ኢንዱስትሪ ፓርኮች ለሠራተኞች የቤት ግንባታ እያከናወኑ መሆኑ ተጠቆመ

0
1411

ኢንዱስትሪ ፓርኮች ሠራተኞቻቸውን የቤት አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ የቤት ግንባታ እያከናወኑ መሆኑን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስታወቀ።
በኢንዱስትሪያል ፓርኮች ውስጥ የሚሠሩ ሠራተኞችን የቤት አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ በባለሀብቶች እንዲሁም መንግሥትና ባለሀብቶች በጋራ ለኢንዱስትሪ ፓርክ ሠራተኞቻቸው የቤት አገልግሎት እንዲያገኙ ሲሠራ ቆይቷል። በዚህም መሰረት እስካሁን በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ሺንትስ የተባለ ድርጅት አራት ሺሕ ቤቶችን ለሠራተኞች ገንብቶ፣ የገነባውን ቤት በከፊል ሠራተኞችን የቤት ተጠቃሚ ማድረግ እንደቻለ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሌሊሴ ለሜ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ኮሚሽነሯ በአዳማ ኢንዱሰትሪያል ፓርክ ውስጥ የሚገኙ ኪንግደም እና አንቴክስ የተባሉ ድርጅቶች በግል ለሠራተኞቻቸው የቤት ግንባታ በማከናወን ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል። በተመሳሳይ ድሬድዋ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ተመሳሳይ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን ኮሚሽነሯ አመላክተዋል።

እንዲሁም በሐዋሳ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ውስጥ ያሉ ድርጅቶችም በተመሳሳይ ለሠራተኞቻቸው የቤት አገልግሎት ለማቅረብ የቤት መሥሪያ ቦታ መረከባቸውን ኮሚሽነሯ ገልጸዋል። ነገር ግን ከሐዋሳ ኢንዱስትሪያል ፓርክ መሬት ይረከቡ አንጅ እንቅስቃሴዎች አለመታየታቸው ተጠቁሟል።

እንደ ኮሚሽነሯ ገለጻ በአጠቃላይ የኢንዱስትሪ ፓርክ ሠራተኞችን ተጠቃሚነት ለማጠናከር በትኩረት እየተሠራበት ነው። ኮሚሽኑ የሠራተኞች የመጀመሪያ ጥያቄ የሆነው መሠረታዊ የቤት አገልግሎት ከተረጋገጠ በኋላ ሠራተኞች ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞችን ማግኘት እንዲችሉ እየሠራ ነው ያሉት ኮሚሽነሯ፣ ሠራተኞች በኢንዱስትሪያል ፓርክ ውስጥ ከማደግ በሻገር የራሳቸውን ነገር ፈጥረው ራሳቸውን ችለው የሚወጡበትንም እድል ለመፍጠር ጅምር ሥራዎች መኖራቸውን ጠቁመዋል።

ከተጀመሩት ሥራዎች ውስጥ በሐዋሳ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ከንግድ ባንክ ጋር በመቀናጀት ሠራተኞች ‹ታታሪ› የተሰኘ የሂሳብ ቁጥር ከፍተው ለሦስት ዓመታት ቆጥበው ራሳቸውን የሚችሉበት ሁኔታ አንዱ መሆኑ ተጠቁሟል። እንዲሁም ሠራተኞች በበዓላት ጊዜና ጥሩ ውጤት በሚያስመዘግቡበት ወቅት ጉርሻ የሚያገኙበትን መንገድ ኮሚሽኑ ከኢንቨስተሮች ማኅበርና ከባለሀብቶች ጋር በጋራ እየሠራ መሆኑን ሌሊሴ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ በተለያዩ ቦታዎች በመንግሥትና በግል ባለሀብቶች ሥራ ላይ በሚገኙ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ወስጥ በአሁኑ ስዓት አጠቃላይ ከ75 ሺሕ በላይ ሠራተኞች በሥራ ላይ እንደሚገኙ የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ሌሊሴ ተናግረዋል። በእነዚህ ሠራተኞች የተለያዩ ችግሮች እንደሚነሱ ኮሚሽነሯ አስታውሰው፣ ከሚነሱት ጥያቄዎች ውስጥም ዋነኛው በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ተቀጥረው የሚሠሩ ሠራተኞች መነሻቸው ከገጠራማ አካባቢ በመሆኑ በአካባቢው የመኖሪያ ቤት ሊኖራቸው እንደማይችል መሆኑን ጠቁመዋል።

በዚህም ሠራተኞች በኢንዱስትሪ ፓርክ ውሰጥ ተቀጥረው ሲሠሩ አንዱና ትልቁ ወጭ ሊሆን የሚችለው የቤት ኪራይ መሆኑን ሌሊሴ አብራርተዋል። የሠራተኞች የመጀመሪያ ችግር የሆነውን የቤት ኪራይ ወይም የቤት አቅርቦት ችግር ለመፍታትም ከዚህ በፊት ባለሀብቱ ራሱ ለሠራተኞች የቤት አቅርቦት ሥራ እንደሠራ እና መንግሥትና የግሉ ድርጅቶች በጋራ በመሆን ለሠራተኞች የቤት አቅርቦት አገልግሎት እንዲሻሻል ሲሠራ እንደነበር ሌሊሴ አስታውሰዋል።

በሌላ በኩል ሰባት የኢንዱስትሪ ፓርኮች የሰው ኃይል አቅርቦትን ለማሻሻል የአትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽንና ፈርስት ኮንሰልት ስምምነት ተፈራርመዋል። በስምምነቱ መሰረት በአዳማ፣ በደብረ ብርሃን፣ በድሬዳዋ፣ በባሕር ዳር፣ በሐዋሳ፣ በመቀሌ እና በኮምቦልቻ የኢንዱስትሪ ፓርኮች የሰው ኃይል አቅርቦትን በማሻሻል የሥራ ዕድል እና ቅጥር እንዲኖር ለማድረግም ይቻላል።

ስምምነቱ በተካሄደበት ወቅት ሌሊሴ እንደገለፁት፣ ኢንቨስተሮችን መሳብ ብቻ ሳይሆን ለኢንቨስተሮችም ምቹ ሁኔታን መፍጠር ዋነኛው አማራጭ ነው። በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ በዋናነት ከቤት ችግር ጋር በተያያዘ የሠራተኛ ፍልሰት የሚታይ ሲሆን፣ ይህም የሠራተኞችን ፍልሰት 97 በመቶ እንዳደረሰው ከዓመት በፊት ሌሊሴ ነሚ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የበጀት እና ቁጥጥር ቋሚ ኮሚቴ ባካሔዱት ስብሰባ ላይ መግለጻቸው ይታወሳል።

ቅጽ 2 ቁጥር 99 መስከረም 16 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here