ባለፉት ሁለት ዓመታት ጊዜ ውስጥ በተደራጁ ቡድኖች የሚፈፀሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እየተበራከቱ እንደሆነ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ጉባኤ ጥናት አመላከተ፡፡
በሀገሪቱ ባለፉት 27 አመታት በመንግስታዊ ተቋማት ይደርስ እንደነበረው የሰብአዊ መብት ጥሰት ሁሉ ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ከመንግስት መዋቅር ውጪ ያሉ በመላው አገሪቱ የሚገኙ ኢ-መደበኛ ቡድኖች የሚፈፅሟቸው የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እየተበራከቱ መምጣታቸውን በጠቅላይ አቃቤ ሕግ ስር የሚሰራው የሚዲያ ሕግ ቡድን መሪ ሰለሞን ጎሹ ለ አዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
በእነዚህ ኢ-መደበኛ በተባሉት ቡድኖች የሚፈፀሙት የሰብአዊ መብት ጥሰቶችም በርካታ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ሰለሞን ጨምረው ገልፀዋል፡፡
እንደ ቡድን መሪው አስተያየት ባለፉት 27 ዓመታት የጸጥታ ኃይሎች ለሰብዓዊ መብት ትኩረት ስለማይሰጡ እና ማናቸውም አይነት የሁከት ምልክት በተፈጠረ ቁጥር ካለምንም ማጣራት ከሕግ አግባብ ውጪ ይወስዱት የነበረው እርምጃ በህብረተሰቡ ዘንድ ፍርሀትን ሲፈጥር ቆይቷል።
ይህ እንዳለ ሆኖ በጊዜው መደበኛ ባልሆኑ ቡድኖች የሚፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በጣም አናሳ እንደነበሩና ከለውጡ ጋር በተያያዘ ግን የተደራጁ ቡድኖች ቁጥር መበራከትና ጥቃት ማድረስ ዋነኛው የወቅቱ ፈተና እንደሆነ ገልጸው እየተፈፀሙ ያሉት አንዳንድ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ለፖለቲካዊ ፍጆታ የማዋል ሁኔታዎች የተስተዋለባቸው ናቸው ይላሉ፡፡
ይህ ሁኔታ ከተፈጠረዉ ሁከትና ብጥብጥ ባሻገር በሕዝብ ዘንድ የመከፋፈልን፣ያለመረጋጋትን፣የመጠላላትና፣የፍርቻ ስሜትን በመፍጠር ማህበራዊ መረጋጋቱን አውኮታል ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ጨምረው ተናግረዋል።
ባለፉት ሁለት አመታት የሰው ልጅ ሰው በመሆኑ ብቻ የተቸራቸዉን መብቶች መጣስ ሰዎችን ማፈናቀል፣ነፃነታቸውን መንፈግ፣ንብረታቸውን ማውደም፣ማገት፣ህይወታቸውን ማጥፋት፣አካል ማጉደል፣ከአካላዊ ጥቃት አልፎ ስነልቦናዊ በሰላም የመኖር፣ተከባብሮ የመኖር፣ ባሉበት ቦታ እየሰሩ የመኖር መብትን በስፋት ሲነጠቁ ታይቷል እንደባለሙያው ሀሳብ።
ለምሳሌ ያክል በ2010 እና 2011 ከጌዲዮ ዞን 860,ሺሕ 56 አካባቢ የሚሆኑ ሰዎች ፣ በጉጂ ዞን ደግሞ በተለያዩ ቀበሌዎች 3,330 የሚሆኑ አባወራዎች በቤተሰብ ደረጃ ደግሞ 9,325 ዜጎች መፈናቀላቸውን አዲስ ማለዳ ካየቻቸው የኢሰመጉ ዶሴዎች ማግኘት ተችሏል።
ከለውጡ ማግስት በተደራጁ ቡድኖች የሚደርሰዉ የሰብአዊ መብት ጥሰት በጣም አሳሳቢ ሆኗል ለዚህም ችግር መበራከት መንስኤው መንግስት እንደከዚ ቀደሙ ስርአት ሀይልን በሃይል ከመመለስ ይልቅ በውይይት ስለሚያምን ነው የሚሉ ሰዎች እንዳሉ ጠቁመው።መንግስት እርምጃ ከመውሰድ አንፃር ያሳየው ከልክ ያለፈ ትዕግስት ለእነዚህ ጥሰቶች መብዛት ከፍተኛ ምክንያት እንደሆነና አንዳንድ ገለልተኛ ያልሆኑ ሚዲያዎች ለጉዳዩ አስተዋፅኦ እንዳላቸውና በዚህም ለግጭት መነሻ የሆኑ ነገሮችን ያሰራጩ እንደነበር ሰለሞን ተናግረዋል፡፡
መገናኛ ብዙሀን የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ከመዘገብ ጋር በተያያዘም ከፍተኛ ክፍተት እንዳለባቸው ገልፀዋል። ገለልተኛ ያልሆኑ ሚዲያዎች መኖራቸዉ በሰው ዘንድ ጥላቻን በመፍጠር፣በመከፋፈል የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በማፋፋም እረገድ ከፍተኛ ድርሻ እንዳላቸዉ አስረድተዋል።
በኢትዮጵያ የሚፈፀመው የሰብአዊ መብት ጥሰት በዚሁ ከቀጠለ ከፍተኛ የሆነ የደህንነት ቀውስ እንደሚያስከትልና ለአገሪቷም አሳሳቢ እንደሆነ፤መንግስት ይህንን ጥቃት ከማስቀረት አንፃር አቅሙን አደራጅቶ የህግ ጥበቃ ማድረግና ህግን ማስከበርን በከፍተኛ መልኩ ጠንካራ ስራ መስራት እንደሚያስፈልግ ቡድን መሪው ጠቁመዋል።
መብትን ያከበረ ውጤታማ የሆነ የፍትሕ ስርአትን መገንባት አስተማማኝ የሆነ የሰብአዊ መብትን ለማሟላትና ዘላቂ መፍትሄን ለመፍጠር መንደርደሪያ ነው።ሰብአዊ መብቶችን መንግስት ብቻ እንዲያስከብር ሳይሆን ሌሎችም ባለድርሻዎች እንዲያስከብሩ መገናኛ ብዙሃን የራሳቸዉ አስተዋፅዖ ማድረግ እንዳለባቸዉም ጠቁመዋል።
የሰብአዊ መብቶችን በማስጠበቅ ረገድ በሀገሪቱ ላይ ፈታኝ የሆነው ነገር መደበኛ ያልሆኑ አደረጃጀቶች በየአካባቢዉ ብሄርን መሰረት አድርገው መዋቀራቸውና ለህግ አስፈፃሚውም እክል መሆናቸው ነው ያሉት ሰለሞን ይህም ለህብረተሰቡ ፈታኝ እየሆነ መምጣቱን ጨምረው ገልፀዋል።
ቅጽ 2 ቁጥር 103 ጥቅምት 14 2013



