በነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክ የሚገኙ ሳር በል የዱር እንሰሳት የመጥፋት አደጋ ተጋርጦባቸዋል

0
1170

በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች እና በኦሮሚያ ክልል መሀከል የሚገኘው የነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክ ውስጥ ያሉ ሳር ተመጋቢ የዱር እንሰሳት በግጦሽ እጥረት ምክንያት በመጥፋት አደጋ ውስጥ መሆናቸው ታወቀ።

በፓርኩ ክልል ውስጥ የሚገኘው የጫሞ ሃይቅም በደለል ምክንያት በመጥፋት አደጋ ውስጥ ይገኛል። በአገራችን በየአመቱ የሚጥለው ዝናብ መጠኑ ባይጨምርም ክብደቱ እየጨማረ በመምጣቱ በጎርፍ ምክንያት እና ከአርባምንጭ ከተማ የሚፈሰው ገባር ወንዝ በሚያመጣው ቆሻሻ እና አፈር ሃይቁ በደለል ተሞልቷል ብለዋል የፓርኩ ኃላፊ አቶ ሽመልስ ዘገየ ለአዲስ ማለዳ። በዚህ ምክንያትም የአንድ ቀበሌ አርሶ አደሮች የሙዝ እርሻ በደለል ተውጧል በርካታ በሀይቁ ዙሪያ የሚኖሩ ገበሬዎች ደግሞ ለመፈናቀል ተገደዋል።

በፓርኩ ከሚገኘው 52 ነጥብ ሁለት ሜዳማ የግጦሽ መሬት 51 በመቶውን ማለትም ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ በፓርኩ ውስጥ ነዋሪ በሆኑ የምዕራብ ጉጂ ገላና ወረዳ ኤርጌንሳ ቀበሌ አርብቶ አደሮች በመቶ ሽሕ በሚቆጠሩ ከብቶቻቸው በመጋጡ በፓርኩ ያሉ የዱር እንሰሳት ህልውና አደጋ ውስጥ ወድቋል ብለዋል የፓርኩ ኃላፊ።

የነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክ 514 km2 ላይ ያረፈ ከአዲስ አበባ 507 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ በውስጡ 351 የአእዋፍ 16 የዓሳ እንዲሁም ከ91 በላይ አጥቢ እንሰሳትን የያዘ እና ጫሞ ሀይቅም ናይል ክሮኮዳይል የተባለ በኢትዮጲያ ብቻ የሚገኝ የአዞ ዝርያን በውስጡ ይዟል። ፓርኩ በደቡብ ክልል ካሉ የሚጎበኙ ቦታወች ከሀዋሳ ቀጥሎ በአመት ከ 41 ሺሕ በላይ ጎብኝዎችን በማስተናገድ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

በፓርኩ የሚገኙ የዱር እንሰሳት የሜዳ አህያ የሜዳ ፍየል እንዲሁም የመሳሰሉት ከስማቸው መነሳት እንደሚቻለው ሜዳማ በሆነ ስፍራ ውስጥ ብቻ መኖር የሚችሉ በመሆናቸው እና አሁን የፓርኩ ሜዳማ ስፍራ በከብቶች ግጦሽ ምክንያት በመውደም ላይ ስለሚገኝ እና ሳራማ አካሉ ወደ ቁጥቋጧማ ስፍራ እየተቀየረ በመጤ አረም እየተወረረ ስለመጣ የዱር እንሰሳቱ መኖር የሚችሉት ሳራማ እንጂ ቁጥቋጧማ ስፍራ ውስጥ ባለመሆኑ ህልውናቸው አደጋ ላይ መውደቁን ሽመልሽ አስታውቀዋል።

ከ2010 በኋላ ማህበረሰቡን መሰረት ያደረገ ህግ የማስከበር ስራ በመስራት ፓርኩ ህገወጥ አደንን ሙሉ በሙሉ ያስቆመ ሲሆን በፓርኩ ውስጥም ሆነ በፓርኩ ዙሪያ ያሉ አርብቶ አደሮች በከፊል አርሶ አደር ሆነው የፓርኩን ክልል ለእርሻ መሬት እንዳይጠቀሙ እየሰራን ነው ብለዋል።ነጭ ሳር ብሄራዊ ፓርክ ውስጥ አንድ ቀበሌ ያሀል አርብቶ አደሮች እንዳሉ ገልፀው እነዚህ ነዋሪወች ፓርኩ ከተመሰረተበት ጊዜ 1967 ጀምረ የሚኖሩ እንጂ አዲስ ሰፋሪዎች አይደሉም ነገር ግን የእነዚህ አርብቶ አደሮች በመቶ ሸሕ የሚቆጠሩ ከብቶች በፓርኩ ውስጥ ስለሚገኙ በፓርኩ ያለውን ሜዳማ የግጦሽ ስፍራ በመጋጣቸው በፓርኩ ያሉ ሳር በል የሆኑ የዱር እንሰሳት አሁን በመጥፋት አደጋ ውስጥ ናቸው ብለዋል ሽመልስ ለአዲስ ማለዳ።

አክለውም በኮሮና ምክንያት ምንም አይነት ጎብኝ ባልነበረበት ወቅት በአካባቢው ለሚኖሩ እና ከጉብኝት በሚገኝ ገቢ ኑሯቸውን መሰረት ላደረጉ ሰዎች ከተባበሩት መንግስታት የሳይንስ እና የባህል ተቋም ’UNSCO’ እና በአካባቢው ከሚገኙ ባለሀብቶች ከተገኘ ገንዘብ ድጋፍ እንዳደረጉ ተናግረው አሁን ግን የባህል እና ቱሪዝም ሚኒስተር ኮሮናን ተካላክለን ቱሪዝምን እናስቀጥል የሚል መመሪያ ካወጣበት መስከረም 13 ቀን ጀምሮ 15 ሸሕ ጎብኝዎችን አስተናግደናል ሲሉ ነው የተናገሩት የፓርኩ ኃላፊ።

በአገራችን 27 ብሄራዊ ፓርኮች ይገኛሉ ከእነዚህ ፓርኮች መካከል 13 ያህሉ በፌድራል ደረጃ ሲተዳደሩ 14ቱን ደግሞ ክልሎች በሞግዚትነት ተረክበው እያስተዳደሯቸው ይገኛሉ።ነጭ ሳር ብሄራዊ ፓርክም ከ 2001 ጀምሮ በፌድራል መንግስት ስር መተዳደር መጀመሩ የሚታወስ ነው።

ፓርኮች ከሰው ንኪኪ ነፃ ባለመሆናቸው ምክንያት በፓርኮች ላይ የተለያዩ አደጋወች ይከሰታሉ።ከብቶች ለግጦሽ ወደ ፓርኮች ክልል ይገባሉ የእንጨት ማር በመፈለግ ሰወች እሳት በመያዝ ወደ ፓርኮች ይገባሉ በዚህ ሳቢያ እና በተፈጥሮ መንገድ ፓርኮች ላይ የቃጠሎ አደጋ ሊከሰት ይችላል። ህገ ወጥ እርሻ እና ህገወጥ አደንን ጨምሮ ሌሎች አደጋወች በፓርኮች ላይ ይከሰታሉ እነዚህ ችግሮች ሳይከሰቱ ለመካላከል በተለይ ደግሞ በሰሜን እና በቃፍታ ሽራሮ ብሄራዊ ፓርኮች ተከስቶ እንደነበረው አይነት የእሳት አደጋ ድጋሚ እንዳይፈጠር ለአካባቢው ማህበረሰብ ስልጠና እንደተሰጠ አቶ ጌትነት ይግዛው የኢትዮጲያ የዱር እንሰሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 103 ጥቅምት 14 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here