በቤኒሻንጉል በኹለት ወራት 150 ሰዎች መገደላቸውን ፓርቲዎቹ አስታወቁ

0
770

በቤኒሻጉል ጉሙዝ ክልል የሚንቀሳቀሱ ሦስት የፖለቲካ ፓርቲዎች በክልሉ በመተከል ዞን ከሠኔ 22/2012 እስከ መስከረም 8/2013 ድረስ ከ150 በላይ ዜጎች ሕይወታቸወን እንዳጡ ጥናት አድርገው ማረጋገጣቸውን ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል። በክልሉ የሚንቀሳቀሱት የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቦዴፓ)፣ የጉምዝ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ እና የቤኒሻንጉል ጉምዝ ሕዝብ ነፃነትና ንቅናቄ ለሰላምና ዴሞክራዊ ድርጅት (ቤሕነን-ሰዴድ) ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቁት፣ ከሠኔ 22/2012 ጀምሮ እስከ መስከረም 8/2013 ብቻ በጉባ፣ በወንበራና በቡለን ወረዳዎች በታጣቂዎችና በፀጥታ አካላት በተወሰዱ እርምጃዎች ከ150 በላይ ሰዎች መሞታቸውንና ከ50 በላይ ዜጎች ላይ የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው አስታውቀዋል።

እንዲሁም ከ700 በላይ ሰዎች በጅምላ እንደታሰሩና ከ35 ሺሕ በላይ ዜጎች ከቀያቸዉ መፈናቀላቸዉን ባደረግነዉ ጥናት ለማረጋገጥ ችለናል ብለዋል።
ፓርቲዎቹ የኅብረተሰቡን ደኅንነትና ሰላም ማስጠበቅ ያልቻለዉ የክልሉ መንግሥት ኮማንድ ፖስት ችግሩን እያባባሰ ስለሆነ፣ በአስቸኳይ ከቦታዉ እንዲነሳና ችግሩ በዘላቂነት ለመፍታት ሁሉን ዐቀፍ ሕዝባዊ ኮንፈረንስ እንዲካሄድ እንጠይቃለን ሲሉ አስታውቀዋል።

አክለውም የክልሉ መንግሥት በመደበኛዉ መዋቅር ክልሉን መምራት ባለመቻሉ ከኹለት ዓመታት በላይ መተከል ዞን በኮማንድ ፖስት እየተመራ እንደሚገኝ አውስተዋል:: ይሁን እንጂ ዞኑ በኮማንድ ፖስት እየተመራ ባለበት ሁኔታ ከ2011 ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ጃዊ አካባቢ የተገደሉት ጉሙዞችን ጨምሮ በቁጥር ከ800 በላይ ሰዎች በአመራሩ መልካም አስተዳደር ችግሮች ምክንያት ሕይወታቸው አልፏል፣ ብዙዎቹ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፣ ከቀያቸውም ተፈናቅለዋል ሲሉም ፓርቲዎቹ በጥናት አረጋግጠናል ያሉትን መረጃ ገልጸዋል።

‹‹የአንድ መንግሥት ቀዳሚ አጀንዳ የዜጎች ደኅንነትና ሰላም ማስጠበቅ ነው። ይሁን እንጂ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግሥት የዜጎችን ደኅንነትና ሰላም ማስጠበቅ፣ የሕግ የበላይነትን ማስከበርና የዜጎች ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ማስከበር ባለመቻሉ ለደረሰው ጉዳት ኃላፊነት ባለ መወጣት ተጠያቂ መሆን አለበት። ስለሆነም የፌዴራል መንግሥት ጉዳዩን በገለልተኝነት እንዲያጣራ ጥሪ እናቀርባለን።›› ሲሉ ፓርቲዎቹ ለፌዴራል መንግሥት ጥሪ አቅርበዋል።

የክልሉ መንግሥት በበኩሉ በመተከል ዞን በተለያዩ አካባቢዎች ከተፈጠረው የጸጥታ ችግር ጋር በተያያዘ ተሳትፈዋል የተባሉ 358 የሚሆኑ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ማዋሉን በክልሉ ሰላም ግንባታ እና ጸጥታ ቢሮ በኩል አስታወቋል። ከሰሞኑ በመተከል ዞን ቡለን እና ወምበራ ወረዳ አንዳንድ ቀበሌዎች ከነበረው የጸጥታ ችግር ጋር በተያያዘ እየተሠራ ባለው የሕግ ማስከበር ሥራ የተለያዩ ተሳትፎዎችን አድርገዋል የተባሉ ተጨማሪ 30 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ማዋሉንም የክልሉ መንግሥት ገልጿል።

የክልሉ መንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ መለሰ በየነ ሰሞኑን ለክልሉ መገናኛ ብዙኀን እንዳስታወቁት፣ በክልሉ ከአንድ ዓመት በፊት የተዋቀረው ኮማንድ ፖስት ለቀጣይ ሦስት ወራት በመተከል ዞን የአካባቢውን ሰላም የማስመለስ ሥራውን አጠናክሮ እንዲቀጥል ተወስኗል።

ከሰሞኑ ግጭት አስተናግደው ያለፉ ቀበሌ ኗሪዎች አሁን ላይ የአካባቢው ሰላም ያለበትን ሁኔታ ለአዲስ ማለዳ ሲገልጹ፣ በአካባቢው መከላከያ ሠራዊት ገብቶ መልካም ሥራ መሥራቱን መስክረዋል። ነገር ግን በአካባቢው ላይ የተፈጠረው ድርጊት ከስጋት ነፃ የሚያደርግ አይደለም። እናም መንግሥት ዘላቂና ጥብቅ ጥበቃ ካላደረገልን ከስጋት ነፃ ሆነን ለመኖር እንቸገራለን ሲሉ ተናግረዋል።

የክልሉ መንግሥት በተፈጠረው ግጭት ሕይወታቸውን ያጡ ዜጎች ቁጥር በግልጽ ከመናገር ይልቅ ‹ቁጥር መግለጹ ሌላ ችግር ይፈጥራል፤ እንጂ ፋይዳ የለውም› በማለት ትክክለኛውን ቁጥር ከመግለጽ ተቆጥቧል።

ቅጽ 2 ቁጥር 99 መስከረም 16 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here