ታሪክ ከፖለቲከኞች የግል መሣሪያነት ወደ ሕዝብ እጅ ሊገባ ይገባል!

0
587

ታሪክ የኋላውን ማስታወሻ፣ የዛሬን መወሰኛ እና የነገን ማቀጃ እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ። እንኳን በአገር ደረጃና በግለሰብም ቢሆን አንድ ሰው ትላንት ያሳለፈውና የቀደመ ልምዱ ለዛሬና ለነገ ግብዓት አድርጎ እንዲጠቀምበት፣ ከተሳሳተ እንዲማርበት፣ ጠንካራ ከነበረ ደግሞ በዛው እንዲገፋበት ይጠበቃል።

የኢትዮጵያን የታሪክ ነገር በወፍ በረር ስንቃኝ የሦስት ሺሕ ዘመን ታሪክ ያላት እንደሆነች መዛግብት ያስረዱናል። ከዚህ ታሪኳ ውስጥ የትኛው ተጻፈ፣ የትኛው ትኩረት ተሰጠው ወዘተ የሚለውን በሚመለከት የታሪክ አጥኚዎችንና ባለሞያዎችን ስንጠይቅ፣ ብዙውን የጦርነት ታሪክ እንደተጻፈ ያስረዳሉ። የሕዝብ ታሪክ አልተጻፈም የሚል ሙግት ከዚህ ጋር አያይዘው ያነሳሉ። ከዚህ ባሻገር ደግሞ ‹የለም! አልተጠናም አልተመራመርንም እንጂ የሕዝብ ታሪክም ተጽፏል› የሚል ትንታኔ የሚሰጡ አሉ።

በዛም አለ በዚህ ግን ይህ ክፍተት ለፖለቲከኞች ምቹ ቀዳዳ የሆነ ይመስላል። በተለይም መንግሥት በታሪክ ጉዳይ እጁን ጣልቃ እንዲያስገባ ፈቃድ ያገኘ እስኪመስል ድረስ ከ1983 ወዲህ፣ በታሪክ አንድም መግባባት ኖሮ የሚያውቅ አይመስልም። ሕወሓት መራሹ ኢሕአዴግ ወደ ሥልጣን በመጣ ማግስት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የነበሩና አሁንም ለዚህ ምስክር መሆን የሚችሉ ያሉ የታሪክ መምህራንን ጠርቶ ባነጋገረበት ወቅት ምሁራኑ፣ ‹የታሪኩን ነገር ለእኛ ተዉልን› ቢሉም፣ በጊዜው መንግሥት ያቋቋመው ፓርቲ ያንን አላደረገም።

ከዛ ጊዜ ጀምሮ ታሪክ የመለያያና የመከፋፈያ ምክንያት ሆኖ ማገልገል ጀምሯል። በተለይም ከመቶ ዓመት በፊት ጀምሮ ወዲህ እስከ ኃይለሥላሴ ዘመን መንግሥት፣ እንዲሁም ደርግን ተሻግሮ ከኢሕአዴግ መምጣት ጀምሮ ያሉ ኹነቶች አጨቃጫቂ ሆነው ቀጥለዋል። በዚህ መካከል ያለው ትውልድም ታሪክን ተምሯል ለማለት አስቸጋሪ ነው።

መታዘብ እንደምንችለው የትኛውም የታሪክ ባለሞያ ምንም ያህል ገለልተኛ ሆኖ የአንድን ታሪክ ልጻፍ ቢል ገና ከመጽሐፉ ርዕስ በመነሳት ብቻ፣ አስቀድሞ ለጸሐፊው በሚሰጥ ታርጋ መሠረት ‹የእገሌ ብሔር ነው› የሚል ድምዳሜ ይሰጣል። ይህንንም ተከትሎ እየተያያዙ የመጡ ሐሰተኛ ትርክቶች እየቆዩ ሲሄዱ እውነት የሆኑ ያህል ተቀባይነት አግኝተው ሐሰተኛውን ከእውነት ለመለየት የሚያዳግት ደረጃ ላይ ተደርሷል። ለእነዚህ ትርክቶችም ሕይወቱን እስከመስጠት፣ የሰውን ሕይወትም እስከመንጠቅ የሚደርሱ ጥቂቶች እንዳልሆኑ አይተናል፡፡

አዲስ ማለዳ የታሪክ ምሁራን ታሪክን ከፖለቲከኞች እጅ መንጠቅ አለባቸው ብላ ታምናለች። ይህ ካልሆነ ቀጣዩም በተመሳሳይ ስለአሁኑ ጊዜ የሚያገኘው ታሪክ የተጣመመ ሊሆን ይችላል። ከዛም የሚከፋው ደግሞ ለታሪክ ያለው አረዳድ ነው። ትርክቶች ሐሰተኛም ይሁኑ እውነተኛ፣ ለዛሬ በምን መንገድ እንጠቀማቸው የሚለው ላይ ጤናማ ዕይታና አስተሳሰብ ያለ አይመስልም። ጣልያን በኢትዮጵያ ላይ ያደረሰችውን ግፍና በደል ሁሉም የሚስማማበትና የሚቀበለው ሆኖ፣ አሁን ከጣልያን ጋር በብዙ መንገድ በዲፕሎማሲ የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ። በአንጻሩ ግን በኢትዮጵያ ተከስቶም ይሁን ሳይከሰት፣ ግን ሆኗል በተባለ አንዳች ክስተት ውስጥ ለዛሬ በቀልን የሚጠማና ‹የእገሌ ወገን› ብሎ የሚጠላው፣ ‹የእኔ ወገን› ብሎ ታሪክን መሠረት አድርጎ የሚገፋው እንዲኖር አድርጓል።

ይህ መሠረታዊና ለታሪክ ካለ አረዳድ የመጣ ስህተት ነው። ታሪክ መማሪያ እንጂ መበቃቀያ ሊሆን ስለማይገባው።

በዚህ መሠረት የቀደመው ትውልድ ዳግም ተፈጥሮ የሆነውን ቢተርክልን ወይም በአንዳች መንገድ ነገሩን ሁሉ መለስ ብለን የምናይበት መነጽር ብናገኝ እንኳን፣ ለታሪክ ያለን አረዳድ እስካልተስተካከለ ድረስ፣ የምንሰማው ታሪክ ሐሰተኛም ይሁን እውነተኛ ዋጋ ላይኖረው ይችላል። ‹ትክክል› ባልሆነ አእምሮ ትክክለኛ ሐሳብ ቦታ ሊኖረው አይችልም። እናም ታሪክን ከማስተማር ጎን ለጎን የማስተማሩ ጥቅም ምንድን ነው የሚለውን መረዳት ከፍተኛ ቦታ ሊሰጠው ይገባል፡፡

በዚህ ረገድ ለሦስት ዐስርተ ዓመታት ሁሉም ተማሪዎች በሰፊው እንዲያውቁት ሳይደረግ የቆየውን የታሪክ ትምህርት በሁሉም የትምህርት ደረጃዎች እንዲሰጥ እየተደረገ ያለው ዝግጅት ተገቢ ነው፡፡ በትምህርቱ አሰጣጥም ጉልህ ቦታ መያዝ ያለበት መቼ፣ ማን፣ ምን እንዳደረገ ሳይሆን ለምን እንዳደረገ፣ ለምን ሕዝብ እንደደገፈው ወይም እንደተቃወመው፣ በዘመኑ የነበረው አስተሳሰብ ምን ይመስል እንደነበር በማሳየት ካለፉት ተግባራት ነባራዊ ትምህርት ለመውሰው ሊሆን ይገባዋል፡፡

ትላንትን እያሉ፣ ስላለፈው እየተነታረኩ ዛሬንና ወጣትነታቸውን እየተነጠቁ ያሉ ወጣቶች ጥቂት አይደሉም። ነገርን ሁሉ ከብሔርና ከወገንተኝነት አንጻር አይቶ አንድነትን አሃዳዊነት ብቻ፣ ብሔርን መጥራትን መከፋፈል ብቻ አድርገው የሚያስቡም ትክክል አይደሉም።

ምንም ያህል በፖለቲካ አመለካከቶች መሠረት የአንድ ታሪካዊ ሒደት ትርጓሜ ብዙ ቢሆንም መሬት ላይ ያሉ ሊረጋገጡ የሚችሉት ዕውነታዎች ግን ከታሪክ ምሁራን የሚደበቁ አይደሉም፡፡ በመሆኑም ታሪክ ከተተበተበበት የፖለቲካ ድር እንዲላቀቅ በማድረግ የታሪክ ምሁራን የሚሉት በቀዳሚነት ቦታ ሊሰጠው ይገባል፡፡ በበቂ ሁኔታ ጥናት ስላልተደረገባቸው እና የሕዝብ ታሪክ ስለሆኑ ቸል ተብለዋል በሚባሉ ጉዳዮች ላይም እኒሁ ምሁራን ጥናት አድርገው ሀቁን ለሕዝብ ሊያሳውቁ ይገባል፡፡ ከዚያ ባለፈ ፖለቲከኞች የሕዝብ ተቆርቋሪ ለመምሰል ወይም ደግሞ ለሌላ ድብቅ አጀንዳ ደስ ባሰኛቸው መንገድ ታሪክን ማዛባታቸው፤ እርሱንም ተከትሎ በሕዝቦች መካከል መራራቅ መፈጠሩ፤ አለፍ ሲልም ሕይወት መጠፋፋቱ ሊበቃ እንደሚገባ አዲሰ ማለዳ ታምናለች፡፡

የታሪክ ትምህርት ዜጎች የጋራ ማንነት ለመገንባት ከፍተኛ ሚና ይጫወታል፡፡ በአገር ውስጥ ያሉ የተለያዩ ማህበረሰቦችን እሴቶች፣ ባህሎች፣ ቋንቋዎች እንዲሁም ታሪኮች የዛ ማህበረሰብ አባል ላልሆኑ ዜጎች በማሳወቅ ታሪክ ዜጎች በአገራቸው ጥላ ስር የጋራ ማንነት እንዲኖራቸው የታሪክ ትምህርት ያግዛል፡፡ ይህም ልዩነቶች ላይ ያተኮሩ፣ ̀የራስ̕ የሚሉትን ወገን ተበዳይ ብቻ፣ ̀ሌላ̕ የሚሉትን ወገን ደግሞ በዳይ ብቻ አድርገው ከሚያቀርቡ ትርክቶች ሕዝብን በመጠበቅ ሀቁን ራሱ አገናዝቦ እንዲያይ እድል ይከፍታል፡፡ በተቃራኒው ደግሞ የታሪክ ትምህርት ለሰፊው ሕዝብ ተደራሽ እንዳይሆን መደረጉ በፖለቲከኞች በዋናነት እንዲያዝ እና ላነገቡት ዓላማ ማስፈፀሚያ የሚጠቅማቸውን ከቱባው ታሪክ ላይ በመምዘዝ ሲፈልጉ አጣምመው፣ ሲፈልጉ ደግሞ አጋነው በማቅረብ ሕዝብን ለማነሳሳት እና ከጎናቸው ለማሰለፍ እንዲጠቀሙበት አድርጓል፤ ሁኔታው ካልተቀየረ ለወደፊትም ያደርጋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የታሪክ ትምህርት ሥልጣን ላይ ያሉ ሰዎች በማናለብኝነት ሕዝብን መበደላቸውን፣ ሰዎችም ሌላው ሲበደል ዳር ቆመው በማየታቸው ሁኔታው እየባሰ ሔዶ እነርሱ ጋር ሲደርስ የሚረዳቸው ማጣታቸውን፣ ተራ ሰዎች ጠንክረው አብረው ሲቆሙ ሊያመጡ የቻሉትን ትልቅ ለውጥ፣ የዘንድሮው ማህበረሰብ ቀደምት ማህበረሰቦች ያጋጠማቸውን ተመሳሳይ ችግር እንዴት እንደተወጡት፣ በሒደቱስ ምን እንደተሳሳቱ እና ሌሎችንም ነገሮች በማሳየት ሰዎች ጥሩ ዜጋ እንዲሆኑ መሠረት ይጥላል፡፡

ከላይ የተጠቀሱት የታሪክ ትምህርት ጥቅሞችን ግምት ውስጥ በማስገባት እና ታሪክን ከፖለቲከኞች መዳፍ ፈልቅቆ በማውጣት በባለሙያተኞቹ እጅ በማድረግ ቀጣይ የአገሪቱን እጣ ፈንታ መታደግ እንደሚቻል አዲስ ማለዳ ታምናለች፡፡ የኢትዮጵያዊነት የአገር ፍቅር ስሜት ከእለት እለት እየተሸረሸረ መገነጣጠሏን የሚመኙ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ለመለፈፍ የሞራል ብቃት ሲኖራቸው አንድ ሆና መቀጠሏን የሚሹ ደግሞ የሚሳቀቁበት ጊዜ ከተፈጠረ ቆየ። በመሆኑም ሁሉንም አካታች በሆነ እና በመረጃዎች በተደገፈ መንገድ ታሪክን ለሰፊው ሕዝብ በመደበኛም ሆነ በኢ-መደበኛ መንገድ ማድረስ ለሥልጣን፣ ለዝና እና ለገንዘብ የማይፈነቅሉት ድንጋይ የሌላቸውን ፖለቲከኞች አስታግሶ ሕዝብን ከእርስ በእርስ ጥላቻ ወደ መግባባት ሊያመጣ ይችላል፡፡

ቅጽ 2 ቁጥር 95 ነሐሴ 23 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here