የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ከተማዋን ደረጃ ወደ ሪጅዎፖሊታንት ለማሳደግ ጥናት አድርጎ ለአማራ ክልል ማቅቡን አስታወቀ፡፡
የከተማዋን የመዋቅር እድገት ለማሳደግ የደብረ ብርሃን ከተማ ነባራዊ ሁኔታን በከተማ አስተዳደሩ የተቋቋመ ኮሚቴ ጥናት አድርጎ ማጠናቀቁ ተገልጿል፡፡
ደብረ ብርሃን አሁን ከምትገኝበት ፈርጅ አንድ የከተማ አስተዳደር ደረጃ ወደ ሪጅዎፖሊታንት ከተማ በማሳደግ ከተማዋን በክፍለ ከተማ ደረጃ ለማደራጀት የተጀመረ ሥራ መሆኑን የተቋቋመው ኮሚቴ ሰብሳቢና የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ህንፃ ሹም ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አምሳሉ መኮንን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡ ኃላፊው እንደገለጹት ደብረ ብርሃን ከተማ አሁን ላይ ያላት መዋቅር በቀበሌ ደረጃ ብቻ የተዋቀረ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ከተማዋ አሁን ከደረሰችበት ስፋት አንፃር በቀበሌ ደረጃ የተዋቀረው አደረጃጀት ተመጣጣኝ አለመሆኑን የገለጹት ኃላፊው የከተማዋን አደረጃጀት በክፍለ ከተማ ደረጃ ለማዋቀር ያለመ ነው ብለዋል፡፡ እንዲሁም የከተማዋ አደረጃጀት ለተቀላጠፈ አሰራርና አገልግሎት ምቹ እንዳልሆነ የጠቆሙት ኃላፊው አዲስ መዋቅር ችግሩን ይፈታዋል ተብሎ ይታሰባል ብለዋል፡፡
ደብረ ብርሃን ከተማ አንድ ከተማ ሪጅዎፖሊታንት ደረጃ ለማግኘት ከ250 ሺሕ በላይ የህዝብ ቁጥር እንደሚስፈልግ ለአዲስ ማለዳ የገለጹት ኃላፊው ደብረ ብርሃን አሁን ላይ ከቀበሌዎች በተሰበሰበ መረጃ 350 ሺሕ በላይ የህዝብ ቁጥር እንዳላት ገልጸዋል፡፡
ኃላፊው ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት ከተማ አስተዳደሩ የደብረ ብርሃንን ነባራዊ ሁኔታ በማጥናት እንዲሁም የሌሎች ከተሞችን ተሞክሮ በማካተት መስከረም 22/2013 ለክልሉ መንግስት አዲሱን የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር መዋቅር ጥናት እንደሚያቀርቡ አመላክተዋል፡፡ የክልሉ መንግስት የቀረበለትን አዲስ የመዋቅር ደረጃ እድገት ተቀብሎ ካጸደቀው ደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር በክፍለ ከተማ ደረጃ አንደምትዋቀር ኃላፊው ተቁመዋል፡፡
አዲስ የቀረበው የመዋቅር እድገት ጥናት በአማራ ክልል ከተማ ልማት ቤቶች ኮንስትራክሽን ቢሮ ተቀባይነት አግኝቶ ከጸደቀ ደብረ ብርሃን ከተማ ተጠሪነቷ ለክልሉ መንግስት እንድትሆን ያስችላታል ብለዋል አምሳሉ፡፡
የከተማዋን ደረጃ ማሳደግ ለከተማዋ እድገት ከፍኛ ጥቅም እንደሚኖረው የጠቆሙት ኃላፊው ወደ ከተማዋ የሚመጡ ኢንቨስትመንቶችን ለመሳደግ ሚና እንደሚኖረው ጠቁመዋል፡፡ ወደ ከተማዋ የሚመጡ የኢንቨስትመንት ጥያቄዎችን በቀጥታ ከመቀበልና ከማሳደግ በተጨማሪም ከተማዋ የሚኖራት ስልጣን ከፍ ስለሚል ችግሮቿን በራሷመፍታት እንድትችልና ተጨማሪ የስራ ማስኬጅና የካፒታል በጀት እንድታገኝ ያስችላታል ተብሏል፡፡
ከተማዋን በአዲስ አደረጃጀት ለማዋቀር የመጨረሻ የክፍለ ከተሞችና የቀበሌዎችን ቁጥር መግለጽ አይቻልም ቢልም የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር የከተማዋ መዋቅራዊ ጥናት መነሻ ሀሳብ በከተማ አስተዳደሩ የተቋቋመው ኮሚቴ ባስቀመጠው የመነሻ ሀሳብ 5 ክፍለ ከተሞች፣ በከተማዋ 17 ቀበሌዎች፣ በክፍለ ከተማ ደረጃ አገልግሎት ሰጭ ተቋማት በጽሕፈት ቤት ደረጃ እንዲደራጁ እና የክፍለ ከተሞች ስያሜ ከከተማዋ ታሪካዊ ኩነቶች ጋር የተዛመዱ እንዲሆኑ ተደርገው ታጭተው ቀርበዋል፡፡
በቀረበው ምክረ ሀሳብ መሰረት የክፍለ ከተሞች ስያሜ ሚኒሊክ ክፍለ ከተማ፣ ዘርዓያዕቆብ ክፍለ ከተማ፣ ልቼ ክፍለ ከተማ፣ አንሳስ ማሪያም ክፍለ ከተማ፣ ጠባሴ ክፍለ ከተማ፣ እቴጌ ጣይቱ ክፍለ ከተማ እና እሌኒ ክፍለ ከተማ የሚሉት በእጩነት የቀረቡ ስያሜዎች ናቸው፡፡
ደብረ ብርሃን ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በአካባቢው ባለው የሰላምና ምቱ የሥራ አሁኔታ በኢንቨስመንት ዘርፍ ከሌሎች አካባቢዎች በተሻለ ማረፊያ እየሆነች እና ጥሩ የሚባል የኢንቨስትመንት ስበት እያገኘች እንደምትገኝም በቅርቡ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ሲዘገብ መቆየቱ የሚታወስ ነው።



