የጎርፍ መጥለቅለቅና የተጎጅዎች ድጋፍ እጥረት

0
767

በኢትዮጵያ በዘንድሮው ክረምት ዝናብ በተለያዩ ቦታዎች ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ በመጣሉ በተለይም በአፋር፣ በጋንቤላ እንዲሁም በአማራ ክልል በርካቶች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል። በርካታ የግብርና ስብል ልማቶች ወድመዋል። ጎርፍ መጥለቅለቅ ባጋጠመባቸው አንዳንድ ቦታዎች እስካሁን ድረስ መሰረታዊ አስቸኳይ እርዳታ እየተደረገ አለመሆኑን ተጎጅዎችና ተፈናቃዮች እየገለጹ ይገኛሉ። ከተጎጅዎች በተጨማሪም በአፋርና በጋንቤላ ለተከሰተው የጎርፍ አደጋ መንግስትና ሚዲያዎች ትኩረት አልሰጡትም በማለት ፖለቲከኞችና ተጽኖ ፈጣሪ ሰዎች ቅሬታቸውን እየገለጹ ናቸው።

ባሳለፍነው ሳምንት መስከረም 04/2013 በጎርፍ አደጋ የተጎዱ ዜጎችን ለመደገፍ አስቸኳይና ዘላቂ ተግባራት ተለይተው እየተሰሩ እንደሆነ በቦታው ጉብኝት ያደረጉት የሰላም ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል እና የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል። በመግለጫው ላይ የሰላም ሚኒስትሯ እንዳሉት በኢትዮጵያ እየጣለ ባለው ከባድ ዝናብ በአምስት ክልሎች በሚገኙ 23 ዞኖች ላይ ጎርፍ ተከስቷል። በዚህም 580 ሺህ ዜጎች የጎርፍ አደጋ የተጋረጠባቸው ሲሆን እስካሁን 217 ሺህ ዜጎች በጎርፉ ምክንያት ከመኖሪያ አካባቢያቸው ተፈናቅለዋል ብለዋል። በተለይ በታችኛው የአዋሽ ተፋሰስ አካባቢዎች ላይ የጎርፍ አደጋው በስፋት መከሰቱንም ገልጸዋል።

መንግስት ለጉዳዪ ትኩረት አልሰጠውም ለሚለው ጉዳይ ሚንስትሯ ሲመልሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ(ዶ/ር) እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በጎረፉ ዜጎች ለከፋ ችግር እንዳይዳረጉ ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተሉት መሆኑንም ተናግረዋል። ነገር ግን እስካሁን ድረስ በተለይ በጋንቤላ ክልል በጎርፍ የተጠቁ የማህበረሰብ ክፍሎች ምንም አይነት ድጋፍ እንዳልተደረገላቸው እየገለጹ ይገኛሉ።

እንዲሁም ችግሩ ጎልቶ በታየበት በአፋር ክልል የአዋሽ ወንዝ ሞልቶ እስካሁንም ድረስ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ነው። በክልሉ በጎርፍ ተጠቅተው የተፈናቀሉ ዜጎች እስካሁን በቂ መሰረታዊ እርዳታ እለማግኘታቸውን ገልጸዋል። የአፋር ክልል መንግስት አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽፈት ቤት በበኩሉ ችግሩ የከፋ ስለሆነ ከአቅሜ በላይ ነው ብሏል። በአፋር ክልል ከነሀሴ ወር መጀመሪያ የጀመረው የጎርፍ መጥለቅለቅ በ17 ወረዳዎች 80 ቀበሌዎች አጋጥሟል ተብሏል። በዚህም ከ230 ሺህ በላይ ዜጎች ከመኖሪያ ቦታቸው ተፈናቅለዋል ሲል ክልሉ አስውቋል።

ወንዙን ወደ ተጥሮአዊ መስመሩ ለመመለስ የፌዴራልና የክልል የኮንስትራክሽን ልማት ድርጅቶች ርብርብ እያደረጉ ነው ተብሏል። በአጭር ጊዜ ስራ ወንዙን መስመር ከማስያዝ በተጓዳኝ ተጎጅዎችን መልሶ ለማቋቋም ከፌዴራልንና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጥምረት እየተሰራ መሆኑንም ተመላክቷል።

በአማራ ክልል የጣና ሐይቅ ውኃ ሞልቶ ወደ አካባቢው በመስፋፋቱ በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ምስራቅ ደንቢያ ወረዳ ጉዳት ማድረሱ ተነግሯል። የጎርፍ መጥለቅለቁ በቀላሉ የሚመለስ እንዳልሆነም እየተነገረ ይገኛል። በተከሰተው ድንገተኛ የጎርፍ አደጋ ለተጠቁ ኗሪዎች ለሚደረገው ድጋፍ በቂ አለመሆኑን ተጎጅዎች እየገለጹ ሲሆን መቂ ድጋፍ እንድደረግላቸውም መጠየቃቸውን የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ገልጿል።

ከሁለት ሳምንት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ(ዶ/ር) ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ባደጉት ውይይት የአፋሩ ሙሳ አደም «ክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴር ለተሰጠኝ እድል እያመሰገንኩኝ በብሄራዊ መግባባቱ ሂደት ላይ እጅግ በጣም ጥሩና አበረታች የሆኑ ውጤቶችን በሁለት ዙር ብቻ ለማስመዝገብ ችለናል ትልቅ ተስፋም ሰንቀናል። ክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴር ወደዚህ ጉዳይ ዝርዝር ከመግባቴ በፊት ግን አንድ መስታወሻ አለኝ በአንድ ደቂቃ ውስጥ በንባብ እንዳቀርብ ይፈቀድልኝ።

ወደ ብሄራዊ መግባባት አጀንዳ ከመግባታችን በፊት የሃገራችን አብዛኛው ክፍል እጅግ አስከፊ በሆነ የጎርፍ አደጋ ውስጥ ይገኛል። ከነዚህ ውስጥ መተሀራን ጨምሮ የአፋር ክልል ነዋሪዎች ዋናኛዎቹ ናቸው። ኩሩው የአፋር እና የመተሐራ ህዝብ በአዋሽ ተፋሰስ ባለስልጣን ደካማ የግድብ አሰራርና አስተዳደር እንዲሁም የቅደመ ማስጠንቀቂያ ሁኔታዎች አለመኖር የተነሳ እድሜ ልኩን ስሰቃይ አለ ዘንድሮም ብሶበታል።

የአደጋው መጠንና ያስከተለው ጉዳት ተመጣጣኝ ትኩረት አላገኘም። አርብቶአደሩና በግብርናው መስክ የተሰማሩ ወገኖቻችን ባዶ እጃቸው ቀርተዋል። በሚዲያዎች ተረስቷል፤መንገስትም ችላ ብሎናል፤ህዝባችን በሄሊኮፕተር ሄዶ የሚመጣ ሚኒስትር ሳይሆን ችግሩን በቋሚነት የሚፈታ በጎርፉ ምክንያት ሊከሰቱ የሚችሉ የጤና እክሎችን ታሳቢ አድርጎ የሚንቀሳቀስ ሀገራዊ ግብረ ሃይል ያስፈልገናልና እንደመንግስት ዛሬ ነገ ሳትሉ አስፈላጊውን የነፍስ ማዳንና የመልሶ ማቋቋም ሂደት ብትጀምሩ እኛም ከጎናችሁ ለመስለፍ ዝግጁ መሆናችንን በአጽንኦት ለመግለጽ እወዳለሁኝ።» መንግሰት ለተጎጅዎች ትኩረት ይሰጥ ዘንድ አሳስቧል።

ሙሳ አክሎም “ይህ የፖለቲካና የተቃውሞ ድምፅ አይደለም ይህ የችግረኛ ዜጋ ድምፅ ነው ሊሰማ ይገባል አብዛኛዎቹን ሚዲያዎች ለመከታተል ሞክሬያለሁኝ ቁንፅል ቁንፅል ነው”ብሏል። አዋሽ ወንዝ ከ30 ዓመት ወዲህ ለመጀመርያ ጊዜ በከፍተኛ መጠን በመጨመሩ ምክንያት በተለይም ከቆቃና ከከሰም ግድብ አቅም በላይ የሆነው ውሃ ከአዋሽ እስከ አፋምቦ ድረስ በአካባቢው ማህበረሰብ ላይ ጉዳት ማድረሱነ ሙፈሪያት በቦታው ላይ ተገኝተው ተጎጅዎችን በጎበኙበት ወቅት ተናግረዋል።

የክልልና ፌደራል መንግስቱ አደጋ ሊከሰት እንደሚችል በማሰብ ቀድሞ ሰፊ ርብርብ ማድረጉ እንደተጠበቀ ሆኖ አደጋው ከተገመተው በላይ ሰፋ ብሎ በመምጣቱ ችግሩ ሊከፋ ችሏል ያሉት ሙፈሪያት አሁንም በርካታ ቤተሰቦች እና ዜጎቻችን የአስቸኳይ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ከመኖራቸውም በላይ ቀጣይ ጉዳት እንዳይደርስም የተጀመረውን እርዳታ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለ ሆኖ ወንዙን ወደ ተለመደው ፍሰቱ ለመመለስ የተቀናጀ ርብርብ እንደሚጠይቅ አስገንዝበዋል።

የአፋር ክልል መንግስት የአካባቢው ነዋሪዎች መከላከያ ሰራዊት የፌደራል ፖሊስ አባላትና የአደጋ ስጋት መከላከል አመራሮችና ሰራተኞች በአጠቃላይ አደጋው ከደረሰበት ጊዜ አንስቶ በህይወት አድንም ይሁን በተለያየ አደጋውን የመከላከል ተግባራት ሰፊ ርብርብ እየተደረገ መሆኑም ተመላክቷል።
በቀጣይም አደጋውን በዘላቂነት ደረጃ በደረጃ ለመፋታት የአጭር የመካከለኛና የረጅም ጊዜ እቅዶችን በማስቀመጥ የተጀመረው ጥረት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ሁሉ በመቀናጀት ከግብ ለማድረስ እንደሚሰራ ሙፈሪያት ጠቁመዋል። ጎርፍ እዳ ሳይሆን የመልካም እድል በር እንዲሆንና አጋጣሚውን የህብረተሰቡን ዘላቂ መቋቋምና ደህንነት ለማረጋገጥ በጋራ ልንሰራ ይገባል ሱሉም ሚኒስትሯ አመላክተዋል። ችግሩን ለመቋቋምና ህብረተሰቡን መልሶ ለማቋቋም አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ሚኒስቴር መስሪያ ቤታቸው እንደሚቀጥልም አመላክተዋል።

የተከሰተውን የጎርፍ መጥለቅለቅ ለመከላከል እስካሁን የተሰሩ ስራዎችን በተመለከተ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ኢኒጂነር ስለሺ በቀለ(ዶ/ር) በበኩላቸው በበጋው ወቅት በአዋሽ ተፋሰስ ብቻ 136 ሚሊዮን ብር በማውጣት 130 ኪሎ ሜትር የሚረዝም የጎርፍ ጥበቃ ስራ መከናወኑን በዚህም የተነሳ ይደርስ የነበረውን ጉዳት መቀነስ መቻሉን አንስተዋል።

በመንግስት ደረጃ የምግብና የመጠለያ ቁሳቁስ ድጋፍ እየተደረገ ቢሆንም በቂና ለሁም አለመዳረሱ ቅሬታ ያስነሳው ጉዳይ ቢሆንም በመንግስትና በግል ተቋምና ግለሰቦች ከሚደረገው ድጋፍ በተጓዳኝ የተራድኦ ድርጅቶችም እየረዱ መሆኑ ተመላክቷል። ባሳለፍነው ሳምነት የኤልሻዳይ ሪሊፍ እና ዲቨሎፕመንት አሶሴሽን ከ1 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ቁሳቁስ ለግሷል። ድርጅቱ ከ300 በላይ ፍራሽና ከ60 በላይ ኩንታል ዱቄትን ጨምሮ የተለያዩ አልባሳትና የምግብ አቅርቦቶችን በክልሉ መንግስት በኩል ለተፈናቃዮች አስረክቧል።

አሁን ላይ ለችግሩ እንደ መፍትሔ እየተሰሩ ነው ከተባሉ ስራዎች ውስጥ ከአጭር ጊዜ መፍትሄ አንፃር ደራሽ ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶች አደጋው ለደረሰባቸው ዜጎች እየቀረቡ መሆኑንም ነው የገለጹ ሲሆን በጎርፉ ምክንያት ወረርሽኝና ሌሎች የጤና ችግሮች እንዳይከሰቱ በቅርበት እየተሰራ ሙፈሪያ መሆኑንም ተናግረዋል።

በጎርፍ ሳቢያ የተከበቡ ዜጎችን የማውጣት ስራም በሁለት ሄሊኮፕተሮችንና ጀልባዎችን በመጠቀም እየተከናወነ መሆኑንም ተነግሯል። ከአጭር ጊዜ መፍትሄ አንጻርም በቀጣዩ የበጋ ወቅት መሰል የጎርፍ መከላከል ስራ ተጠናክሮ እንሚቀጥል ሙፈሪያት አብራርተዋል። የጎርፍ አደጋውን በዘላቂነት ለመከላከል ስትራቴጂካዊ እቅድ አውጥቶ መንቀሳቀስ እንደሚገባም ሚኒስትሯ አመላክተዋል። ከዚህ አንጻር ወደ አዋሽ ተፋሰስ በሚገባው የሎጊያ ወንዝ ላይ አነስተኛ ግድብ ለመስራት ቅድሚያ ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑንም ተጠቁሟል።በወንዙ ላይ የሚሰራው ግድብም ለመስኖ ስራ እንሚውልም ተጠቁሟል።

በላይኛውና በመካከለኛው የአዋሽ ተፋሰስ ላይም ውሃን ማቀብ የሚችሉ ግድቦችን ለመስራት የሚያስችሉ ጥናቶችና ሌሎች ቅድመ ዝግጅቶች እየተከናወኑ መሆኑንም ገልጸዋል። በተለይ የቆቃ ግድብ ሲሞላ ወደ ዝዋይ ሃይቅ በማፋሰስ በመጥፋት ላይ ያለውን የአብያታ ሃይቅን መታደግ ይቻላል ነው ያሉት ሚኒስትሯ። ከክልሎች ጋር በቅንጅት በመሆን የተጠናከረ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ስርዓት ለማበጀት እየተሰራ መሆኑንም ሚኒስተሩ ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚነስትሩ ያሳለፍነው ሐሙስ መስከረም 7/2013 የፌደራል እና የክልል መንግሥታት አመራሮች በተለያ ክልሎች ዜጎችን ያጠቃውን የተፈጥሮ አደጋ አስመልክቶ መንግሥት የወሰዳቸውን እርምጃዎች መገምገማቸውን ገልጸዋል። ከፍተኛ የጎርፍ መጥለቅለቅ ቢከሠትም፣ ምንም ዓይነት የሞት አደጋ አለመድረሱ መልካም መሆኑን ያነሱት ጠቅላይ ሚነስትሩ የሀገር መከላከያ ሠራዊታችንም በየስፍራው ተገኝቶ አስፈላጊውን ድጋፍ እየሰጠ ይገኛል ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይሄን ይበሉ አንጅ የግምገማው ውጤት ምን እንደሆነና ወደፊትም እስከ መስከረም ወር መጨረሻ ድረስ ይቀጥላል ስለተባለው ከፍተኛ ዝናባና ሊስከትል ስለሚችለው አደጋ እና ስለሚሰሩ ስራዎች ያሉት ነገር የለም።

በዘንድሮው ክረምት በኢትዮጵያ በተለያዩ ቦታዎች በተከሰተው የተፈጥሮ አደጋ የሰው ሂወት አይጥፋ አንጅ ብዙዎችን ከቤት ንብረታቸውና በቀጣይ በጋ ወራት ለምግብ ፍጆታ የሚውል ብርካታ ሰብል ልማቶች መውደማቸው ተጎጅዎቸን በቀጣዩም በጋ ወራት ተረጅ ሊደርጋቸው እንሚችል እየተነገረ ነው። ተጎጅዎች አንደሚሉት የጎርፍ አደጋው ያስከተለው ጉዳት ሊጠናቀቅ የተያዘው መስከረም ወር ብቻ ይቀርዋል በተባለው ክረምት የሚበቃ እንዳልሆነ ተናግራል።
በጎርፍ መጥለቅለቅ የተከሰተውን የወደፊት ጉዳት ተጎጅወች ሲገልጹ በአርብቶ አደሩ አፋር ህዝብ ላይ የእንሰሳቶች መኖ መውደም፣ በጋንቤላ ክልል ደግሞ ግጦሽ መሬቶች ልምላሜ በጎርፍ መገፈፉ እና በአማራ ክልልም እንዲሁ የእርሻ ማሳዎች በጎርፍ መሸርሸር ስላባው እስከ ቀጣዩ ዓመት እንደሚዘልቅ ተናግረዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 99 መስከረም 16 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here