የኦሞ ብሔራዊ ፓርክ ከይዞታው 40 በመቶ ያህሉ እንደተወሰደበት አስታወቀ

0
1472

ተጨማሪ ይዞታዎቹም በሌላ ፕሮጀክት ተይዘዋል

በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት ስር የሚገኘው የኦሞ ብሔራዊ ፓርክ ይዞታ 40 በመቶ ያህሉ በኦሞ ኩራዝ ቁጥር ሦስት የስኳር ልማት ፕሮጀክት እንደተወሰደበት ገለጸ።

ከአራቱ የኦሞ ስኳር ፕሮጀክቶች መካከል በፓርኩ ከልል ውሰጥ የሚገኘው የኦሞ ቁጥር ሦስት የስኳር ፕሮጄክት ሲሆን፤ ይህም የፓርኩን 40 በመቶ ያህሉን ቦታ እንደወሰደ የዱር እንሰሳት ልማት እና ጥበቃ ባለስልጣን የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጌትነት ይግዛው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ከዚህም ጋር ተያይዞ ኦሞ ኩራዝ ቁጥር አምስት ፕሮጄክትም በፓርኩ ውስጥ ያለውን ጥብቅ ደን በመመንጠር ሸንኮራ አገዳ እንደዘራበትም አዲስ ማለዳ ከባለስልጣኑ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።

በኦሞ የስኳር ፕሮጀክቶች በ100 ሺሕ ሄክታር መሬት ላይ የሚለማ የሸንኮራ አገዳ ተጠቅመው በቀን 60 ሺሕ ቶን አገዳ የመፍጨት አቅም ያላቸው አራት ስኳር ፋብሪካዎች የተገነቡ ሲሆን በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል የኦሞ ወንዝን በሚዋሰኑ በካፋና ቤንች ማጂ ዞኖች የሚገኘው የኦሞ ኩራዝ ቁጥር ሦስት ስኳር ፋብሪካ ፕሮጄክት ደግሞ 293,600 ሄክታር ቦታ ከሚሸፍነው ከኦሞ ብሄራዊ ፓርክ ክልል ላይ 40 በመቶውን ከመውሰዱ በተጨማሪ ከኦሞ ወንዝ ተጠልፎ ለመስኖ በተቆፈረው የውሃ ቦይ ምክንያት እና በቁፋሮው ወቅት በተከማቸው ከፍተኛ መጠን ያለው አፈር ሳቢያ በፓርኩ የሚገኙ እንሰሳት ወድቀው የመሞት አለያም የመሰበር አደጋ እያጋጠማቸው እንደሆነም ጌትነት ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።

ቦዩ በፈጠረው የቦታ መከፋፈል ምክንያት ደግሞ እናት እና ልጅ የሆኑ በፓርኩ የሚገኙ እንሰሳትም ለመለያት ተገደዋል ብለዋል ጌትነት። በኢትዮጲያ የሚገኙት ሁሉም ፓርኮች በተለያየ ምክንያት ዳግም እየተከለሉ እንደሆነ እና በዳግም ክለላውም ከሰሜን ብሔራዊ ፓርክ ውጭ ሁሉም በሚባል ደረጃ የቆዳ ስፋታቸው እንደቀነሰ ለማወቅ ተችሏል።

ፓርኮች በሕገ ወጥ ሰፈራ በሕገ ወጥ እርሻ በፖለቲካ አለመረጋጋት ሲነሳ በሚፈጠሩ የከሰል ማክሰል እና ሌሎች ሕገወጥ ተግባራት ተሰማርተው ወደ ፓርኩ ክልል የገቡ ሰዎችን መልሶ ለማስወጣት የሚደረገው ሙከራ እጀግ ፈታኝ በመሆኑ ምክንያት ፓርኮች ስፋታቸውን ቀንሰው ዳግም እንደሚከለሉ ጌትነት ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

የኦሞ ብሔራዊ ፓርክን ክልል ለመወሰን በወጣ ደንብ ቁጥር 82/2003 መሰረት የፓርኩ ክልል 293,600 ሄክታር ቦታ እንደሚሸፍን ተቀምጧል።ፓርኩ በደቡብ ምዕራብ አቅጣጫ ከአዲስ አበባ 870 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ የጎብኚዎች መዳረሻም ነው። በዱር እንስሳት ልማት እና ጥበቃ ባለስልጣን አጠቃቀም አዋጅ ቁጥር 541/1999 መሠረት የኦሞ ብሔራዊ ፓርክ በፌደራል የዱር እንስሳት ጥበቃና ልማት ባለስልጣን አማካይነት የሚተዳደር የኦሞ ኩራዝ ስኳር ልማት ፕሮጀክት የአገር ጉዳይ ነው የፓርኩም ጉዳይም በተመሳሳይ የአገር ጉዳይ ስለሆነ አጣጥሞ መሥራት ያስፈልጋል ችግሩ የተከሰተው ካለመናበብ ነው ሲሉ ጌትነት ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

አሁን ላይ ከፓርኮች ልማት ጋር የተያያዘ ስራ መስራት እንዳቆሙ ገልፀው ስማቸው እንዳይነገር የፈለጉ ባለሙያ ደግሞ የኦሞ ስኳር ፕሮጀክት ክለላ በ2001 ሲካሄድ ፓርኩ ህጋዊ ይዞታውን ያላገኘ እንደነበር አስታሰው ከፓርኩ ደቡባዊ ክፍል 63 ሽሕ ሄክታር ከሰሜናዊው ከፍል ደግሞ 100 ሽሕ ሔክታር እንደወሰደ ነገር ግን ያኔ ቦታው የፓርኩ ህጋዊ አካል እንዳነበር እና እንስሳት ግን በዋናነት ይኖሩበት እንደነበር ገልፀዋል። ከአራቱ የኦሞ ኩራዝ ስኳር ልማት ፕሮጀክት መካከል ግን ቁጥር ሶሰት የተባለው ፋብሪካ የፓርኩ ክልል ውስጥ እንደሚገኝ አረጋግጠዋል።

ግለሰቡ አክለውም በብዙ የአፍሪካ አገራት በፓርኮች ውስጥም ሆነ አቅራቢያ የስኳር ፋብሪካዎች እንዳሉ አስታውቀው የእኛ ችግር ተናቦ አለመስራት ነው ብለዋል። አሁን ባለው ሁኔታ የፓርኩ እና የስኳር ፕሮጀክቱ ችግር በስምምነት እየተፈታ ያለ ጉደይ ነው በፓርኩ ያሉ እንደ ዝሆን ላሉ እንሰሳት መተላፊያ መራቢያ መመገቢያ የሚሆኑ ስፍራዎች ተለይተዋል ይህ አንዱ መፍትሄ ሲሆን የኦሞ ብሔራዊ ፓርክን ወደ ደቡብ ሱዳን ድንበር የማስፋት ስራ ተሰርቷል ብለዋል።

ይንን ጉዳይ ለመጠየቅ የኢትዮጲያ ስኳር ኮርፖሬሽን የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ወደሆኑት ጋሻው አይችሉህም ስልክ የደወልን ቢሆንም በወቅቱ ለስራ ጉዳይ አዳማ መሆናቸውን ገልፀው መረጃው የቁጥር በመሆኑ ጊዜ ወስደው በሚቀጥለው ሳምንት እንደሚመልሱ ቃል ገብተዋል። በዚህም መሰረት ከስኳር ኮርፖሬሽን የተገኘውን ምላሽም ይዘን እንደምንቀርብ ከወዲሁ እናስታውቃለን።

ቅጽ 2 ቁጥር 104 ጥቅምት 21 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here