የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በያዝነው ዓመት ሰኔ ወር ላይ የመጀመሪያውን ዙር ሃይል ማመንጨት እንደሚጀም የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚንስትሩ ስለሺ በቀለ (ኢ/ር) አስታወቁ፡፡
ሚንስትሩ ዩሲኤል ከተሰኘ የዩናይት ኪንግደም ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎችና ተማሪዎች ጋር የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ ተወካይ በተገኙበት፤ ኢትዮጵያ በታዳሽ ሃይል ልማት ዘርፍ የምታከናውናቸውን ተግባራት በተመለከት ያላቸውን ልምድ አካፍለዋል፡፡
በኢትዮጵያ እና በምስራቅ አፍሪካ ሁለንተናዊ የኃይል አቅርቦትንና ሌሎች የእድገት ዓላማዎችን ለማሳካት የታዳሽ ኃይል ልማትን እንዴት ማፋጠን ይቻላል በሚል ሐሳብ ዙሪያ በቪዲዮ ኮንፈርንስ ተወያይተዋል፡፡
ሚንስትሩ ልምዳቸውን እንዲያጋሩ የተጋበዙት በዘርፉ ከ30 ዓመታት በላይ የስራ ልምድና ከፍተኛ የሆነ የትምህርት ዝግጅት ያላቸው በመሆኑ ነው ተብሏል፡፡
በተጨማሪም ኢትዮጵያ ታዳሽ ኃይልን ለማጎልበት የምትሰራው ስራ ለሌሎች ሃገራት ምሳሌ የሚሆን በመሆኑ የዩኒቨርሲቲው ተመራማሪዎችና ተማሪዎች ከዚህ ልምድ እንዲቀስሙ ለማስቻል እንደሆነም ነው የተገለጸው፡፡
ሚንስትሩም ኢትዮጰያውያን በመተባበር በራሳቸው ገንዘብ እየገነቡት የሚገኘው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ 5 ሺህ 150 ሜጋ ዋት ኃይል በማመንጨት ንጹህና ታዳሽ የሆነ የኤሌክትሪክ ሃይል ለዜጎች ለማቅረብ እንደሚያስችል ገልጸውላቸዋል፡፡
በተያዘው ዓመት ሰኔ ወር ላይም የመጀመሪያውን ዙር ኃይል ማመንጨት እንደሚጀምር አስታውቀዋል፡፡
በተጨማሪም ኢትዮጵያ ለራሷ ብቻ ሳይሆን ለምስራቅ አፍሪካ አገራት የንጹህና የታዳሽ ኃይል ምንጭ ቋት ለመሆን አቅዳ እየሰራች መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
ቅጽ 2 ቁጥር 108 ኅዳር 19 2013



