የዘንድሮው የአሜረካን ፕሬዘዳንታዊ ምርጫ በሥልጣን ላይ በሚገኙት ሪፐብሊካኑ ዶናልድ ጄ ትራም እና የዴሞክራቲክ ፓርቲን እጩ ጆሴፍ አር ባይደን መካከል ከፍተኛ ፉክክርን እያስተናገደ ይገኛል። ፕሬዘዳንት ለመሆን ቢያንስ 270 ኤሎክቶሪያ ኮሌጅ ድምጽ ማስመዝገብ የሚጠበቅ ሲሆን እስካሁን ይፋ በተደረገው ድምጽ መሰረት ባይደን አሸናፊ ሊያደርጋቸው የሚችል አስራ ሰባት ኤሌክቶሪያል ኮሌጅ ድምጽ ሲጠባበቁ ባላንጣቸው ትራምፕ ደግሞ 57 ድምጽ ማግኘት ይጠበቅባቸዋል።
የፕሬዘዳንታዊው አሸናፊ ውጤት ሳይገለጽ ለቀናት የቀጠለ ሲሆን ከዚህ ቀደም ከተካሄዱት ምርጫዎች ከፍተኛ ፉክክር የታየበት መሆኑን ዓለማቀፍ መገናኛ ብዙኀን በመዘገብ ላይ ይገኛሉ።
በሳምንቱ ለኹለተኛ ጊዜ ኀሙስ፣ ጥቅምት 26 ምሽት ላይ ፕሬዘዳንት ትራም ከዚህ ቀደም ባልተለመደ ሁኔታ ለሰላሳ ደቂቃ የዘለቀ በንባብ ንግግር አድርገዋል። በንግራቸውም የፖለቲካ ጠላቴ ያሏቸው የምርጫውን ውጤት በማጭበርበር ለተቀናቃኛቸው መስጠታቸውን ማስረጃ ሳያቀርቡ ከስሰዋል። “የሕጋዊ መራጮች ድምጽን ከቆጠራችሁ አሸንፋለሁ፤ ሕገ ወጡን ድምጽ ከቆጣራችሁ ግን ምርጫውን እንደሰረቃችሁን እንቆጥረዋለን” ሲሉም ትራምፕ አስጠንቅቀዋል።
ባይደን በበኩላቸው ማክሰኞ ዕለት በሰጡት መግለጫ የአሜካኖች ድምጽ ይቆጠራል ሲሉ የትራምፕን የድምጽ ቆጠራ ይቋረጥልኝ ጥሪ በማጣጣል “በምርጫው አሸናፊነታችንን እያወጅኩ ሳይሆን አዝማሚያው ግን አሸናፊነታችንን ያረጋግጣል” ብለዋል።
የፕሬዘዳንታዊው ፍክክር ማዕከል አሪዞና፣ ኔቫዳ፣ ጆርጂያ፣ ፔንሲልቫኒያ እና ሰሜን ካሎራይና ግዛቶች ሲሆኑ የባይደን አሸናፊ መሆን ዕድል ሰፊ ቢሆንም ትራምፕ በእጃቸው የሚገኘውን ሥልጣን ለማስከበር ጨርሶ የተዳፈነ ባይሆንም ጠባብ ዕድል እንዳላቸው ተንታኞች ያስረዳሉ።
አዲስ ማለዳ ለኅትመት እስከገባችበት ጊዜ ድረስ ጆ ባይደን በ253 ኢሌክቶሪያል ኮሌጅ ድምጽ ሲመሩ ትራምፕ በ213 ድምጽ ይከተላሉ። ውጤቱ መገለጽ ከተጀመረበት ማክሰኞ ሌሊት ጀምሮ ሙሉ ለሙሉ በሚያስብል መልኩ ባይደን ፕሬዘዳንት ትራምፕን ከኋካ በማስከተል መርተዋል።
ቅጽ 2 ቁጥር 105 ጥቅምት 28 2013



