በመተከል 13 የአንድ ቤተሰብ አባላት የደረሱበት አልታወቀም

0
750

‹‹አርባ ሰዎችን በየተራ ገድለዋቸዋል›› በሕይወት የተረፈ

በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል መተከል ዞን በቡለን ወረዳ ኤጳር ቀበሌ ከጳጉሜ አንድ አስከ ጳግሜ 3/2012 በታጠቁ ኃይሎች በደረሰው ጥቃት ሰለባ የሆኑ 13 የአንድ ቤተሰብ አባላት እስካሁን የደረሱበት አንዳልታወቀ ተጠቆመ።

አዲስ ማለዳ ከወረዳው መንግስት ኮምኒኬሽን ኃላፊ ካሳሁን አዲሱ ያገኘችው መረጃ እንደሚያመለከትው የአንድ ቤተሰብ አባል የሆኑት 13 ሰዎች አስካሁን የት አንደደረሱ እንዳልታወቀ የአካባቢው ኗሪዎች እና ዘመዶቻቸው ቢገልጹም አንድ ቤተሰብ አባል ሥለመሆናቸውና ሥለ አለመሆናቸው የተጣራ ነገር የለም ነገር ግን አንድ ቤተሰብ አባል አልተጎዳም ማለት አይቻልም ሲሉ ተናግረዋል።

ጳጉሜ 1/2012ከሌሊቱ 8፡00 ሠዓት ገደማ በቡለን ወረዳ ኤጳር ቀበሌ የታጠቁ ሀይሎች ገብተው ባደረሡት ጥቃት የንጹኃን ዜጎች ሕይወት ማለፉን የቡለን ወረዳ መንግስት ኮሙኒኬሽን ሀላፊ ካሳሁን አዲሱ ለአዲስ ማለዳ ገልጽዋል። እንደ ሀላፊው ገለጻ በአካባቢው መከላከያ ሰራዊት ከገባ ወዲህ ከ30 በላይ ሰዎች ሬሳ ከጫካ ተነስቶ እንደተቀበረ ነው የተናገሩት። ነገር ግን እስካሁን የተጎጂዎችንና የሟቾችን ቁጥር ማወቅ እንዳልተቻለ ካሳሁን ጠቁመዋል።

ኤጳር ቀበሌ ማዕከልን ጨምሮ በዞኑ የጸጥታ ችግር በተፈጠረባቸው አካባቢዎች የመከላከያ ሠራዊት፣ የፌዴራል ፖሊስና የክልሉ የጸጥታ ኃይል ችግሩ በተፈጠረ ማግስት ወደ ቦታው መድረሳቸውን የገለጹት ኃላፊው፣ ጸጥታውን የማረጋጋትና የሕግ የበላይነት የማስከበር ሥራ እየሠሩ መሆኑን አስታውቀዋል።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን በተደጋጋሚ የፀጥታ ችግር ሲፈጠር ቢቆይም መንግስት ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ በቂ የጸጥታ ሀይል ባለማሰማራቱ ህብረተሰቡ በተደጋጋሚ ለጥቃት እየተዳረገ መሆኑን ለደህንነቴ ሲባል ስሜ እንዳይጠቀስ ያሉ በቡለን ወረዳ በመንግስት መስሪያ ቤት ውስጥ የሚሰሩ ግለሰብ ጠቁመዋል። እንደ አዲስ ማለዳ ምንጮች ጥቆማ በአካባቢው ጳጉሜ አንድ 2012 ምሽት ታጣቂዎች በሦስት ቀበሌዎች ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን ገልጸዋል። ታጣቂዎቹ ከቡለን ወረዳ በተጨማሪ በጉባ ፣ ዳንጉር እና ወምበራ ወረዳዎች ላይ ተመሳሳይ ጥቃት መፈጸማቸውን ኗሪዎች አረጋግጠዋል።

ኗሪዎቹ አንደሚሉት የታጠቁ ኃይሎች የአካባቢውን ሰው አግተው ወደ አንድ ቦታ በማከማቸት ለሦስት ቀን ያከል እንዳሻቸው ሲገድሉና ሲያንገላቱ አንደነበር ጠቁመዋል። በወቅቱ በአካባቢው የነበረው የፖሊስ አባል ታጣቂዎቹን መከላከል የሚያስችል አቅም ስላልነበረው ምንም የተደረገ ነገር አንዳልነበር ኗሪዎቹ አስታውሰዋል። ተጨማሪ የጸጥታ ኃይል ወደ አካባቢው የገባው ጳጉሜ አራት 2012 መሆኑን ኗሪዎቹ ተናግረዋል።

አዲስ ማለዳ ካነጋገረቻቸው የቡለን ወረዳ ኗሪዎች ውስጥ ስማቸው አንዳይጠቀስ የጠየቁ ከፍተኛ የመንግሰት ሰራተኛ ይገኙበታል። ግለሰቡ አንደገለጹት ከሆነ መከላከያ ጳጉሜ አራት 2012 አንደገባ ጠቁመው ጥቃት ፈፃሚው የታጠቀ ቡድን ከመከላከያ ኃይል ጋር በከፈተው የተኩስ ልውውጥ ኹለት የመከላከያ አባላት አንደሞቱ ለአዲሰ ማለዳ ተናግረዋል። አንዲሁም ስምንት አባላት ቆስለው ህክምና እየተደረገላቸው መሆናቸውን አክለው ጠቁመዋል። የአዲሰ ማለዳ ምንጭ አንደሚሉት ችግሩ የተከሰተው ችግሩ ከመከሰቱ በፊት ስጋት መኖሩን መንግስት እያወቀ ተጨማሪ የጸጥታ ኃይል ማሰማራት ባለመቻሉ ነው ብለው አንደሚያምኑ ገልጸዋል።

የወረዳው ኮሙኒኬሽን ኃላፊ በበኩላቸው ጥቃት አድራጊ ቡድኑ የመከላከያ ሰራዊት ወደ አካባቢው በሚገባበት ጊዜ ቀድሞ ቦታ በመያዝ በሰራዊቱ አባላት ላይ ጥቃት ማድረሱን ተናግረዋል።

የክልሉ ሰላም ግንባታ እና ጸጥታ ቢሮ በበኩሉ በአካባቢው የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር ለማረጋጋትና የህግ የበላይነትን ለማስከበር እየሰራሁ ነው ብሏል። ይሁን አንጅ የአካባቢው ኗሪዎች በተደጋጋሚ በታጠቁ ኃይሎች ጥቃት ሲደርስብን ከመታደግ እና ቀድሞ ከመጠንቀቅ ይልቅ መንግስት እየደረሰ ያለው ጉዳት ከተፈጸመብን በኃላ ነው ሲሉ ቅሬታቸውን ገልጸዋል።

አዲስ ማለዳ በአካባቢው በተፈጠረው ጥቃት ሰለባ ሆኘ ከሞት ተረፍኩ ያለ አንድ ወጣት አነጋግራለች። “ጳግሜ አንድ ከሌሊቱ ሰምንት ስዓት በአካባቢው ከፍተኛ የተኩስ ድምጽ ሰምተን ምንድን ነው ብለን አንደተደናገጥን አግተው ወደ አንድ ትምህርት ቤት ውስጥ ወሰዱን። ቁጥራችን በግምት አርባ አንሆናለን አርባችንንም በገመድ አስረው ትምህርት ቤት ውስጥ አስገቡን በኋላም በተራ እያስወጡ ገንዘብ በመጠየቅ ገንዘብ ያለውን እየተቀበሉ በተራ ገደሏቸው።

እኔ እንዳጋጣሚ የታሰርኩበት ገመድ የላላ ስለ ነበር ከጎኔ የነበረው ታጋች እጀን በማስለቀቅ አግዞኝ እነሱ በተራ እየጠሩ ሲገድሉ በመስኮት አምልጨ ወደ ጫካ ገባሁ። ይሄው አሁን ፈጣሪ አትሙት ብሎኝ መከላከያ በአካባቢው ሲደርስ ከጫካ ወጥቼ እገኛለሁ። እንደ ነገርኩህ ከኔ ጋር ታግተው የነበሩ በግምት አርባ የሚጠጉ ያልኩህ እስካሁን በህይወት የተረፈ አላገኘሁም” ሲል ለአዲስ ማለዳ እማኝነቱን ሰጥቷል።

ቅጽ 2 ቁጥር 98 መስከረም 9 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here