ኪነ ጥበብ የአገርን እድገት ለማፋጠን ብሎም የአገርን ችግር ለይቶ በማሳየት እንዲቀረፍ በማድረግ ረገድ ጉልህ ሚናን ከሚጫወቱ ዘርፎች ውስጥ አንዱ ነው። በኪነ ጥበብ የአንድ አገር ባህላዊ፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ስነ ልቦናዊና ፖለቲካዊ እሴቶች በስፋት ይዳሰሳሉ።
የአገራችን የኪነ ጥበብ ታሪክም እረጅም ዘመናትን ያስቆጠረ ሲሆን፤ በዘርፉም የተለያዩ እውቅ እና አንጋፋ ባለሙያዎች ፈርተውበታል፤ አሁንም ድረስ እየፈሩበትም ይገኛሉ።
ታዲያ ይህን ቀደምት የኪነ ጥበብ ዘርፍ ከማሳደግና ብቁ የሆኑ ባለሙያዎችን ከማፍራት አንፃር በአገራችን የሚገኙ ሲኒማና ትያትር ቤቶች የሚጨጫወቱት ሚና ይህ ነው የሚባል አይደለም። ብዙሃኑ የአገራችን ቀደምት የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችም በዘርፉ ላተረፉት አንቱታና ክብር መሰረቱ በቴአትር ቤቶች ውስጥ በቆዩባቸው ጊዜያት የቀሰሟቸው ሙያዊ ልምድ እና ስነ ሥርዓቶች መሆናቸውን ሲናገሩም ይስተዋላሉ።
እኛም በዛሬው የአዲስ ማለዳ ሕይወትና ጥበብ መሰናዶአችን በቅርቡ የ65ተኛ ዓመት የምስረታ ክብረ በዓሉን ለማክበር በዝግጅት ላይ የሚገኘውንና በአገራችን የኪነ ጥበብ እድገት ላይ የራሱን የሆነ ደማቅ አሻራ ያሳረፈውን፤ የቀድመሞውን ‹‹የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ›› የአሁኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ምስረታና የ65 ዓመታት ጥበባዊ ጉዞ በጥቂቱ ልናስዳስሳችሁ ወደድን መልካም ቆይታ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ምስረታ
ከ1928-1933 የጣሊያን ወረራ በኋላ አገራችን ኢትዮጵያ ከውጪ አገራት ጋር የነበራትን ግንኙነት በከፍተኛ ደረጃ የተጠናከረበት ወቅት ነበር። ማኅበረሰባችንም በሙዚቃ፣ በሲኒማ፣ በስዕላዊ መፅሄት እንዲሁም በሌሎች የተለያዩ ጥበባዊ መንገዶች የውጪዎቹን ባህል እና የአኗኗር ዘይቤ መልመድ የጀመረበት ጊዜም እንደነበር ቀደምት የታሪክ ድርሳናትና ፅሁፎች ያስረዳሉ።
ይህም የምራባዊያኑ ከፍተኛ የባህል ተፅዕኖ ያሳሰባቸው የወቅቱ የአገራችን ምሁራኖች አንድም ይህን ተፅእኖ ለመቋቋም፤ ብሎም ከአለም የኪነ ጥበብ እድገት ውስጥ ትምህርትን ለመቅሰም እንዲቻል፤ የአገራችንን የኪነ ጥበብ ዘርፍ ማሳደግና ዘመናዊ ማድረግ እንደሚገባ የተስማሙት ጉዳይ ነበር።
ከ1943 ጀምሮም የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ መንግሥት ብሔራዊ የአገር ፍቅርና የጀግንነት ስሜትን ለማጠናከር፤ ሙዚቃና ቴአትር ያላቸው አቅም ከፍተኛ መሆኑን በማመን በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ሥር የሙዚቃና የቴአትር ቡድን እንዲደራጅ አደረገ።
ይህም ቡድን ያቀርባቸው የነበሩ የሙዚቃና የትያትር መሰናዶዎች በሕዝቡ ዘንድ አድናቆት እና ተወዳጅነትን በማትረፋቸው እንዲሁም ትዕይንቶቹን ለመታደም የሚመጣው ተመልካች ቁጥርም በከፍተኛ ሁኔታ በመጨመሩ ምክንያት የማሳያ አዳራሹ እየጠበበ፤ ብዙ ተመልካችም ትርዒቶቹን ሳይመለከት ይመለስ ነበር።
በዚህም ምክንያት ተጨማሪ ዘመናዊ እና ሰፋ ያለ የማሳያ አዳራሽ በማስፈለጉ የአሁኑ የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት በተሠራበት ከአቡነ ጴጥሮስ ሀውልት ፊት ለፊት ከሚገኘው ሥፍራ ላይ አዳራሹ እንዲሰራ እቅድ ይወጣል።
ታዲያ በ1947 መገባደጃ ላይ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ 25ተኛ ዓመት የንግሥና የብር ኢዮቤልዩ በዓል በመድረሱና ለበዓሉም ድምቀት ሰፊና ዘመናዊ አዳራሽ በማስፈለጉ ይኸው አዳራሽ በአስቸካይ እንዲሰራ ትዕዛዝ ተላለፈ።
በወቅቱም አዲስ ቴአትር ቤት ለመገንባት ታስቦ የነበረ ቢሆንም ለክብረ በዓሉ የቀረው የአራት ወራት ጊዜ ብቻ በመሆኑ ሕንጻውን ገንብቶ ለማድረስ አዳጋች መሆኑ እርግጥ ሆነ። በዚህም ምክንያት ፋሺስት ኢጣሊያ በአገራችን በቆየበት ወቅት በመዲናችን አዲስ አበባ እንብርት ላይ ‹‹ቺኒማ ማርኮኒ›› በሚል ስያሜ ግንባታውን ጀምሮት የነበረውንና ከአገራችን ተባሮ ሲወጣ በግማሽ የቀረውን የሲኒማ ቤት አዳራሽ እንዲጠናቅ ሃሳብ ቀረበ። በቀረበውም ሐሳብ ላይ ውሳኔም በመተላለፉ ዘመናዊና ደረጃውን የጠበቀ ህንፃ ገንብቶ በአራት ወራት ውስጥ ለማጠናቀቅ ከፍተኛ ርብርብ ተጀመረ።
ግንባታውንም የአዲስ አበባ ማዘጋጃ በቤት በባለቤትነት እንዲያሰራው በመወሰኑ የማዘጋጃ ቤቱ የምህንድስና ክፍል ኃላፊ የነበሩት ሄነሪ ሾሜት ተሾሙ። ለግንባታው ተጫርተው አሸናፊ የሆኑት ‹‹ጣና ማኅበር›› የተባለው ተቋራጭ የሕንጻውን ግንባታ፤ ሌላው ‹‹ጄ ሳልሞን›› የተሰኘው ተቋራጭ ደግሞ የአደባዩን ሥራ እንዲሰሩ ተወስኖ ሥራው ተጀመረ። በማለት ቴአትር ቤቱ በየዓመቱ በሚያሳትምው ‹‹ሙያችን›› በተሰኘውና የቴአትር ቤቱን 60ኛ አመት ክብረ በዓል በማስመልከት በህዳር ወር 2008 ባወጣው መፅሄቱ ላይ አስነብቧል።
በመፅሄቱ ላይ እንደሰፈረውም በቴአትር ቤቱ አደባባይ ላይ ለቆመው ሃውልት እና በአዳራሹ መግቢያ ላይ ለቆሙት ስድስት ሃውልቶች ሥራ ጨረታ ተዘጋጅቶ ‹‹ሞሪስ ኮልካ›› የተባለ ተወዳዳሪ በማሸነፉ ሁሉም መሃንዲሶች የግንባታ ዲዛይናቸውን አስገምግመው በማስፀደቅ ወደ ወደ ሕንጻው ግንባታ ሥራ መግባታቸውን ያወሳል።
በዚህም መሠረት ‹‹ጄ ሳልሞን›› 200 ሠራተኞችን በማሰለፍ የሕንጻውን እና የውጪውን አደባባይ ሥራ ሲያከናውን የ‹‹ጣና ማኅበርም›› 750 ባለሙያዎችን በማሰማራት የውስጥ ድርጅት ሥራውን ያከናውን ቀጠለ።
የቅርፃ ቅርፅ ባለሙያው ‹‹ሞሪስ ካላካ›› በበኩሉ ከሙያ አጋር ባልደረቦቹ ጋር በመሆን፤ በአዳራሹ ዋና መግቢያ በር ላይ የሚታዩትን ስድስት ሃውልቶች ማለትም አራቱን እህትማማች ጥበባት ትራጄዲን፣ ኮሜዲን፣ ዳንስንና ሙዚቃን የሚመስሉ ቅርፆችን እንዲሁም በግራና ቀኝ የቆሙ ኹለት የእንስሳት ቅርፆችና የይሁዳ አንበሳን ሃውልት ሥራን ጀመሩ።
ጎን ለጎንም ቀደም ሲል የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ባለሙያዎች ለአዲሱ ቴአትር ቤት ብቁ ይሆኑ ዘንድ ከኦስትሪያ አሰልጣኝ እንዲመጣ ተደርጎ ‹‹ዳዊትና ኦሪዮን›› የተሰኘ በሙዚቃ የታጀበ ትያትርን ለበዓሉ ለማድረስ ልምዳቸውን አጠንክረው ይዘዋል።
በመጨረሻም በባለሙያዎቹ የተሰራው የቴአትር ቤቱ ሃውልት ጥቅምት 30 ቀን 1948 ከምሽቱ በ11፡00 ሰዓት በግርማዊ ንጉሰ ነገስት ቀዳማዊ አጼ ኃይለስላሴ የተመረቀ ሲሆን፤ በጊዜውም በሦስት ነጥብ አምስት ሚሊየን ብር ወጪ ግንባታው እንደተጠናቀቀ የሚነገርለት የቀድሞው ‹‹የቀዳማዊ ኃይለስላሴ›› የአሁኑ ‹‹የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር›› ህንፃ ህዳር 3 ቀን 1948 ከምሽቱ 2፡00 ሠዓት ተመርቆ ሥራውን በይፋ ጀመረ።
በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይም ከፈረንሳይ አገር በመጡ የባሌት አርቲስቶች ትርዒት የቀረበ ሲሆን ከማዘጋጃ ቤት ወደ አዲሱ ቴአትር ቤት በተዛወሩ አርቲስቶች እና የሙዚቃ ባለሙያዎችም የተሠራው ‹‹ዳዊትና ኦሪዮን›› የተሰኘው ተውኔት የቴአትር ቤቱ የመጀመሪያ ተውኔት ሆኖ ቀረበ። በዚህም የመክፈቻ ሥነስርዓት ላይ 1264 ተመልካቾች ተገኝተው ትርዒቱን መታደማቸውን ይገለፃል።
‹‹ዳዊትና ኦሪዮን›› የተሰኘውም ተውኔት በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስቴር በነበሩት በክቡር ቢትወደድ መኮንን እንዳልካቸው የተፃፈና በኦስትሪያዊው ፍራንሰስ ዘልቬከር የተዘጋጀ ሲሆን የማጀቢያ ሙዚቃውም በእኚሁ ኦስትሪያዊ ባለሙያ ተፅፎ እንደቀረበ በዚሁ ‹‹ከሙያችን›› በተሰኘውና በቴአትር ቤቱ የሕዝብና አለም አቀፍ ዳይሬክቶሬት ባተዘጋጀው የ2008 እትም መፅሄት ላይ ሰፍሮ ይገኛል።
የብሔራዊ ቴአትር 65 ዓመታት ጥበባዊ ጉዞ
ቴአትር ቤቱ ከተመሰረተና ‹‹ዳዊትና ኦሪዮን›› የተሰኘውን ትያትር ለሕዝብ በማቅረብ ሥራዉን ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስከ አሁን ድረስ ከ160 በላይ ተወዳጅ የመድረክ ሥራዎች በቴአትር ቤቱ የቀረቡ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ ከ1948-1952 ሥነ ስቅለት፣ አኒባል፣ ቴዎድሮስ፣ አስቴር፣ ሚስጥረ ቅዳሴ የተሰኙ ሥራዎች ቀርበዋል። እነዚህም ተውኔቶች በአመዛኙ ሃይማኖታዊና ታሪካዊ የይዘት ያላቸው እንደነበሩ ይገለፃል።
ከ1952 አንስቶም እስከ 1966 በቴአትር ቤቱ ይቀርቡ የነበሩ ተውኔቶችም ማህበረራዊ ጉዳይ ላይ ትኩረታቸው ያደረጉና ብቃት ባላቸውና የትያትር ትምህርትን በተከታተሉ ባለሙያዎች ይሰሩ የነበረ ሲሆን ይህ ጊዜ በቴአትር ቤቱ ወርቃማ ጊዜ ሊባል የሚችና እውቅና ሥመጥር ባለሙያዎችም የታዩበት ወቅት ነበር።
የፌዝ ዶክተር፣ አወናባጁ ደብተራ፣ በልግ፣ እቃ ብዬ መጣሁ፣ ሰማህ ማሞ እንዲሁም ኦቴሎ በፀጋዬ ገብረመድህን፤ ከተፎና መንጥር፣ ያስቀመጡት ወንደላጤ፣ ደና ሁኚ አራዳና ሌሎችም በጌታቸው ደባልቄ፤ የሺ፣ ላቀችና ድስቷ፣ አባትና ልጆች እንዲሁም ሌሎችም በተስፋዬ ገሠሠ ተደርሰው እና ተዘጋጅተው በወቅቱ የቀረቡ ሥራዎች ነበሩ። በእዚህም ወርቃማ ዘመን አንጋፋዎቹ ተዋንያን ተስፋዬ ሳህሉ፣ ሰላማዊት ገ/ሥላሴ፣ አውላቸው ደጀኔ፣ አስካለ አመነሸዋ፣ አስናቀች ወርቁ፣ ተስፋዬ ተሰማ፣ መአዛ ማሞ፣ ወጋየሁ ንጋቱ፣ ጀንበሬ በላይ፣፣ ደበበ እሸቱ እና ሌሎችም ድንቅ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች በመድረኩ ደምቀው ይታዩ ነበር።
በሙዚቃውም ዘርፉ አንጋፋና ብቁ የሆኑ ሙዚቀኞችን ያበረከተው ይሄው ቴአትር ቤት መርዓዊ ስጦታ፣ ተፈራ አቡነወልድ፣ ተስፋዬ ሳህሉ፣ ወዳጄነህ ፍልፍሉ፣ አፈወርቅ ሀ/ማርያም፣ ግርማ ደምሴ፣ ሚኒሊክ ወስናቸው፣ ፍቅረማርያም አየለ፣ ግርማ ነጋሽ፣ ጠለላ ከበደ፣ መልካሙ ተበጀ፣ ጌጡ አየለ፣ ፍቅርተ ደሳለቃ እና ሌሎችም በርካታ ቀደምትና ሥመጥር ባለሙያዎች ይሰሩበት እነደነበር ይገለፃል።
በአጠቃላይ ቴአትር ቤቱ በእስካሁኑ በ65 ዓመታት የኪነ ጥበብ ጉዞው ለቁጥር የሚታክቱ እልፍ የኪነጥበብ ባለሙያዎችን ያፈራና እንደ ሥሙ ብሔራዊ እውቅናን ያሰጠ የቀደምት ጠቢባን መናህሪያ ቤት ነበር።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ሲቋቋም ሙዚቃ፣ ትያትር፣ ፊልም፣ ሰርከስ፣ የቁንጅና ውድድርና ሌሎች ጥበባዊ ሥራዎችን ሁሉ አካቶ ይሰራ እንደ ነበር የሚናገረው የትያትር ቤቱ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ በፍቃዱ ከፈለኝ ነው። በፍቃዱ ለአዲስ ማለዳ እንደገለፀው በአሁኑ ሠአት ግን ክውን ጥበባት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ትያትርና ሙዚቃ ላይ ያጠነጠኑ ሥራዎችን ብቻ በቴአትር ቤቱ በመቅረብ ላይ እንደሚገኙ ይናገራል።
አርቲስት ወይንሸት በላቸው በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ከ1958 አንስቶ በጡረታ እስከ ተገለለችበት 1992 ድረስ ተወዛዎዥነት አንስቶ እስከ ተዋናይነት ድረስ ማገልገሏን ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራት ቆይታ ታወሳልች።
በቴአትር ቤቱ የተቀጠረችበትን አጋጣሚ ስታስታውስም ‹‹እኔ የድሬድዋ ልጅ ነኝ። ብሔራዊ ቴአትር ከመግባቴ በፊት ምንም አይነት የጥበብ እውቀቱም ችሎታዉም አልነበረኝም። ከቤተሰቦቼ ጋር ወደ አዲስ አበባ ከመጣሁ በኋላ ስድስት ተወዛዋዦች እንዲሁም አንድ ዘፋኝ ሆነን በ1958 ላይ ተፈልገንና ተመርጠን ወደ ቴአትር ቤቱ ገባን።›› በማለት አስታውሳ በጊዜውም ትልቅ የሚባለው የአንድ መቶ ብር ክፍያ የእነርሱ እንደነበር ትገልፃለች። ከእነርሱ በፊት የነበሩት ባለሙያዎችም ያን ያህል ይከፈላቸው እንዳልነበርም ትናገራለች።
በቴአትር ቤቱ ከተወዛዋዥት በቀጥታ ወደ ትያትር ሥራ እንደተዘዋወረች የምትናገረው አርቲስት ወይንሸት በትያትር ክፍሉም ሆና ውድቅት፣ የባለ አገር ፍቅር፣ ቀዝቃዛ እረመጥ፣ እንዲሁም ሀምሌት ላይ ደግሞ በተወዛዋዥነት የሠራች ሲሆን ከውጪ ደግሞ አስኳል፣ አንፋታም እና ሌሎች ተውኔቶች ላይ ተሳትፋለች። ከቴአትር ቤቱ በጡረታ ከተገለለች በኋላም እስከ አሁን ድረስ በበርካታ ፊልሞች ላይ በመሳተፍ ድንቅ ብቃቷን በማሳየት ላይ ትገኛለች።
ወይንሸት በጊዜውም በቴአትር ቤቱ የነበረውን የአርቲስቶች የሙያ ፍቅር እና ስሜት ስትገልፅ ‹‹የአሁኑና የበፊቱ ሁኔታ ሰማይና ምድር ነው። እኛ ሌላው ቀርቶ በፊት ለፊት እንኳን አንወጣም ነበር። ድብቆች ነበርን። ስንገባም በኋላ በኩል፣ ስንወጣም እንደዛው በኋላ በኩል ነበር።
አርቲስት አውላቸው ደጀኔ ነብሳቸውን ይማረውና እንደ ሙሽራ ነበር የሚያዩን። ሰው አያውቀንም እንደ አሁኑ ግልፅ አልነበርንም። በብሔራዊ ቴአትር መሰናዶ አለ ከተባለ….! እኛን ለማየት ሕዝቡ ሲገባ መስታወት ሁሉ ይሰበር ነበር። በጣም ፍቅር ነበረን።›› በማለት አስርት ዓመታትን የኋሊት በማስታወስ ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራት ቆይታ አጫውታናለች።
አዳፍኔ ብዙነህ ቀደም ባለው ጊዜ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ሥራ አስኪያጅ የነበረ ሲሆን በአሁኑ ወቅት የቴአትር ቤቱ የትያትር ቡድን መሪና የፕሮጀክቶች አስተባባሪ ነው። በተጨማሪም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር 65ተኛ ዓመት ክብረ በዓል ላይም የዝግጅቱ ስፖንሰርሽፕና አስተባባሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ በመሆን በመሥራት ላይም ይገኛል።
በቴአትር ቤቱ በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ከ15 ዓመት በላይ እንዳገለገለ የሚናገረው አዳፍኔ፤ እርሱ በቴአትር ቤቱ ከመግባቱ በፊት የነበረው ጊዜ እጅግ ወርቃማ የሚባለው ጊዜ እንደ ነበር ያስታውሳል። እርሱም በቴአትር ቤቱ ሥራ ከጀመረ ወዲህም በጣም የተወደዱና አድናቆትን ያተረፉ ሥራዎች እንደተሰሩም በመግለፅ የዛኑ ያህል ደግሞ ይሄ ነው የሚባል ሥራ ሳይሰራባቸው ያለፉ ዘመኖች እንደ ነበሩም ይናገራል።
የዛሬ 15 ዓመት የቴአትር ቤቱ 50ኛ ዓመት ሲከበር እንደተቀጠረና በክብረ በዓሉ ላይም እንደተሳተፈ የሚናገረው አዳፍኔ በዛን ወቅት እነ አለሙ ገብረአብ፣ ፍቃዱ ተክለማርያም፣ ጌትነት እንየው የነበሩበት ጊዜ እንደመሆኑ በጣም በከፍተኛ ሁኔታ ሥራዎች ይሠሩ የነበረበት ጊዜ እንደ ነበር ይገልፃል።
ቴአትር ቤቱ የባለሙያዎችን አቅም ከማጎልበት አንፃር
እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ብዙ አንቱ የተባሉ ባለሙያዎች የፈሩትበት አንጋፋ ቴአትር ቤት ነው። በአፍሪካ ውስጥም ካሉ ጥቂት የሚባሉ ቴአትር ቤቶችም የተሻለ ተመልካች፣ ባለሙያና አደረጃጀትም ያለው፤ በመንግሥት የሚደደገፍ ተቋም ነው። ታዲያ ይህ ተቋም የባለሙያዎችን የመሥራት አቅም ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሳደግ የሚሠራቸው ሥራዎች ይኖሩ ይሆን? ብለን ጥያቄን አነሳን።
‹‹በፊት እኮ በጀት የለውም ነበር! በሆታ ብዙ ሰው ተጋሎ ሰልፍ ወጥተን ነበር ባጀት የሚለቀቅልን›› የምትለው ወይንሸት ክፍያቸውም በኹለት አመት እና በሦስት ዓመት ትንሽ ትንሽ ጭማሪ ጣል ጣል የሚደረግበት እንደነበር ታስታውሳለች። አክላም ‹‹ነገር ግን›› ትላለች ‹‹ነገር ግን ፍቅር አለን። የሕዝብ ፍቅር እና የአለቃ ፍቅር ነበረን። ክፍያችንም እርሱ ነበር።›› ስትል ትገልፃለች።
ባለሙያዎችን ከማብቃት አንፀፃር ያለው እንቅስቃሴ በጣም ዝቅተኛ ነው። እንደውም ምንም የለም ማለት ይቻላል። የሚለው ደግሞ አዳፍኔ ነው። ‹‹ኪነ ጥበብ ማለት ንክኪ ያለው የቡድን ሥራ ነው። እውነትን፣ ውበትን ህይወትን የምንገልፅበት ጥበብ ነው። እነዚህ ሥራዎች ደግሞ ካልተካካህ፣ ትንፋሽ ለትንፋሽ ካልተገናኘህ፣ ሕይወትን እንዳለች በተጨባጭ መሳየት ካልቻልክ መስራት አትችልም። በዚህ ረገድ ኮቪድ 19 በእኛ አገር ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ላይ እያደረሰ ያለው ጉዳት የሚታወቅ ነው።
ከዚህ አንፃር ቀደም ብለን የተዘጋጀንበት ነገር ስላልነበረን፤ የኪነ ጥበብ ባለሙያውም ከጥበብ ሥራዉ ውጪ ሌላ ሥራ ሰርቶ ገቢ የሚያገኝበት ክህሎት ወይንም ችሎታም ስለሌለው ባለሙያው በጣም ተጎድቷል። ይሄ እንደ ትልቅ ችግር ነው። ከዛ ጎን ለጎን ደግሞ እንደ ተቋም በብሔራዊ ደረጃ እንደመስራታችንም ሆነ፤ በአለም አቀፍ ደረጃ ሥም ያለው ተቋም እንደመሆኑ የባለሙያዎችን አቅም የማጎልበት ሥራ በጣም በሚያሳዝን ሁኔታ አልተሠራም።
ማንም ሳይሆን እኛ እንደተቋም በውስጥ ያለን ሰዎች ይሄን ማድረግ አልቻልንም። ከቲያትር ክፍል ባለሙያዎች ይመረጣሉ፤ ምንም አይነት ስልጠናና የማብቃት ሥራ ሳይሰራባቸው ያረጃሉ ጡረታም ይወጣሉ። ሙዚቀኞችም አልፎ አልፎ ወደ ውጪ አገራት ሲሄዱ ከቀስሟቸው ትምህርቶችና እራሳቸውን ለማሳደግ በግል ከሚያደረጉት ጥረት ውጪ እንደ ተቋም በአለም አቀፋዊ ደረጃ አቅማቸውን ሊያጎብቱ የሚችሉ ሥራዎች አይሰሩም።
በሙዚቃ፣ በግጥም በኮንቴንፖራሪ ዳንስ፣ በትወና፣ በፕሮዳክሽን፣ በመድረክ ዲዛይን ቴክኖሎጂ፣ በመድረክ መብራት ኢንጂነሪንግ፣ በድምፅ ኢንጂነሪንግ ውስጥ ምንም የሚሰጥ የሙያ ማጎልቻ ስልጠና የለም።›› በማለት እልህ እና ቁጭት በተቀላቀለበት ስሜት ለአዲስ ማለዳ ያስረዳል።
የ65ተኛ ዓመት ክብረ በዓል መሰናዶዎች
65ተኛ ዓመት ክብረ በዓሉን ከትያትር ትርዒት ዳግመኛ መጀመር ጋር አጣምረን ማክበር አስበናል የሚለው በፍቃዱ የክብረ በዓሉ ቀን ህዳር ሦስት ቢያልፍም ቴአትር ቤቱ ግን በተለያዩ ዝግጅቶች እለቱን አስቦ ለማሳለፍ ማቀዱን ያናገራል።
ከእነዚህም ሥራዎች ውስጥ አንዱ የኤግዚቢሽን መርሃ ግብር ሲሆን በዚህም የአራት አርቲስቶች ሥራዎች እንደሚዘከሩና የሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን እንዲሁም የመንግሥቱ ለማ ‹‹አብዬ መንግሥቱ›› ሥራዎች ከትያትር ዘርፍ፤ በተጨማሪም ከሙዚቃዉ ደግሞ የነርሲስ ናልቫንዲያን እና መርዓዊ ስጦት ሥራዎች ተቀነጫጭበው በቪዲዮ እንደሚቀርቡም ለአዲስ ማለዳ አስረድቷል።
የአራቱንም አርቲስቶች ሥራዎች ያተካተ ብሮሸር እንደሚኖር የገለፀው በፍቃዱ በተጨማሪም የአራቱንም አርቲስቶች ሥራዎችን የሚያሳዩ ወደ 80 የሚጠጉ ፎቶዎች ኤግዚቢሽኑ ላይ እንደሚቀርቡ በመግለፅ ከዛ ባለፈ የሙዚቃ ክፍሉ የሚያቀርባቸው ሥራዎች እንደሚኖሩና የትያትር ክፍሉ ደግሞ ‹‹ጋሞ›› የተሰኘውን የሎሬት ፀጋዬ ገብረመድን ትያትርን ለማቅረብ እየሰራ እንደሚገን ተናግሯል።
‹‹የቴአትር ክፍሉ፣ የሙዚቃ ክፍሉ፣ የሕዝብ ግንኙነት ክፍሉም የሚሠራው ሥራ አለ።›› የሚለው ደግሞ አዳፍኔ ነው። ከዚህም በተጨማሪም በፕሮጀክቱ መሰረት፤ ተጋባዝ አርቲስቶችንና የተቋሙን ባለሙያዎች በመርሃ ግብሩ እንዲሳተፉ በማድረግ እንዲሁም በስፖንሰሮች በመደገፍ ወደ ሥራ እንዲመለሱ ለማድረግ መታሰቡንም ይናገራል።
‹‹በተጨማሪም›› ይላል አዳፍኔ ‹‹በተጨማሪም ከብሔራዊ ቴአትር በኃላፊነት ላይ የነበሩና ከኃላፊነታቸው የተነሱ ባለሙያዎች አብዛኞቹ በበረንዳው ላይ ማለፍ እንኳን አይፈልጉም። ይሄ በጣም ያሳዝናል። በሌላ በኩል በጣም የምንወዳቸው አርቲስቶች በጡረታ፣ በፍቃዳቸው እንዲሁም በተለያየ ምክንያቶች ከቴአትር ቤቱ ወጥተዋል። አብዛኞቹም ወደ ውጪ ተሰደዋል። ስለዚህ በየትኛውም ዘመን ላይ በቴአትር ቤቱ በሃላፊነት ሥፍራ ላይ የነበሩ ባለሙያዎችን እውቅና ለመስጠት አስበናል። በነበሩበት ዘመን አቅማቸው የሚፈቅደውን አስተዋፆ አድርገዋል፤ ስለዚህ እንደ ጠላት መታየት የለባቸውም። ይሄንን ነገር በእኛ ጊዜ መስበር ይገባናል።›› በማለት ከክብረ በአሉ ጋር ተያይዘው ሊከናወኑ ስለታሰቡ መሰናዶዎች ለአዲስ ማለዳ አስረድቷል።
‹‹ከኮቪድ 19 ጋር በተያያዘ በእለቱ በርካታ ታዳሚያን ሊመጡ ስለሚችሉ ከፍተኛ ጥንቃቄ እያደረግን ነው። የጤና ሚኒስቴር ባለሙያም ሥልጠና ሰጥተውናል። ማሟላት የሚገባንን ነገሮች እያሟላን እንገኛለን። የተወሰኑ የሚቀሩን ነገሮች አሉ እነርሱ እንደተሟሉ ዝግጅታችንን እናቀርባለን። ኤግዚሽኑና 65ተኛ ዓመት ክብረ በዓሉ ቀርቦ ሙሉ ለሙሉ ውጤታማ መሆኑ ሲረጋጣጥ፤ በዛውም ደግሞ ትያትሮቻችንን ማሳየት እንጀምራለን።›› በማለት በፍቃዱ ያስረዳል።
አዲሱ የኢትዮያ ብሔራዊ ትያትር ሕንጻ እና የቴአትር ቤቱ ቀጣይ ሥራዎች
በአሁኑ ሰዓት ያለው ነባሩ ሕንጻ ከተገነባ 65 ዓመት ሞልቶታል። በዚህም ቀደምት ሕንጻ ውስጥ በርካታ ቅርሶች የሚገኙ ሲሆን እንዚህን ቅርሶች እንዳበላሹና እንዳይጎድሉ ከመጠበቅ አንፃር ምን እየተሠራ ነው? በማለት አዲስ ማለዳ ላነሳችው ጥያቄ የቴአትር ቤቱ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ በፍቃዱ ከፈለኝ እንዲህ ይላል።
‹‹አሁን የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሙያዎች መጥተው ዶክመንቶችን ወስደዋል። የመለካት ሥራም ሰርተዋል በቅርቡ ሰርተፍኬት እንደሚሰጡን ይጠበቃል። የአዲሱ ሕንጻ ግንባታ ሲጀመር የቅርስነት ባህሪ ያላቸው ነገሮች እንዳይነኩ ከማሰብ አንፃር የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ኹለት ባለሙያዎችን መድቦልናል። ስለዚህ ግንባታው ሲጀመር እነዚህ ነገሮች እንዳይነኩ ታስቦበት ነው የተጀመረው። የቅርብ ክትትልም እየተደረገበት ነው›› ሲል ያስረዳል።
አዲሱ ሕንጻ ቴአትር ቤቱ ለበርካታ አመታት ሲጠይቀው የነበረና ምላሽ ያገኘ ጥያቄው ነው። ፕሮጀክቱ የአንድ ነጥብ አምስት ቢሊየን ብር ፕሮጀክት ሲሆን በሦስት አመታት ውስጥ ተገንብቶ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል። በእቅዱም መሰረት 1500 ሰዎችን ማስተናገድ የሚችል ትልቅ አዳራሽ የሚኖረው ሲሆን በተጨማሪም 600 ሰዎችን ማስተናገድ የሚችል ሌላ አዳራሽም ይኖረዋል። እንዲሁም በመገጣጠም ትናንሽ ክፍሎች የሚሆኑ ያንን በማንሳት ደግሞ ትላልቅ አዳራሾች ማድረግ የሚቻሉ ክፍሎችንም ያካተተ ነው። ጎን ለጎን የተለያዩ ልምምዶችና ስብሰባዎች የሚካሄዱበት ክፍሎች የሚኖሩት ዘመናዊ ሕንጻ ይሆናል ተብሎ ወደ ሥራ ተገብቷል። በቀጣይ አዲሱና ነባሩ ሕንጻዎች ጎን ለጎን አገልግልት እንዲሰጡ እንደሚደረግም በፍቃዱ ለአዲስ ማለዳ ገልጿል።
በተያዘው ፕሮግራም መሠረትም ታህሳስ ሰባት ትያትሮችን ማሳየት እንጀምራልን ብለን እቅድን ይዘናል የሚለው በፍቃዱ በዚህም ቀን የጥላሁን ዘውገ ‹‹የእኛ ሰፈር›› የተሰኘው ተውኔት እንደሚቀርብና ታህሳስ 11 ደግሞ ‹‹አልቃሽና ዘፋኝ›› ትያትር እንደሚታይ ገልፆ በቀጣይም ኮሮና ከጠፋ እንደ ከዚህ በፊቱ በሳምንት እስከ ስምንት ትያትሮች የሚታዩበት ደረጃ ላይ ይደርሳል ተብሎ ተስፋ እንደተደረገም ያስረዳል።
በቀጣይም የተለያዩ የማስታወቂያ ስራዎችን በመስራትና ተመልካች በቴአትር ቤቱ በር ላይ መሰለፍ ሳኖርበት የሚፈልገውን ትያትር እና ቀን መርጦ በ‹‹ኦን ላይን›› ትኬት ሽያጭ እንዲገዛ በማድረግ እንዲሁም ሌሎች የተለያዩ ስልቶችን በመጠቀም የተመልካቹን ቁጥር ወደ ቀድሞው ለመመለስ እየተሰራ መሆኑንም ጨምሮ ገልጿል።
ቅጽ 2 ቁጥር 108 ኅዳር 19 2013