የፌደሬሽን ምክር ቤት የትግራይ ምርጫ ላይ አቅጣጫ ለማስቀመጥ እየሰራ ነው

0
1591

የፌደሬሽን ምክር ቤት ህገ ወጥ ነው ባለው የትግራይ ክልላዊ ምርጫ ላይ አቅጣጫ ለማስቀመጥ የህግ አሰራሮችን እየተመለከተ መሆኑ ተጠቆመ።
ምክር ቤቱ የትግራይ ክልል መንግስት ጳጉሜ 4/2012 ምርጫ ለማካሄድ ምርጫ ህገ ወጥ መሆኑን ጠቅሶ ምርጫ ለማድረግ የሚደርገውን እንቅስቃሴ እንዲያቆም በደብዳቤ ቢገልጽም ሊቀበል ባለመቻሉ ነው የፌደሬሽን ምክር ቤት የህግ አስራሮችን እንዲመለከት እንዳደረገው ታውቋል።

የፌደሬሽን ምክር ቤት ህገ ወጥ ነው ያለውን የትግራይ ክልል ምርጫ ጉዳይ በህገ መንግስቱ የተቀመጡ አሰራሮችን በመመርመር ምርጫውን ለማስቆም ወይም ከተደረገ በኋላ ሊወሰዱ ስለሚገቡ እርምቶችን ለመውሰድ የሚያስቸሉ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን የፌደሬሽን ምክር ቤት የህገ መንግስት ትርጉምና ማንነት ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ፀሀፊ ወርቁ አደም ለአዲስ ማለዳ ገልዋል።
ምርጫ ነፃ፣ ገለልተኛና ፍትሐዊ መሆን አለበት ያሉት ጸሀፊው ገለልተኛና ፍትሐዊ ምርጫ ለማድረግ ገለልተኛ የሆነ ምርጫ አስፈጻሚ አካል አስፈላጊ በመሆኑ የአገሪቱን ምርጫ የሚካሂደው ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ብቻ ነው ብለዋል።

ከዚህ አንጻር ትግራይ ክልል ምርጫ ህገ መንግስታዊ ካለመሆኑም በተጨማሪ ገለልተኛና ነፃ እንደማይሆን ጠቁመዋል።
በዚሁ መሰረት ምክር ቤቱ ለትግራይ ክልል ምክር ቤት የላከውን የምርጫ ይቁም ትዕዛዝ ክልሉ እስከመጨረሻው ካልተቀበለና ህገ መንግስቱን ካላከበረ በህገ መንግስቱና ሌሎች አዋጆች ላይ የተመሰረተ እርምጃ እንደሚወሰድ ተጠቁሟል።ምክር ቤቱ በአሁኑ ጊዜ በጉዳዩ ላይ አቅጣጫ ለማስቀመጥ ህገ መንግስቱን የማጥናት ስራ እየተሰራ መሆኑን የጠቆሙት የምክር ቤቱ የህገ መንግስት ትርጉምና ማንነት ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ፀሀፊ ወርቁ ጉዳዩ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ምክር ቤቱ ፍላጎት እንዳለው ገልጸዋል።

“የትግራይ ክልል አሁን ያለበት ሁኔታ ከመስመር የወጣ ነው።” ያሉት ፀሀፊው በትግራይ ክልልና በፌደራል መንግስት መካከል የተፈጠረውን ልዩነት በውይይት ለመፍታት አስቸጋሪ መሆኑን ጠቁመዋል።

የትግራይ ክልል መንግስት ምርጫ ለማካሄድ የመራጮች ምዝገባ ባሳለፍነው ሳምንት ማካሄዱ ይታወሳል።በዚሁ የምርጫ ምዝገባ ወቅት በትግራይና በአማራ ክልል አዋሳኝ ቦታ ላይ የሚገኙ የራያና የወልቃይት ኗሪዎች ምርጫ ላይ የግል መሳተፍ አለባችሁ ተብለው እስር፣ ድብደባና እንድልት እየደረሰብን ነው ሲሉ አቤቱታቸውን በማሰማት ላይ ይገኛሉ።ነገር ግን የትግራይ ክልል መንግስት በራያና በወልቃይት አካባቢ በዜጎች ላይ ያደርሳል የተባለውን በደል አላደረኩም ሲል አስተባብሏል።

ክልሉ ችግሩ አልተፈጠረም ብሎ ቢክድም በተጠቀሱት ቦታዎች አዋሳኝ ላይ የሚኖሩ ዜጎች በደል እየተፈጸመባቸው መሆኑን ቅሬታ ለማሰማት ለፌደሬሽን ምክር ቤት በአካል ተገኝተው ማቅረባቸውን ወርቁ ለአዲስ ማለዳ አረጋግጠዋል።

ምክር ቤቱም የዜጎቹን ቅሬታና ጥያቄ ተቀብሎ እየተወያያበት መሆኑን ወርቁ ጠቁመዋል።በቦታው ላይ የሆነውን ሁነት ተጨማሪ ማጣራት እንደሚጠይቅ የጠቆመት ወርቁ ምክር ቤቱ የዜጎችን ሰብዓዊ መብት ለማስከበር የሚወስደው እርምት እንደሚኖር አመላክተዋል።የዜጎችን መብት ከማስከበር ባሻገር ምክር ቤቱ ጥፋቱን ፈጽመው በተገኙ አካላትን ተጠያቂ ያደርጋልም ተብሏል።
በትግራ ክልል የፊታችን ጳግሜ 4/2012 የሚደረገው ምርጫ በምንም አግባብ ተቀባይነት የሌለውና እውቅና የማይሰጠው ከንቱ ምርጫ እንደሚሆን ወርቁ ተናግረዋል።

የትግራይ መንግስት በበኩሉ የትግራይን ምርጫ የማድረግና ራስን በራስ የማስተዳደር መብት የሚጋፋ ማንኛውም አካል ከመጣ የሕይወት መስዋትነት እንከፍላለን የሚል አቋም እንዳላቸው የህወሓት ስራ አስፈጻሙ አባል ጌታቸው ረዳ ባሳለፍነው ሳምነት ለአዲስ ማለዳ መናገራቸው ይታወሳል።

ቅጽ 2 ቁጥር 95 ነሐሴ 23 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here