የሰው ልጅ ከተሰጡት ተፈጥሮዓዊ ችሮታዎች አንዱ በነጻነት የማሰብ መብቱ ነው። ይህ መብቱ ዛሬ ያገኘው ሳይሆን ገና ወደዚህ ምድር ሲመጣ ከፈጣሪው የተቀበለው ነጻ ሰጦታው ነው ።ይሁንና ይህን ነጻ ስጦታው እንዴት ባለ አውድ ቢጠቀመው እንደ ሕዝብ ሆነ እንደ አገር ይበጃል ሲባል ማዕቀፍ ይበጅለታል።ሲልም የአገሪቱ መተዳደሪያ ሕገ መንግስት አልያም የመንግስት ሕግ ሆኖ ይቀመጣል። ይኸው የሕግ ማዕቀፍ ሁሉም በእኩል ደረጃ የሚገዙለት እሱም ሁሉን በእኩል አይን የሚዳኝ ይሆናል።
ይሁንና ይህ የሁሉ የግል ጠባቂ ሚና ያለው የሕግ ማዕቀፍ አንዳንድ ጊዜ ሁሉን በእኩል አይን ማየት ሲያቅተው ሕዝቦችን ላልተገባ መከፋትና አልፎ ተርፎም ቁጡ ወደመሆን ያደርሳል። ይህ ክስተት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገራችን መታየት ለመጀመሩ አንዳንድ አመላካቾች እንደታዩ አዲስ ማለዳ ትገነዘባለች።
በተለይም ሀሳብን በነጻነት የመግለጽና የመንገድ ላይ ተዕይንተ ሕዝብ ማካሄድ አንዳንድ ጊዜ የሚቻል አንዳንድ ጊዜ ደግሞ የማይቻል ሲሆንና ላለመቻሉም ሚዛን የሚደፋ ምላሽ ሳይገኝ ሲቀር የዜጎች መብት ሲሸራረፍ በዝምታም ታይቶ እንዳልታየ ሲታለፍ በሕዝቦች መሀከል ጥያቄ ማስነሳቱ አይቀሬ ጉዳይ ነው። ዜጎችን ባልተንሸዋረረ መነጽር በእኩል አያለሁ የሚለው ሕገ መንግስት የሀሳብ ነጻነትን አስመልክቶ በዐንቀጽ 29 እንዲህ በዝርዝር አስቀምጦታል
1ማንኛውም ሰው ያለማንም ሰው ጣልቃ ገብነት የመሰለውን ሀሳብ መያዝ ይችላል።
2ማንኛውም ሰው ያለማንም ጣልቃ ገብነት ሀሳቡን የመግለጽ ነጻነት አለው ይህ ነጻነት በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጭ ወሰን ሳይደረግበት በቃልም ሆነ በጽሁፍ ወይም በህትመት በሥነ ጥበብ መልክ ወይም በማንኛም በመረጠው አይነት መረጃና ሀሳብን የመሰብሰብ የመቀበልና የማሰራጨት መብት እንዳለው ይደነግጋል።
በዚህ አንቀጽ ዜጎች መብታቸውን በመጠቀም የህዝብና የአገርን ህልውና ለአደጋ እስካላጋለጡ ድረስ ሀሳባቸውን ለማንጸባረቅ ያላቸውን መብት የሚያሳይ ነው።ይሁንና ይህ ሀሳብን በነጻነት በቀዳሚነት ተጠቃሚ የሆነው የሚዲያው ማሕበረሰብ እየደረሰበት ያለው አፈና በዚህ የሚቀጥል ከሆነ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታው ከፊቱ ምን ሊጠብቀው እንደሚችል የሚያመላክት ነው ስትል አዲስ ማለዳ ትገነዘባለች። አሁን አሁን ጋዜጠኞች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ስራ ቦታቸው ድረስ በመሄድ በሲቪል ለባሽ የፖሊስ አባላት ለጥያቄ ትፈለጋለህ በማለት ብቻ ከኣራት ሰዓታት በላይ ያለተግባ እንግልት እንዲደርስባቸው ካደረጉ በኃላ ‹‹በስም ማጥፋት የተጠረጠሩ በመሆኑ ነው ስንፈልግዎት ሌላ ጊዜ የመጣሉ›› ማሰናበት ለዚያውም የጠፋው ስም የቱ እንደሆነና በየትኛው አጋጣሚ እንደጠፋ እንኳን በማይታወቅበት ኹኔታ ለሚፈጠረው እንግልት ተጠያቂው ማን ነው በሕገ መንግስቱ ላይ ፀድቆ የሚገኘው ሀሳብን በነጻነት የማንጸባረቅ መብት ወደ አፈና እየሄደ የሆን የሚል የሚያስነሳ ጉዳይ ስትል አዲስ ማለዳ ትታዘባለች።
በሌላ በኩልም ዜጎች የተሰማቸውን የድጋፍም ሆነ የተቃውሞ ሀሳብ የሚንጸባርቁበት ሕገ መንግስታዊ መብት አላቸው ።የህም በሕገ መንግስቱ ዐንቀጽ 30 ተቀምጧል ። ማንኛውም ሰው ከሌሎች ሰዎች ጋር በመሆን መሳሪያ ሳይዝ ሰላማዊ ሰልፍ ማከናወን እንደሚችል በዝርዝር ተቀምጦ እያለ መንግስትን ደግፈው ለወጡ የለሚኩራ ክፍለከተማ ነዋሪዎች እዲሁም በሱማሌ ክልል መዲና ጅግጅጋ ከተማ ተፈቅዶ እያለ በማንነቴ ጉዳት ደርሶብኛልና ድምጼን ላሰማ ለሚል አካል የመንገድ ላይ ትዕይንተ ሕዝብ ማድረግ የተከለከለ የሚሆነበት አሰራር በምን ሚዛን ታይቶ ነው የሚል ጥያቄ እንደሚያስነሳ አዲስ ማለዳ ታምናለች
ጥቅምት 18ቀን 2013 በአማራ ክልል ከተሞችና በአዲሰ አበባ ከተማ ዜጎች ድምጻቸውን ለማሰማት በአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ‹አብን›የተጠራ ቢሆንም በመንግስት አካላት እንዳይደረግ ታግዷል መባሉ በአንድ ቤት ኹለት አይነት ልጆች አሉን የሚል ጥያቄን የሚያስነሳ ያደርገዋል ።በእርግጥ በአንድ ቤት ኹለት አይነት ልጆች ሊኖሩ ይችላሉ ግን ኹለት አይነት አባት ሊኖራቸው አይችልም ‹‹እሰይ የኛመንግስት አበጀህ›› የሚለውን ድምጽ ከወደድን አረ የመንግስት ያለህ ለሚለው የዜጎች ጩኸት ጆሮ ዳባ ሊባል አይገባም። ነገር በልኩ ይሁን እንጂ አይን ያየውን ልብም መርምሮ ያጠናውን እውነት በደስታም ይሁን በሀዘን መንፈስ የሚገለጽ የዜጎች ድምጽ ማፈንና በተጽዕኖ ስር ማድረግ የፍትህ ሚዛኑ እኩል ቦታ ላይ አለመሆኑን ያሳያል ስትል አዲስ ማለዳ ትገነዘባለች ።
በአንድ ቤት ውስጥ ጥሩ ጥሩውን ብቻ የሚናገር ጎበዝ ድክመቶችና ችግሮችን የሚያመለክት ደግሞ ሟርተኛና ችግር ጠሪ ተደርጎ አይታይ የአባት ሚናው የልጆቹን ድምጽ በአግባቡ መስማት ነው የሚለው የአዲሰ ማለዳ ጽኑ አቋም ነው። የወደድነውን ብቻ ሳይሆን የጠላነውንም እንስማ ደስ ያለውን ብቻ ሳይሆን ያዘነውንም እናድምጥ ።ደስታችሁ አምጡ ሀዘናችሁን በሆዳችሁ ያዙት አንበል። ነገሮች በዚሁ ከቀጠሉ እና ደግ ደጉን ብቻ የመስማት ፍላጎት ካለን ለነቃሹ እና ነገ የተስተካከለ ቁመና እንዲኖረን ለሚያደርገው ደምጽም በራችንን መዝጋት ተገቢ አይደለም ስትል አዲስ ማለዳ አቋሟን ትገልጻለች።
ሕዝብ ወዶ እና ፈቅዶ ሳይሆን ተገዶ እና ጫናው ሲበዛበት ወደ አደባባይ እንደሚወጣ እና ፍረዱኝ ማለቱን ከመንግሥት በላይ ሊረዳው እና ሊያደምጠው የሚችል እንደሌለ የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ ከውዳሴው ውጭ ለመስማት አለመፍቀድ እና ብሶትን በአደባባይ እንዳይገለጽ መከልከል የበዛ ስህተት መሆኑ ሊታወቅ ይገባል። ሀሳብን በነጻነት መግለጽን መብት መንግሥት አፍኖ ቆይቷል ከእንግዲህ ወዲህ ግን ይህ ጉዳይ አይደገምም ሲባል በአደባባይ ሕዝብ የፈነደቀውን ያህል በተግባር ግን ለየቅል ሆኖ ሲገኝ ቀቢጸ ተስፋ እንደሚሆን እና የሕዝብን ሆድ እንደሚያሻክር ልብ ያለው ልብ ይበል።
ዕገዳው በበዛ ቁጥር ውስጥ ውስጡን የተዳፈነ እና እየቆየ የሚያመረቅዝ ቁስልን ከመፍጠር የዘለለ እና በኋላ ላይ ሊታከም ከማይችልበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ ማድረግ ትርፉ በመፍትሔ ዕጥረት ከመሰቃየት ውጭ ምንም ነው። ስለሆነም መንግሥት በሕጋዊው መንገድ ድምጻቸውን ለማሰማት የሚወጡትን ሰዎች ከማገድ ሕገ መንግሥታዊ ከለላ እንዲያደርግላቸው እንዲሁም በጋዜጠኞች ላይ የሚደርሰውን ወከባም እንዲያስቆም አዲስ ማለዳ ትጠይቃለች። በተለይም ደግሞ ከሰሞኑ በጋዜጣዋ ዋና አዘጋጅ ላይ የደረሰው ወከባ ጋዜጣዋን ጭራሹኑ እንዳትበገር የሚያደርግ እና ለዕውነት ከመቆም እንዲሁም ሕዝብን በቅንነት ከማገልገል እንደማያግዳት ሊታወቅ ይገባል።
ቅጽ 2 ቁጥር 104 ጥቅምት 21 2013


