በኢትዮጵያ የሚገኙ ኢንዱስትሪያል ፓርኮችን ሙሉ በሙሉ ወደ ግል ይዞታ ለማዘዋወር የተለያዩ ጥናቶች በመደረግ ላይ ናቸው ሲሉ የገንዘብ ሚኒስቴር ከፍተኛ የምጣኔ ሀብት አማካሪ ብሩክ ታዬ (ዶ/ር) ለአዲስ ማለዳ ተናገሩ።
በኢትዮጵያ 13 ያህል ኢንደስትሪያል ፓርኮች ያሉ ሲሆን ዐሥሩ በሥራ ላይ ሲሆኑ ኹለቱ በቅድመ ምስረታ አንዱ ደግሞ ግንባታው በመጠናቀቅ ላይ ነው። በእነዚህ ኢንደስትሪያል ፓርኮች 60 ሺሕ የሚደርሱ ሠራተኞች አሉ። አብዛኛዎቹ የኢንደስትሪ ፓርኮች በጨርቃጨርቅ ምርቶች ላይ የተሠማሩ መሆናቸውን የኢንደስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የሕዝብ ግንኙነት እና የማርኬቲንግ ኃላፊ የሆኑት በኃይሉ ከበደ ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።
ኢንደስትሪያል ፓርኮችን ወደ የግል ይዞታ ለማዘዋወር የቅድመ ፕራይቬታይዜሽን ሥራዎች ማለትም እንደ የቴክኒክ አማካሪ እና ወደ ግል ይዞታ የማዘዋወሩ ጉዳይ በምን መንገድ የበለጠ አዋጭ እንደሚሆን ጥናት የሚያጠና ድርጅት የመቅጠር ሥራዎች እየተሠሩ እንደሆነ ብሩክ (ዶ/ር) ገልጸዋል።
የኢንደስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽን ኢንድትሪያል ፓርኮችን ገንብቶ እና በውስጡ መካተት ያለባቸውን የባንክ የጉምሩክ እና ለሠራኞቹ አስፈላጊ የሆኑ የመገልገያ ስፍራዎችን ያሟላል። ከዚያም ለሦስተኛ ወገን በኪራይ የማስተላለፍ እና ከአካባቢ ብክለት ጋር በተያያዘ በምርት ወቅት የቆሻሻ አወጋገድ እና ሌሎች ቁጥጥሮችን ላለፉት አምስት ዓመታት እያደረገ ይገኛል ሲሉ በኃይሉ ተናግረዋል።
የኢንደስትሪ ፓርኮችንም ሆነ ሌሎች የልማት ተቋማትን ወደ የግል ይዞታ የማዘዋወርን ጥቅም ብሩክ (ዶ/ር) ሲያስረዱ እንደየ ተቋሙ ቢለያይም፤ ለምሳሌ እንኳን ብናነሳ በብድር ገንዘብ የተገነቡ ፓርኮች ብድራቸውን ለመመለስ ሳይችሉ ከቀሩ ወይንም ደግሞ ግንባታቸው ያላለቀ የኢንደስትሪ ፓርኮችን ግንባታ ለማጠናቀቅ ሌላው ደግሞ መንግሥት ከመነገድ ይልቅ ከፕራይቬታይዜሽኑ በሚገኘው ትርፍ እንደ መንገድ ውሃ መብራት የመሳሰሉ መሰረተ ልማቶችን ቢገነባ የተሻለ ነው ብለዋል።
ከዚህ በተጨማሪ መንግሥት ሲሠራቸው የነበሩ የንግድ ሥራዎችን ወደግሉ ዘርፍ በማዛወር ምርቶችን ወደ ውጭ አገራት የመላክ እና ከውጭ ወደ አገር ውስጥ የማስገባት ሥራዎች ላይ የሚወስደውን የተራዘመ አሠራር የግሉን ሴክተር በማሳተፍ አሠራሩ በተቀላጠፈ መንገድ እንዲከወን የራሱ አስተዋፆ አለው ሲሉ ተናግረዋል።
ብሩክ (ዶ/ር) አክለውም መንግሥት ካለበት የሥራ ጫና የተነሳ አሁን ወደ ግል ይዞታ የማዘዋወር ሂደት ላይ ያሉ የስኳር ፕሮጀክቶችን ወይንም ኢትዮ ቴሌኮምን ከሚቆጣጠር ይልቅ በከፊል ወይንም ሙሉ በሙሉ ወደ ግሉ ዘርፍ በማዞር በሚያገኘው ገንዘብ ወደ ሌሎች የልማት ሥራዎች ፊቱን ቢያዞር እና በከፊል ወይንም ሙሉ በሙሉ በግሉ ዘርፍ የሆኑትን ተቋማት በሕግ ማዕቀፍ ቢቆጣጠር የተሸለ ውጤት ማስመዝገብ ይችላል ብለዋል።
እንደ ከፍተኛ የኢኮኖሚ አማካሪው ማብራሪያ መንግሥት ወደ ግል የሚዛወሩትን የመንግሥት የልማት ድርጅቶች በጥንቃቄ አጥንቶ፣ ዋጋቸውን መዝኖ እና ተምኖ የአገሪቱን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም በሚያረጋግጥ መንገድ እየተገበረው ይገኛል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ፣ የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል፣ የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን 13 የስኳር ፋብሪካዎች፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን እና ሌሎችም በሙሉ እና በከፊል ለሽያጭ የቀረቡ ድርጅቶች እንደሆኑ ገልጸዋል።
ቦሌ ለሚ አዲስ አባባ ውስጥ የሚገኝ የመጀመርያው የኢንደስትሪ ፓርክ ሲሆን የሐዋሳ የኢንደስትሪ ፓርክ ደግሞ ኹለተኛው የኢንደስትሪ ፓርክ ነው።ፓርኩን የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ መመረቃቸው የሚታወስ ነው።በ 13ቱ የኢንደስሪያል ፓርኮች 89 ሺሕ ያህል ሠራተኞች የነበሩ ቢሆንም በኮሮና እና በሌሎች ምክንያቶች አሁን 60 ሺሕ ያህል ሠራተኞች ይገኛሉ ብለዋል።
ቅጽ 2 ቁጥር 109 ኅዳር 26 2013



