ፍጥነት መገደቢያ ባላስገጠሙ ተሽከርካሪዎች ላይ ስምሪት መከልከል ተጀመረ

0
875

እስከ አሁን 800 የሚሆኑ አገር አቋራጭ መኪኖች አስገጥመዋል

ከመስከረም አንድ ቀን 2013 ጀምሮ የፍጥነት መገደቢያ መሣሪያ ያላስገጠሙ ተሽከርካሪዎችን የስምሪት ፈቃድ የመከልከል ሥራ መጀመሩን የፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን መሥርያ ቤት ለአዲስ ማለዳ ተናገረ።

የፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን መሥሪያ ቤት በተሰጠው ኃላፊነት የመንገድ ትራንስፖርት ትራፊክን ለመቆጣጠር በሚኒስቴሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 208/2003 ማንኛውም ተሽከርካሪዎች ፍጥነት መገደቢያ መሣሪያ ማስገጠም እንዳለበት መመሪያ አስቀምጧል።

የተዘጋጀውን መመሪያ ተግባራዊ ለማድረግ ከመስከረም አንድ ጀምሮ ትዕዛዙን ባላከበሩት እና የፍጥነት መገደቢያ መሣሪያ ያላስገጠሙ ተሽከርካሪዎች እንዳይንቀሳቀሱ የማድረግ እንዲሁም የስምሪት ወረቀት የመከልከል ሥራ ተጀምሯል ሲሉ የፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ይግዛው ዳኘው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ተሸከርካሪዎቹን በተገኙበት ከማስቆም እና ስምሪት ከመከልከል ባሻገር ግን የገንዘብ መቀጮ አለመቀመጡን ይግዛው ተናግረዋል። አክለውም የገንዘብ መቀጮው ከጥቂት ቀናት በኋላ ይፋ እንደሚደረግ ገልፀዋል።

ባለሥልጣኑ ወደዚህ እርምጃ ለመግባት የተገደድንበት ምክንያት በተገባደደው ዓመት በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉት ከ1.2 ሚሊዮን ተሸከርካሪዎች ውስጥ የፍጥነት መገደቢያ መሣሪያ ያስገጠሙ 1.4 በመቶ ብቻ በመሆናቸው እንደሆነ ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም መሥሪያ ቤቱ ለአዲስ ማለዳ አሳውቆ እንደነበረው ከፍጥነት መገደቢያ ጋር ተያይዞ የወጣውን አዋጅ ተግባራዊ የማያደርጉት ላይ የመጀመርያ የስምሪት አገልግሎት እንዳያገኙ የሚደረግ መሆኑን አንስተው፣ በተጨማሪም የማስተማር እና የማስጠንቀቅ ሥራ ሲሠራ መቆየቱን ጠቅሰዋል።

ይህንን ተላልፈው በሕገ ወጥ መንገድ ሲያሽከረክሩ የተገኙትን አሽከርካሪዎች ለመቆጣጠር በአራቱም ማዕዘን ያሉ ኬላዎች ላይ የቁጥጥር ሥራ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።

በመሆኑም እስከ አሁን ድረስ ባለው ሁኔታ ሁሉንም ተሽከርካሪዎችን ጨምሮ በኢትዮጵያ ከ1.2 ሚሊዮን በላይ ተሸከርካሪዎች ያሉ ቢሆንም፣ 17 ሺሕ 500 በላይ ብቻ የሚሆኑ ተሽከርካሪዎች ማስገጠማቸውን መሥሪያ ቤቱ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ስለሆነም ከመስከረም አንድ ቀን 2013 ጀምሮ የፍጥነት መገደቢያ መሣሪያ በተሽከርካሪዎቻቸው ላይ ያላስገጠሙ የአገር አቋራጭ የሕዝብ ማጓጓዣ ባለንብረቶች ማኅበራትና ድርጅቶች ስምሪት መከልከል መጀመሩን ይግዛው ተናግረዋል። በተጨማሪም ከመናኽሪያ ውጪ በሕገ ወጥ መንገድ የሚሠሩ ካሉ በሁሉም መውጫ በሮች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር እንደሚደረግም ተናግረዋል።

የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ የተሽከርካሪ ፍጥነት መገደቢያ መሣሪያ ስለመግጠም እና ስለማስተዳደር በሚል በታኅሳስ ወር 2011 የፀደቀው መመርያ ቁጥር 27/2011 ተግባራዊ ከሆነበት ጊዜ ጀምሮ፣ እስከ 2012 በጀት ዓመት ማጠናቀቂያ ድረስ 17 ሺሕ በላይ በሆኑ የጭነት እና የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ላይ ተገጥሟል። ቁጥሩም እስከ አሁን ባለው አነስተኛ መሆኑን የፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል።

ይሁንና በዚሁ በመመሪያው መሰረት መተግበር የጀመረው በ2011 ሲሆን ነገር ግን አሁን በፌዴራል ደረጃ እየተሠራ ያለው አዳዲስ የሚገቡ ተሽከርካሪዎች ላይ አስገዳጅ ሆኖ፣ ገና ወደ አገር ውስጥ ሲገቡ መሣሪያውን ገጥመው እንዲገቡ እየተደረጉ ነው። በፈረንጆቹ አቆጣጠር ከ2000 የምርት ዓመት እና ከዛ በኋላ ባሉት ሥሪቶች የፍጥነት መገደቢያ መሣሪያ እንዲገጠም በሚል መመሪያ ወጥቶ እሱን በማስተግበር ላይ ነን ብለዋል።

አዲስ ማለዳ ከዚህ ቀደም በሠራችው ዘገባዋ ላይ አካታው የነበረው አንዱ የፍጥነት መገደቢያውን እንዳይጠቀሙ እንከን የሆነው፤ ከፍተኛ የግንዛቤ እጥረት ስላለ ነው የሚሉት ይግዛው፤ ‹‹የፍጥነት መቆጣጠሪያ ስንገጥም በቀላሉ መግባት ስንችል መንገድ ላይ ያስረናል›› በሚል እንደማይፈልጉት መናገራቸው የሚታወስ ነው።

ቅጽ 2 ቁጥር 99 መስከረም 16 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here