የእለት ዜና

የባህር ዳር ኢንዱስትሪ ፓርክ በመጪው መስከረም መጨረሻ ወደ ስራ ይገባል

በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በባህር ዳር ከተማ የሚገኘው የባህር ዳር ቁጥር አንድ ኢንዱስትሪ ፓርክ በመጪው መስከረም መጨረሻ 2012 ወደ ስራ እንደሚገባ ተገለፀ። የኢንዱሰትሪ ፓርኩ ዋና ስራ አስኪያጅ አማረ አስገዶም ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት ስምንት ሼዶች ያሉት የመጀመሪያው ምዕራፍ ሙሉ በሙሉ ‹‹ሆፕ ሉን›› በተባለ የሆንግ ኮንግ ኩባንያ መያዙንና በመጪው መስከረም መጨረሻም የማሽ ተከላ ሥራዎች ይጀመራሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አስታውቀዋል።

በቻይናው ኩባንያ ሲሲኢሲሲ የተገነባው ባህር ዳር ኢንዱስትሪ ፓርክ በጨርቃ ጨርቅና ልብስ ስፌት ዘርፍ የተሰማራውን የሆንክ ኮንግ ኩባንያ ለመቀበል አስፈላጊ ቅድመ ዝግጅት እያደረገ እንደሚገኝም አዲስ ማለዳ በስፍራው ተዘዋውራ ለመመልከት ችላለች። ሼዶችን በሙሉ የተከራየው ሆንግ ኮንግ ኩባንያ ሙሉ በሙሉ ወደ ስራ ሲገባ ለ6ሽሕ ሰራተኞች የስራ ዕድል ይፈጥራል ተብሎ እንደሚታሰብ ተገልጿል። በዋናነት ደግሞ በባህር ዳር ዩኒቨርስቲ ቴክስታይልና ፋሽን ዲዛይንት ትምህርት ቤት ለሚመረቁ ወጣቶች የስራ ትስስር እንደተፈጠረ ከወዲሁ ታውቋል።

የግንባታ ስራውን የሚያከናውነው ኩባንያ ሲሲኢሲሲ የባህር ዳር ኢንዱስትሪ ፓርክ ኃላፊ ሶንግ ዮንግ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት ከኩባንያው ጋር የተገባውን የጊዜ ውል መሰረት ተደርጎ ለማስረከብ ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ እንደሚገኝ አስታውቀው እስካሁንም የቆየበት ምክንያት ከውጭ ምንዛሪ እጥረት ጋር በተገናኘ እንደሆነ አስታውቀዋል። ሶንግ አያይዘውም በዚህ ስራ ላይ ያጋጠማቸውን ተግዳሮቶች ትምህርት በመውሰድ በቀጣይ ለሚካሔደው የማስፋፊያ ስራ በተሻለ የግንባታ ፍጥነት ለማስረከብ እንደሚተጉ ቃል ገብተዋል። የግንባታ ኩባንያው ሲሲኢሲሲ የባህር ዳር ኢንዱስትሪ ፓርክን ጨምሮ በአገሪቱ በበርካታ ክልሎች የሚገነቡትን የኢንዱስትሪ ፓርኮች በመገንባትና ላይ የሚገኝ እና ገንብቶም ያስረከበ የቻይናዊ የግንባታ ኩባንያ ነው።

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!