የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አንድ ኩንታል የዳቦ ዱቄት በ 800 ብር ሲያቀርብላቸው የነበረው ሂደት ባልታወቀ ምክንያት እንዳቋረጠባቸው ዳቦ ጋጋሪዎች ለአዲስ ማለዳ ገለጹ፡፡
አንድ ኩንታል ዱቄት በ 800 ብር ማቅረብ በመቆሙም ምክንት ዳቦ ጋጋሪዎቹም ከፍተኛ ችግር ውስጥ መግባታቸውን እና አሁን በሶስት እጥፍ አድጎ አንዱን ኩንታል በ2 ሺህ 650 ብር በኩንታል ከፋብሪካዎች እየገዙ እየተጠቀሙ መሆኑን አንስተዋል፡፡
የዳቦ ቤቶች ባለንብረቶች እንደሚሉት፣ መንግሥት የሚያቀርብላቸው የዳቦ ዱቄት ዋጋ በአንድ ኩንታል በ 800 ብር ሲሆን፣ 15 ኩንታል በ 12000 ብር በወር ኹለት ጊዜ ይረከቡ እንደነበር ይናገራሉ። ነገር ግን ከትስስር (መንግሥት የዳቦ ዱቄትን በቅናሽ የሚያስረክባቸው አባላት መደብ) እንዲወጡ ከተደረጉ በኋላ፣ ከግል ነጋዴዎች ላይ አንድ ኩንታል የስንዴ ዱቄት በ 1 ሺሕ 800ብር ለመግዛት እየተገደዱ መሆኑን እና በዚህም ምክንያት የዳቦ ዋጋ ላይ ጭማሪ ማድረጋቸውን ይናገራሉ።
ከዚህ በተጨማሪም ዳቦ ጋጋሪዎቹ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት ከሆነ በምን ምክንያት ዱቄት መሰጠት እንዳቆመ ተደጋጋሚ ጥያቄ ብንጠይቅም ምክንያቱ እንኳን ሳይነገረን ‹‹ እስከ መስከረም ግማሽ ወይንም ጥቅምት መጀመርያ ላይ ይመጣል ጠብቁ›› የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡
ይሁን እና በዚህ ምክንያት ከባድ ኪሳራ ውስጥ ከመግባት ባለፈ አሁን ላይ መንግስት እያደረገ ያለው ሸገር ዳቦ ስለተከፈተ አነስተኛ ዳቦ ጋጋሪዎችን ከገበያ የማስወጣት ስራ እየተሰራ ነው በማለት ይናገራሉ፡፡ ‹‹ብንናገርም የሚሰማን አካል የለም›› አሁን ካለው አንፃራዊ ሁኔታ ጋር ስናየው ‹‹ ስንዴው ሸገር ዳቦ ጋር እና በጎርፍ ምክንያት ለተፈናቀሉ ሰዎች ወደ እዛ እየሄደ ነው›› የሚል ሃሳብ ነው ያለን፡፡ በሕጋዊ አካሔዱ መሰረት ቅድሚያ ወረዳ ሄደን ከዛ ደብዳቤ ከተፃፈልን በኋላ ክፍለ ከተማ እንሄድና ክፍለ ከተማው ደግሞ ድጋሚ ደብዳቤ ይሰጠን እና እሱን ይዘን ፋብሪካ እንሄዳለን ከዛ አንድ ኩንታል 800 ብር እንረከብ ነበር አሁን ግን አንድ ኩንታል በብዙ ዕጥፍ ጨምሮብን 2650 ብር ነው ምንገዛው ሲሉም አስረድተዋል፡፡
ማንን ማናገር እንደምንችልም አናውቅም ከፍተኛ ችግር ውስጥ ነው ያለነው፡፡ ንግድ እና ኦንዱስትሪ ሚኒስቴር ሳይቀር ጥያቄ አቅርበን ነበር ታገሱ ከማለት ውጪ ምንም ምላሽ ማግኘት አልቻልንም በማለት ዳቦ ጋጋሪዎቹ ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የንግድ እና ኢንዱስትሪ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት ምንም አይነት ዱቄት እጥረት እንዳልተፈጠረ እና ከዚህ ቀደም እንደነበረው ነው ያለው ብለዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ስለተነሱት ቅሬታም የሚያውቁት ነገር እንደሌለ የንግድ እና ኢንዱስትሪ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡
ነገር ግን ካለፈው አመት ጀምሮ መተግበር የጀመረው ይህ ዱቄት እያጠፉ እያመጡ ያለው አሰራር ተጠናክሮ መቀጠሉን እና በቀን ከሦስት ሺሕ ዳቦ በታች የሚያመርቱ ዳቦ ቤቶች አቅማቸውን ካላሳደጉ ዱቄቱን እንዳማያቀርብላቸው እንደተነገራቸው የዳቦ ቤት ባለቤቶች ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።



