ከሰሞኑ አንድ ድንገተኛ የመንግስት ውሳኔ ተሰምቶ በርካታ ሩጫዎች የተስተዋሉባቸውን ጉዳዮች መመልከት እና ተቀዛቅዞ ነበረው ወይም ተዳፍኖ ነበረው የሕገ ወጥ ገንዘቦች ዝውውርም በይፋ በቁጥጥር ስር ሲውል ሰንብቷል። በቅርቡ ገንዘብ ቅየራው ጉድ ታዲያ በኢትዮያ በባንክ ስርዓት ውስጥ ከሚንቀሳቀሰው ይልቅ በኢመደበኛው የንግድ ስርዓት ውስጥ የሚገኘው ገንዘብ እጅጉን ይበዛል እና የገንዘብ ቅየራው ተግባራዊ ለመደረጉ ጠቅላይ ሚንስትሩ አረጋግጠው ነበር።
በተለይም ደግሞ አገሪቱ ካለችበት የምጣኔ ሀብት ስብራት ለመታደግ እና ፍትሃዊ ያልሆነው የሀብት ክምችት ከዚህ በኋላ ዕድሜው እንዳይረዝም እና እስካሁን የተሔደበትም መንገድ እጅግ አሰልቺ እና አጥፊነቱ በዚሁ ሊገታ እንደሚገባም የታመነበት እንቅስቃሴ እንደሆነ ለማየት ተችሏል። በጆንያ እና በፌስታል ገንዘብ እየተቀባበሉ ኢመደበኛ ንግዱን አጧጡፈውታል የሚባልላቸውን ግለሰቦች ኪስ ከማድረቅ አኳያም ጉዳዩ እጅግ ጠቀሜታው የጎላ እንደሚሆንም ከብሔራዊ ባንክ ገዢው እስከ ጠቅላይ ሚንስትሩ ድረስ ከፍተኛ ተስፋን ሰንቀው ይፋ ያደረጉት የብር ቅየራ በመላው አገሪቱ ተግባራዊ ሆኖ እስኪያልቅ ሦስት ወራትን እድሜ ተለግሶታል።
በዚህ ወቅት ታዲያ ከ100 ሽህ ብር በላይ በዕጃቸው ይዘው የሚገኙ ግለሰቦች ታዲያ መንግስት በመጀመሪያው አንድ ወር ሙሉ ቀይረው እንዲጨርሱ እና ይህ ባልሆነበት ሁኔታ ግን መንግስት በሚወስደው ዕርምጃ ቅር ሊሰኙ እንደማይገባ በይፋ ተናገረበት አጋጣሚ ነበር። 113 ቢሊዮን ብር ይንቀሳቀሳል ሚባልባት አገር እና መንግስትም ይህን ጉዳይ ለመፍታት ገንዘብ ቀየረባት ኢትዮያችን ቀሪውን ሦስት ወራት ጊዜ የሩጫ ይሆናል ብለው እንደሚያምኑ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
በሙስና እና በስርቆት ላይ የሚገኙ ግለሰቦች እና መንግስት መዋቅር ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን በጆንያ እና በፌስታል ገንዘብ እየተቀባበሉ ግብይት የሚፈጽሙትን ሰዎች ጉዳይ ለመቆጣጠር እና እንደ ጠቅላይ መሚንስትሩ አባባል ‹‹ሌቦች ኢንቨስት ስለማያደርጉ›› ገንዘብ በሕገ ወጥ መንገድ ስለሚዘዋወር ይህን ሁሉ ለመቆጣጠር እና ኢትዮያ ካጋጠማት የኢኮኖሚ ስብራት የምታገገምበትን ጉዳይ እንዲፋጠን በምስጢር የተያዘው ብር ቅየራው ጉዳይ መፋጠኑን ተናግረዋል። ‹‹ኮቪድ ባያዘገየን ኖሮ እና ሕትመት ስራው ባይጓተት ኖሮ ከዚህ ቀደም ብለን መቀየር እንችል ነበር›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የምስጢር ገንዘብ የመቀየር ሒደቱ ከኮቪድ በፊት ማለትም ከመንፈቅ እድሜ በላይ ምናልባትም ወደ አንድ ዓመት የሚጠጋ ጊዜ መውሰዱን አመላካች ነው። የብር ለውጡን ለማድረግ ዋናው ምክንያት ከሁለት ዓመታት ወዲህ በአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ለመለወጥ እየተሞከረ ያለውን የኢኮኖሚ ስብራት መጠገን እንደሆነ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ከለውጡ በኋላ በተደረገ ዳሰሳ ኢኮኖሚው ከፍተኛ የሆነ የማክሮ ኢኮኖሚ ማዛባት እንዳለበት በመረጋገጡ ቁልቁል ሲሄድ የነበረውን ኢኮኖሚ ማስቆም ዋናው ዓላማ ነው ብለዋል።
ይኸው ከፍተኛ ገንዘብ ማለትም በሰኔ ወር 2012 በብሔራዊ ባንክ እንደተገለጸው 113 ቢሊዮን ብር ከባንክ ስርዓት ውጪ የሚዘዋወር ሲሆን ይህም ከአመት በፊት ከነበረው የ92 ቢሊዮን ብር ከባንክ ውጪ ይዘዋወር እንደነበር ታውቋል። ይህ ከባንክ ስርዓት ውጪ በመዘዋወር በኢመደበኛው ንግድ ሒደትን በከፍተኛ ሁኔታ ሲደጉም ነበረው ገንዘብ እና በፍጥነት እያደገ የመጣበትም ጉዳይ ካለው ከፍተኛ የሆነ የብድር ፍላጎት አንጻር እንደሆነ መረጃዎች ያመላክታሉ።
በ2007 እና 2008 ላይ 66 ቢሊዮን የነበረው ከባንክ ስርዓት ውጪ ይዘዋወር የነበረው ገንዘብ በቀጣዩ አኣመት በ10 በመቶ ዕድገት በማሳየት ከፍ ብሎ ነበር። ነገር ግን ከፍተኛ የሆነ ገንዘብ ከባንክ ውጪ ወጣው እንደ ብሔራዊ ባንክ ገለጻ አገሪቱ ከፍተኛ የሆነ አለመረጋጋት እና ውጣ ውረዶች በነበሩበት የ2008 እና 2009 ላይ እንደነበር ታውቋል። እነዚህን እና መሰል ጌዜያቶችን በመጠቀም ከባንክ ስርዓት ውጪ ሲንቀሳቀሱ ነበሩት ገንዘቦች ሔደው ሔደው 113 ቢሊዮን ብር ደርሰዋል።
ከሰሞኑ ታዲ ይፋ በተደረጉ የገንዘብ ኖቶች ባንክ የማያውቃቸው እና ሕገ ወጥ ዝውውሮች እና ግብይቶችን የሚያጠናክሩ ገንዘቦች የአገልግሎት ዘመናቸው የተጠናቀቀ ይመስላል። ለሦስት ወራት መቀሪያ ጊዜ የተሰጣቸው ገንዘብ በእጃቸው ሚገኝ ግለሰቦች የሚከተሏቸውን ቅደም ተከተሎችንም ይፋ ተደርጓል። ከ 10 ሽህ ብር በላይ ይዞ ወደ ባንክ በመሔድ ለመቀየር የፈለገ ግለሰብ የባንክ አካውንት እንዲኖረው እንደሚያስፈልግ እና መክፈትም እንደሚኖርበት ይደነግጋል። በዚህ ሒደት የሌላ ሰው ገንዘብ መመንዘር እንደማይቻል እና ገንዘቡን ይዞት መጣው ግለሰብ ገንዘቡን በስሙ በተከፈተ አካውንት ውስጥ ማስገባት እንደሚኖርበት በሚገባ ተነግሯል።
የብር ኖቶቹን መቀየር አስፈላጊነት አክለው ያስረዱት የብሔራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ኖቶቹን መቀየር ያስፈለገባቸው በርካታ ምክንያቶች እንዳሉት ተናግረዋል። የመጀመርያው ምክንያት በርካታ ገንዘብ ከባንክ ውጪ በመኖሩ ሕገወጥ ተግባራት፣ ሙስናና ኮንትሮባንድ ስለተስፋፉ ያንን ለመከላከል ነው ብለዋል። ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ ባንኩና ውጪ ያለ ገንዘብ ሲበራከት የጥሬ ገንዘብ እጥረት ስለሚያጋጥማቸው ያንን ለመከላከል ታስቦ እንደሆነ አስረድተዋል።
ባለ 10፣ 50፣ 100 እና አዲስ ደግሞ ባለ 200 ብር ኖትን ያካተተው አዲሱ የብር ኖት አገሪቱ ለ23 ዓመታት ከ1990 ጀምሮ የተጠቀመችባቸው ገንዘቦች እንደተቀየሩ ታውቋል። የብሔራዊ ባንክ ገዢው ይናገር ደሴ እንደሚሉት በ1996 አካባቢ የተወሰነ ማሻሻያ የተደረገበት የተወሰኑ የብር ኖቶች መኖራቸውን አውስተው ነገር ግን በዚህ ወቅት የተደረገው የብር ቅራ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ተደረገ እንደሆነ እና ከፍተኛ ወጪ የወጣበት እንደሆነ ይፋ አድርገዋል።
የሆነው ሆኖ ግን የብር ቅየራው ይፋ በተደረገበት ወቅት ጠቅላይ ሚንስትሩ በሕገ ወጥ መንገድ ገንዘብ በሚዘዋወርበት ወቅት በቁጥጥር ስር ያዋለው የጸጥታ አካል ራሱ ገንዘቦችን እንዲወርሳቸው እና ለተቋሙ ማጠናከሪያ እንዲሆን ወስነዋል። ይህ ጉዳይ ግን ታዲያ ሰፊ ክትትል የሚያሻው እና ኃላፊነቶች ሊመዘኑ እንደሚገባም አዲስ ማለዳ በአጽንኦት ትገነዘባለች። የብር ቅየራው ይፋ ከተደረገበት ካለፉት ጥቂት ቀናት ጀምሮ በድንበር አካባቢዎች በርካታ የብር ኖቶች መያዛቸው እና ሕገ ወጥ ዝውውሩም መጠናከሩን ማሳያ እንደሆኑ ቢገለጽም ቅሉ ኃላፊነት የተሰጣቸው የጸጥታ አካላት ሰውነታቸውን መርሳት እንደሌለብን እና ብልሹ አሰራሮችን በመከተል ገንዘቦችን ከሕጋዊው ሕዝብ ሊነጥቁ የሚፈልጉ መኖራቸውን በመገንዘብ መንግስት ልዩ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አዲስ ማለዳ ታስገነዝባለች።
እየሆነ ያለውን የኃላፊነት ደረጃ ጋዜጣዋ ብትገነዘብም ከዚህ ቀደም ወደ መንግስት ካዝና በሚገባበት ወቅት የነበረው መዘናጋት አሁንም እንዳይቀጥል የታሰበ ቢሆንም ነገር ግን በትክክለኛው እና የአገርን ገንዘብ ከማዳን እና ሕገ ወጥነትን ከማክሸፍ አንጻር የሚሰሩ ስራዎች መልካቸው ሕግን ማስከበር ብቻ እንዲሆን አዲስ ማለዳ ሃሳቧን ታስተጋባለች። ጠቅላይ ሚንስትሩ እንዳሉት ዋናው ጉዳይ ሕገ ወጥነትን ማጥፋት ቢሆንም እና ይህንንም ደግሞ አዲስ ማለዳ የምትደግፍ ሲሆን ነገር ግን በሕጋዊነት እየተንቀሳቀሱ ለፍተው ጥረው ግረው ያገኙት ገንዘብ ደግሞ የአገር እና ሕዝብ ኃላፊነትን በተሸከሙ ጸጥታ አካላት እንዳይዘረፉ ከወዲሁ ቁጥጥር የሚያደርግ አካል ሊኖር እንደሚገባ አዲስ ማለዳ ታስገነዝባለች። ምክንያቱ ደግሞ በመንግስት እና በሕዝብ መካከል የሚኖረው መተማመን እንዳይናድ እና ኃላፊነቶች ያለ ሕዝብ ተሳትፎ ግብ እንደማይመታ የሚታወቅ ሲሆን በዚህች አጭር ቀናት ውስጥ የሚፈጠረውን ጉዳይ በትኩረት ሊታይ እንደሚገባው አዲስ ማለዳ ታሳስባለች።
ቅጽ 2 ቁጥር 98 መስከረም 9 2013


