ከሦስት የኢንዱስትሪ ፓርኮች 132 ሚሊዮን ዶላር የውጪ ንግድ ገቢ መገኘቱ ተገለፀ

0
763

ገቢው ከአጠቃላይ የኢንዱስትሪ ፓርኮች የኤክስፖርት ገቢ 80 በመቶውን ይይዛል

በኢትዮጵያ በፈረንጆች 2019/20 ከሦስት የኢንዱስትሪ ፓርኮች 132 ሚሊዮን ዶላር የወጪ ንግድ ገቢ መገኘቱ ተገለፀ።
ገቢው የተገኘው በአሁኑ ወቅት በሥራ ላይ ከሚገኙ ዐስር የኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ከሦስቱ ብቻ ሲሆን፣ ከእነሱም 132 ሚሊዮን ዶላር የውጪ ንግድ ገቢ መገኘቱን ሴፍየስ ካፒታል የተሰኘው እና መቀመጫውን በዩናይትድ ኪንግደም ያደረገው የምርምር እና የትንተና ተቋም ይፋ አድርጓል።

እንደተቋሙ መረጃ ከሆነ በ2019/20 በኢትዮጵያ ከሚገኙ ሦስት ግንባር ቀደም የኢንዱስትሪ ፓርኮች ማለትም ከሐዋሳ የጨርቃ ጨርቅ እና አልባሳት ኢንዱስትሪ 73 ሚሊዮን ዶላር፣ ከቦሌ ለሚ የጨርቃ ጨርቅ እና ቆዳ ኢንዱስትሪ 44 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም ከምሥራቅ ጥምር ዘርፍ ኢንዱስትሪያል ዞን 15 ሚሊዮን ዶላር የውጪ ንግድ ዓመታዊ ገቢ መገኘቱን አስታውቋል።

በአጠቃላይ በአገር ውስጥ ከሚገኙት ዐስር ንቁ የኢንዱስትሪ ፓርኮች በአጠቃላይ 165 ሚሊዮን ዶላር የውጪ ንግድ ገቢ መገኘቱን ያመለከተው መረጃው፣ ከሦስቱ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ብቻ የተገኘው የ132 ሚሊዮን ዶላር ገቢም ከአጠቃላዩ የኢንዱስትሪ ፓርኮቹ የውጪ ንግድ ገቢ ወስጥ 80 በመቶን እንደሚሸፍን ገልጿል።
በተጨማሪም የኮምቦልቻ አልባሳት ኢንዱስትሪያል ፓርክ፣ የመቐለ አልባሳት ኢንዱስትሪያል ፓርክ እንዲሁም የአዳማ የጨርቃ ጨርቅ፣ አልባሳት፣ ማሽኖችና መሣሪያዎች የኢንዱስትሪ ፓርክ እያንዳንዳቸው በዓመት ከአራት እስከ ዘጠኝ ሚሊዮን ዶላር ከውጪ ንግድ ገቢ እንደሚያስገኙ መረጃው አመላክቷል።

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ዐስር ንቁ የኢንዱስትሪ ፓርኮች እንደሚገኙ ያስታወቀው የተቋሙ መረጃ፣ ከእነሱም አምስቱ የግል እንዲሁም አምስቱ ደግሞ የመንግሥት መሆናቸውን ጠቅሷል። በስራቸውም 189 ተቋማትና 71 ሺሕ ሠራተኞች እንደሚገኙም አስታውቋል። በተጨማሪም ኹለት በምረቃ ሂደት፣ አምስት በኮንስትራክሽን ሥራ እንዲሁም ተጨማሪ አምስት በእቅድ ደረጃ ያሉ የኢንዱስትሪ ፓርኮች መኖራቸውንም ጨምሮ ገልጿል።

ከእነዚህም የኢንዱስትሪ ፓርኮች የተገኘው የ165 ሚሊዮን ዶላር የውጪ ንግድ ገቢ በባለፈው ዓመት ከተገኘው የውጪ ንግድ ገቢ ጋር ሲነፃፀር የ16 በመቶ ጭማሪ ያሳየ ሲሆን፣ በአገሪቱ በዓመቱ በውጪ ንግድ ከተመዘገበው አጠቃላይ የ2 ቢሊዮን 9 መቶ 88 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ውስጥም አምስት በመቶውን እንደሚይዝ ታውቋል።

የኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ዓመታዊ የውጪ ንግድ ገቢ ከዚህ የበለጠ እንዳያድግ በተለይም በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ከሚያዚያ ወር ጀምሮ የተከሰተው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ የሠራተኞችን ቁጥር በመቀነስና ይህንም ተከትሎ ወደ ውጪ የሚላኩ ወርሃዊ ምርቶችን መጠን መቀነሱ ተግዳሮት እንደሆነበት ተገልጿል።
የኢንዱስትሪ ፓርክ ልማት ኮርፕሬሽን በያዝነው ዓመትም 400 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ወደ ውጪ ከሚላኩ ምርቶች ለማግኘት እቅድ መያዙን ያስረዳው መረጃው ይህም ካለፈው የ2019/20 ገቢ ጋር ሲነፃፀር በ2.4 እጥፍ እንደሚሆን ታውቋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 99 መስከረም 16 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here