የስኳር ሕመምተኞች በመድኃኒት እጥረት እየተቸገሩ መሆኑ ተገለጸ

0
754

በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ የስኳር ሕመምተኞች ኢንሱሊን የተባለው መድሐኒት እጥረት በመከሰቱ ታማሚዎች በከፍተኛ ችግር ውስጥ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ስኳር ሕመምተኞች ማኅበር አስታወቀ።

በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ መከሰቱን ተከትሎ መድሐኒቶች በሚፈለገው መጠን ወደ አገር ውስጥ ባለመግባታቸው ላለፉት ኹለት ወራት የኢንሱሊን እጥረት በአገር ደረጃ በመከሰቱ ታማሚዎች የሚፈልጉትን አቅርቦት እያገኙ እንዳልሆነ የኢትዮጵያ ስኳር ሕመምተኞች ማኅበር ፕሬዝዳንት ዶክተር አብዱረዛቅ አህመድ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

እጥረቱ በስፋት ጎልቶ የሚታየው በግል ተቋማት መሆኑን የሚገልጹት ዶክተር አብዱረዛቅ በመንግሥት ተቋማቶች ችግሩ ቢኖርም የተጋነነ አይደለም ብለዋል። ፕሬዝዳንቱ ይህን ይበሉ እንጅ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የስኳር ሕመምተኛ በአዲስ አበባ በሦስት የከነማ መድሐኒት ቤቶች አቅንተው ኢንሱሊን ማግኘት አለመቻላቸውን ገልጸዋል።

በሦስት የከነማ መድሐኒት ቤቶች አቅንተው ኢንሱሊን የጠየቁ ሕመምተኛ እንደሚሉት መድሐኒት ቤቶቹ የሚቀርብላቸው የኢንሱሊን መጠን ከሚያስተናግዱት ሕመምተኛ ቁጥር አንጻር በእጅጉ ሊጣጣምላቸው አለመቻሉን እንዳስረዷቸው ተናግረዋል። ሕመምተኛው እንደገለጹት ካቀኑበት የመድሐኒት ቤት አገኘሁት ብለው ለአዲስ ማለዳ ያጋረቱ መረጃ እንደሚመላክተው በቀን እስከ 500 ሕመምተኛ ኢንሱሊን ለመግዛት በመድሐኒት ቤቱ እንደሚመጡ ተነግሮኛል ብለዋል። ነገር ግን ወደ መድሐኒት ቤት የሚያቀኑት የስኳር ሕመምተኞች መድሐኒቱን ማግኘት እንዳልቻሉ ተመላክቷል።

ፕሬዝዳንቱ እንደገለጹት አሁን ላይ የመድሐኒት እጥረቱ የተከሰተው የኮሮና ቫይረስ መከሰቱን ተከትሎ የዓለም አገራት እንቅስቃሴ ከመገታቱ የመነጨ መሆኑን ተናግረዋል። በተጨማሪም በአገሪቱ የተፈጠረው የዶላር እጥረት ሌላኛው የመድሐኒት አቅርቦት እንዲፈጠር ምክኒያት ነው ብለዋል ፕሬዝዳንቱ። ችግሩ ወደፊትም ተጽኖው ሊቀጥል እንደሚችል የማኅበሩ ፕሬዝዳንት ስጋታቸውን ገልጸዋል።

በመንግሥት መድሐኒት ቤቶች የኢንሱሊን አቅርቦት እጥረት በመፈጠሩ የስኳር ሕመምተኞች ወደ ግል መድሐኒት ቤቶች ለመግዛት አቅንተው በአንዳንድ መድሐኒት ቤቶች ቢገኙም እንኳን ዋጋው በእጅጉ የተጋነነ መሆኑ ተመላክቷል።

አዲስ ማለዳ በጉዳዩ ላይ የቀድሞ የኢትዮጵያ ስኳር ሕመም ማኅበር ፕሬዝደንት ምሥራቅ ታረቀኝን አነጋግራ ሁኔታው እጅግ አሳሳቢ መሆኑን ገልጸዋል። ምሥራቅ እንደሚሉት ባለፉት ኹለት ወራት እጥረቱ የተከሰተ ሲሆን ከአንድ ሳምንት ወዲህ ደግሞ እጥረቱ በመባባሱን እና ኢንሱሊን ያላቸው የግል መድሓኒት ቤቶች ዋጋውን በእጅጉ እንዳናሩት ማረጋገጣቸወን ተናግረዋል። በአንድ ሳምንት ውስጥ የአንድ ብልቃጥ ኢንሱሊን ዋጋ ከ250 ብር የ50 ብር ጭማሪ በማሳየጥ ወደ 300 ብር ማሻቀቡን ምሥራቅ ለአዲስ ማለዳ አረጋግጠዋል። የኢንሱሊን የዋጋ ንረት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሆኑን የገለጹት ምስራቅ ከኹለት ዓመታት በፊት የአንድ ብልቃጥ ኢንሱሊን ዋጋ 100 ብር እንደነበር አስታውሰዋል።

ምሥራቅ እንደሚሉት የማኀበሩ ፕሬዝዳንት በነበሩበት ጊዜ በስኳር ሕመም በኩል በርካታ ችግሮች እንደነበሩ አስታውሰዋል። ከነበሩት ችግሮች መሀከል ለበሽታው በጤና ሚኒስቴር በኩል የሚሰጠው ትኩረት በእጅጉ አናሳ እንደነበር አስታውሰዋል።

መንግሥት ችግሩን ተገንዝቦ አፈጣኝ ምላሽና ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም የማኅበሩ ፕሬዝዳንት ጠቁመዋል። የሕሙማን ማኅበሩ ዋና ሥራው ለሕሙማኖች ድምጽ መሆን ነው ተብሏል። በመሆኑም “ይሕ የጤናና የሕይወት ጉዳይ ነው ጊዜ አይሠጥም” ሲሉ ዶ/ር አብዱረዛቅ ገልጸዋል።

የቀድሞዋ የማኀበሩ ፕሬዝዳንት በበኩላቸው መንግሥት ችግሩን በትኩረት አይቶ አፋጣኝ መፍትሔ ካልሰጠ የብዙ ሕሙማን ሕይወት አደጋ ላይ ይወድቃል ብለዋል። ምሥራቅ የማኅበሩ ፕዴዝዳንት በነበሩበት ጊዜ የኢንሱሊን እጥረት በማጋጠሙ በርካቶች ሕይወታቸውን እንዳጡ አስታውሰዋል።

አሁንም ታማሚዎች መድሐኒቱን መግኘት ባለመቻላቸው ከተፈቀደላቸው ዶዝ በታች ቀንሰው በመጠቀማቸው ሕይወታቸው አደጋ ላይ ሊወድቅ ይችላል ብለዋል። ምሥራቅ ይሕን ያሉት ሰሞኑን በተፈጠረው የኢንሱሊን እጥረት የሚያውቋቸው የስኳር ታማሚዎች ጊዜው እንድራዘምላቸው በማሰብ ከተፈቀደው መጠን በታች እየተጠቀሙ መሆኑን በታዘባቸውን ተናግረዋል።

የማኅበሩ ፕሬዝዳንት ዶ/ር አብዱረዛቅ ችግሩን ለመፍታት ከሚመከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር እየተነጋገሩ መሆኑን የጠቆሙ ሲሆን ኢንሱሊን የሚያቀርቡ የግል ድርጅቶች መድሐኒቱን ወደ አገር እንዳስገቡ እየተነጋገርን ነው ብለዋል። የግል ድርጅቶች መድሐኒቱን በአንጭር ጊዜ ውስጥ ወደ አገር እንደሚስገቡ እንደነገሯቸው ፕሬዝዳንቱ ጠቁመዋል።

ኢንሱሊን በሰውነታችን በቆሽት አማካኝነት የሚመነጭና በደም ውስጥ የሚገኘውን የስኳር (ግሉኮስ) መጠን ለመቆጣጠር የሚያግዝ ንጥረ ነገር ነው። የስኳር በሽታ ያለባቸው ሰዎች ኢንሱሊን የተባለውን ኬሚካል ሰውነታቸው በአግባቡ ማምረት ወይም መጠቀም አይችልም።

አዲስ ማለዳ በጉዳዩ ላይ ከኢትዮጵያ ጤና ሚኒስቴርና መድሐኒት አቅራቢ ኤጀንሲ ምላሽ ለማግኘት በተደጋጋሚ ብትሞክርም ምላሽ ማግኘት አልቻለችም።

ቅጽ 2 ቁጥር 109 ኅዳር 26 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here