላይ ቤቶቹ ዘመናዊ የመኖሪያ መንደር ከመሆናቸው በተጨማሪ የዕለት ከዕለት ኑሮአቸው አስፈላጊ የሆኑ ቁሳቁሶችንና አገልግሎቶችን የሚያቀርቡ ተቋማትን አረንጓዴ ቦታዎችን፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎችንና መዝናኛ ቦታዎችን ያካተተ መሆኑን ተናግረው ነበር፡፡
የኮንትራቱን ፊርማ የፈጸሙት የኦቪድ ሕንፃ ግንባታ ተቋራጭ (Ovid Constriction) ኩባንያ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ዮናስ ታደሰ ስለ ኩባንያውና ግንባታው በወቅቱ እንደገለጹት፣ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማስተዋወቅ ቀዳሚ ኩባንያ መሆኑንና ተገጣጣሚ ግድግዳ (ማግኔዢየም ቦርድ) ሥራ በስፋት መሥራቱ በምሳሌነት እንደሚጠቀስ ተናግረዋል፡፡ ከቤቶች ኮርፖሬሽን ጋር ባደረጉት የኮንትራት ውል በኢትዮጵያ ተግባራዊ የሚያደርጉት አዲስ ቴክኖሎጂ አልሙኒየም ፎርምወርክ የሚባል ቴክኖሎጂ ሲሆን፣ የቤት እጥረትን ለመቅረፍ ተመራጭና ልዩ ቴክኖሎጂ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ቅጽ 2 ቁጥር 95 ነሐሴ 23 2012


