ለውጭ አገር ተጓዦች የኮቪድ-19 ምርመራ ሰርተፍኬት የሚሰጡ ተቋማት ወደ 7 አደጉ

0
709

ከኢትዮጵያ ወደ ውጭ አገራት ለሚጓዙ ተጓዦች የኮቪድ-19 ምርመራ ውጤት ሰርተፍኬት የሚሰጡ የጤና ተቋማት ወደ ሰባት ማደጋቸው ታወቀ።
ዓለም አቀፍ ተጓዦች የኮቪድ-19 የምርመራ ውጤት ከጤና ተቋም ማረጋገጫ እንዲያቀርቡ በመጠየቃቸው ከኢትዮጵያ ወደ ሌሎች ውጭ አገራት ለሚጓዙ ተጓዦች በኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ፈቃድ ከተሰጣቸው ተቋማት የምርመራ ውጤት ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል። በመሆኑም ከኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከዚህ ቀደም ፈቃድ ወስደው ሲሰሩ የነበሩ ኢንተርናሽናል ክሊኒካል ላብራቶሪስ እና ኢንተርናሽናል ኦርጋናይዜሽን ፎር ማይግሬሽን በተጨማ ለአዲስ አምስት የጤና ተቋማ ፈቃድ መስጠቱን የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል።

ወደ ውጭ አገር ለሚጓዙ መንገደኞች የኮቪድ-19 ምርመራ ውጤት ሰርተፍኬት እንዲሰጡ አዲስ ፈቃድ የተሰጣቸው የጤና ተቋማት ዉዳሴ ዲያግኖሲስ ስንተር፣ አሜሪካ ሜዲካል ሴንተር፣ ቤተዛታ ሆስፒታል፣ አሚን ጀነራል ሆስፒታልና ሲንክሮድ ሆስፒታል መሆናቸውን በኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስትቲቱ የላብራቶሪ ክፍል አስተባባሪ ይማም ጌታነህ ለአዲስ ማለዳ አረጋግጠዋል።

ተቋማቱ የምርመራ ፈቃድ የተሰጣቸው በኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዮት ሙሉ የቴክኒክ ምዘና ተደርጎ መሆኑን የኢንስቲትዩቱ የላብራቶሪ ክፍል አስተባባሪ ጠቁመዋል። የቴክኒክ ምዘና ዋና ዋና መስፈርቶች የተቋማቱ የመመርመሪያ ማሽን አቅም፣ ዘመናዊና በዲጂታል የተደገፉ አሰራር፣ ብቁ የሰው ሀብት መሟላት፣ ምርመራውን ለማካሄድ አስፈላጊ ግብዓቶች መሟላታቸውን መሰረት በማድረግ የኮቪድ-19 ምርመራ ማከናወን እና ሰርተፍኬት መስጠቱን አስተባባሪው አመላክተዋል።

የተቋማቱ አሰራር ትክክለኛነት ቁጥጥር እንደሚደረግበት የጠቆሙት አስተባባሪው ፈቃድ ተሰጣቸው የጤና ተቋማት ለተጓዦች የሰጡት የምርመራ ውጤት በሌላ ላብራቶሪ ትክክለኛነቱ አንደሚመዘን አመላክተዋል። በዚህም ተቋማቱ ለተጓዦች የሚሰጡት የምርመራ ሰርተፍኬት ውጤት በጥብቅ ቁጥጥር እንደሚደረግበት ነው አስተባባሪው የገለጹት። የተቋማቱ አሰራርና ውጤት ጥራት የሚመዘንበት ጠንካራ አሰራር ስርዓት መኖሩም ተመላክቷል።

የምርመራ ክፍያን በተመለከተ ፈቃድ የተሰጣቸው ተቋማት መንግስት ባስቀመጠው የክፍያ መጠን እንዲያስከፍሉ መመሪያ መሰጠቱን ተናግረዋል። ነገር ግን አንደ ይማም ገለጻ ተቋማቱ መንግስት ያስቀመጠቀውን የክፍያ እርከን ተግባራዊ ያድርጉ አያድርጉ ተጨማሪ ክትትል የሚያስፈልግ ጉዳይ ነው ብለዋል። መንግስት ያስቀመጠው የክፍዩ መጠን 1200 ብር መሆኑን ይማም ተናግረዋል።

የኮቪድ-19 ምርመራ ለማከናወን እና የምርመራ ውጤት ሰርተፍኬት ለመስጠት ፈቃድ አንዲሰጣቸው ጥያቄ ያቀረቡ ተቋማት 22 መሆናቸውን የገለጹት ይማም፣ በኢትዮጵያ ህብረተብ ጤና ኢንስቲትዩት የቴክኒክ ምዘና መስፈርቱን ያላሟሉ ተቋማት ፈቃድ እንዳልተሰጣቸውን ጠቁመዋል።

በኢንስትቲቱ የቴክኒክ ምዘና የብቃት ማረጋጋጫ መስፈርቱን ያሟሉ ተቋማት በኮቪድ-19 ምርመራ ላይ የሚሰማሩ ሰራተኞቻቸውን በኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ለኹለት ሳምንት ስልጠና መውስድ እንደሚኖርባቸው ይማም ተናግረዋል።

ፈቃድ የወሰዱት ተቋማት በተሻለ የመመርመር አቅም ወደ ሥራ ሲገቡ የተጓዦችን የምርምራ ውጤት መዘግየት እንደሚያሻሽለው አስተባባሪው ጠቁመዋል። ከአንድ ሳምንት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ በተሻለ ሁኔታ የኮቪድ-19 ምርመራ ውጤት የሰርተፍኬት መስጠት ሥራው በተሻለ አቅም ጥራት ያለው አገልገሎት እንደሚሰጥ ይማም አመላክተዋል።

ጤና ሚኒስቴር በኢትዮጵያ ኮቪድ-19 ከተከሰተ መጋቢት 2012 ጀምሮ እስካሁን ድረስ የምርመራ ስራዎች የመመርመር አቅሙን ከአስር ሺሕ በላይ አድርሶ የነበረ ቢሆንም አሁን ላይ በአንድ ቀን የሚመረመረው ሰው ብዛት በአብዛኛው ከአስር ሽሕ በታች እየወረደ ነው። የምርመራ ስራው ቢቀዛቀዝም የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በኢትዮጵያ እንዳልቀነሰ እና እንደውም እየጨመረ መሆኑን የጤና ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

ቅጽ 2 ቁጥር 104 ጥቅምት 21 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here