በአፍሪካ በርዝመቱ ቀዳሚ የሆነ መስቀል በአዲስ አበባ እየተገነባ ነው

0
1126

በአፍሪካ በርዝመቱ የመጀመሪያ የሆነ 64 ሜትር ከፍታ ያለው መስቀል በአዲስ አበባ ቀበና ደብረ እንቁ ልደታ ቤተክርስትያን እየተገነባ ነው።
በቀበና ከጀርመን ኤምባሲ ጀርባ ጋራ ስር የሚከናወነው ይህ የመስቀል ግንባታ ፕሮጀክት፣ በአሁኑ ጊዜ የመሠረት መቀመጫው ተጠናቆ ቀጣዩን የግንባታ ሥራ ለማስጀመር የግንባታ ግብዓት በማቀረብ ሂደት ላይ መሆኑን የፕሮጀክቱ የቴክኒክ መሀንዲስ ኢንጅነር ዮሴፍ አንዳርጋቸው ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
የቴክኒክ መሀንዲሱ እንደገለጹት የመስቀል ፕሮጀክቱ በውስጡ ፓራናሚክ አሳንሰር ይገጠምለታል ብለዋል። በዚህ ግዙፍ መስቀል ላይ 40 ሜትር ከፍታ ላይ መላው አዲስ አበባን ሙሉ በሙሉ ማሳየት የሚያስችል ሰገነት ያለው መሆኑን አክለው ተናግረዋል።

በተጨማሪም በመስቀሉ ውስጥ የሚገጠም አብረቅራቂ መብራት ይኖረዋል ተብሏል። በአፍሪካ ትልቅ ከፍታ አለው የተባለው በመቀሌ ከተማ ተራራ ላይ የሚገኘው 52 ሜትር ከፍታ ያለው ‹መስቀል ጮምዓ› ነው። ይሁን እንጂ ይኸው አዲሱ የመስቀል ግንባታ ከዚህ ቀደም ተይዞ የነበረውን ሪከርድ ያሻሽለዋል ተብሎም ይጠበቃል።
ኢንጅነር ዮሴፍ አያይዘው የፕሮጀክቱ ይዘት ቱሪስት መስህብን መሰረት ያደረገ ነው ብለዋል። ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅም ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ትልቅ የቱሪስት ሀብት እንደሚሆንና ለአገሪቱም የገቢ ምንጭ ሊያስገኝ የሚችል ግዙፍ የአገር ሀብት መሆኑን ተናግረዋል።

በቦታው ላይ እየተገነባ በሚገኘው የመስቀል ፕሮጀክት በተጨማሪ የቤተክርስትያኗን ሕንፃ ቤተክርስትያን ጨምሮ ዓለም ዐቀፍ ጥናት እና ምርምር ማዕከል፣ ከተራራ ስር በግማሽ ተፈልፍሎ የሚሠራ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን ጥንታዊ ታሪክ የሚያስቃኝ ግዙፍ ቤተ መዘክር፣ ጎብኚዎች በቀጥታ እንዲከታተሉት የሚያስችል የድጓ፣የዝማሬ፣ የቅዳሴ እና የአቋቋም ስምንት ክፍሎች ያሉት የአብነት ትምህርት መማሪያ እንደሚገነባ ተመላክቷል።

እንዲሁም ለሕዝብ ክፍት የሚሆን እስከ አምስት ሺሕ ሰው የሚያስተናግድ ግልፅ አንፊ ቲያትር፣ ግዙፍ ዘመናዊ የደመራ ፕላዛ እና በዲዛይን የሚለሙ የአበቦች እና የአገር በቀል ዛፎች ፓርክ እንደሚካተት አብራርተዋል። በተጨማሪም በአምስት ሺሕ ካሬ ላይ የሚያርፍ እስከ አራት ሺሕ ሰው ማስተናገድ የሚችል አዳራሽ በፕሮጀክቱ ተካቷል። አዳራሹ የሚገነባው ከወለል በታች ነው ተብሏል።

የመስቀል ፕሮጀክቱ አካል የሆኑት ዝርዝር ፕሮጀክቶች በተለያዩ በጎ ፈቃደኛ መሀንዲሶች ተከፋፍሎ የግንባታ ሥራው እየተከናወነ መሆኑን ዮሴፍ ተናግረዋል። በዚሁ መሠረት ሕንፃ ቤተክርስትያኑ ከ60 እስከ 70 በመቶ የሚሆነው ሥራ መከናወኑን ገልጸዋል።

ፕሮጀክቱን ለማስጀመር ከኹለት ዓመት በላይ ዝርዝር ጥናት ሲደረግ መቆየቱን በማስታወስም፣ ፕሮጀክቱን ሙሉ በሙሉ ለማጠናቀቅና ሥራ ለማስጀመር ከሦስት ዓመት ያላነሰ ጊዜ እንደሚፈጅ ጠቁመዋል።

የፕሮጀክቱ አካል የሆኑትን ሙሉ የግንባታ ሥራዎችን ለማጠናቀቅ ከ60 እስከ 80 ሚሊዮን ብር ሊፈጅ እንደሚችል ዮሴፍ ተናግረዋል። ነገር ግን ፕሮጀክቱን ለማጠናቀቅ የሚፈጀው ትክክለኛ ገንዘብ ምን ያክል እንደሚሆን ለማረጋገጥ የትንተና ሥራው ገና በሂደት ላይ መሆኑ ተጠቁሟል። እንደ ዮሴፍ ገለጻ ፕሮጀክቱ የቤተክርስትያን ሥራ ስለሆነ በሕዝብ ድጋፍ እንደሚሠራ ታምኖበት መጀመሩን በመጠቆም፣ ከራሳቸው ጀምሮ የተለያዩ ባለሙያዎች በነፃና ሁሉም በሚችለው እየተሳተፈ መሆኑን አመላክተዋል።

ፕሮጀክቱ ለመላው ኢትዮጵያዊ፤ ለሙስሊሙም ለክርስትያኑም የጋራ ሀብቱ በመሆኑ በአገር ውስጥና በውጭ አገር በገንዘብና በግንባታ ግብዓት ገቢ ለማሰባሰብ በቤተክርስትያኗ የተቋቋመ ኮሚቴ የገንዘብ ማሰባሰብ ሥራውን እና የግንባታ ግብዓት ግዥውን እያከናወነ ነው ተብሏል።

ቅጽ 2 ቁጥር 99 መስከረም 16 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here