በአዲስ አበባ ባለ ኹለት እግር ተሽከርካሪዎች በቁጥጥር ሥር እየዋሉ ነው

0
652

የራሳቸውን ሰሌዳ ቁጥር ለጥፈው የሚንቀሳቀሱም ይገኙበታል

ማንኛውንም ባለ ኹለት እግር ተሽከርካሪ በሰዓት ከ40 እና ከዛ በላይ የሚጓዙ ያለ ሰሌዳ ቁጥር መንቀሳቀስ እንደማይችሉ በ2011 የወጣ መመሪያ እንዳለ እና አሁን ተሽከርካሪዎቹን በቁጥጥር ሥር እያዋሉ እንደሚገኙ የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።

በሞተር ብቻ የሚሠሩ ፣ በኤሌትሪክ ኃይል የሚሠሩት ፣ በጸሐይ ኃይል የሚሠሩ እንዲሁም በፔዳል የሚሠሩትን ተሽከርካሪዎች በጠቅላላ በቁጥጥር ላይ እያዋሉ እንዳለና ይህም አግባብነት ያለው የሕግ ማስከበር ሥራ ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ ስጦታው አካለ ለአዲስ ማለዳ አስታወቁ።

ባለ ኹለት እግር ተሽከርካሪን የሚቆጣጠር 2011 ላይ የወጣ መመሪያ እንዳለ እና እስከዛሬ ተግባራዊ እንዳልተደረገ አሁን ግን ተግባራዊ የማድረግ ሥራ እየተሠራ እንደሆነ በዚህም በቁጥጥር ሥር የማዋል ሥራ እየተሠራ እንዳለ የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ለአዲስ ማለዳ ጨምሮ ተናግሯል።

የሕግ ማስከበር ሥራው ከትራፊክ ማኔጅመንት ፣ ከፖሊስ ኮሚሽን እና የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ በጋራ በመሆን እንደሚሠሩም ኃላፊው ተናግረዋል።
በዋናነት እነዚህን ባለኹለት እግር ተሽከርካሪዎች የሰሌዳ ቁጥር የሌላቸው ብቻ ሳይሆኑ የራሳቸውን የኢፌደሪ መንግሥት የማያውቀውን የራሳቸውን ኮድ የያዘ የሰሌዳ ቁጥር ለጥፈው ሲንቀሳቀሱ የተገኙ እንደሆኑም አስረድተዋል።

የኢፌደሪ መንግሥት የማያውቀውን ሰሌዳ ቁጥር መስጠት ከባድ ወንጀል በመሆኑን እና፤ በዚህም ሁሉን ያለ ሰሌዳ የሚንቀሳቀሱ ባለኹለት እግር ተሽከርካሪዎች የመያዝ ሥራው እንደሚቀጥል እና ለሕግም እንደሚያቀርቧቸውም ተናግረዋል።

በተጨማሪም ሰሌዳ ቁጥር ሳይለጥፉ የሚንቀሳቀሱ ተሸከርካሪዎች ከከባድ እስከ ቀላል ወንጀሎችን የሚሠሩ እንዳሉ እናውቃለን ያሉት ኃላፊው የራሳቸውን ሰሌዳ መሥጠት ወንጀል መሥራት አመቺ ነው እኛ ለመቆጣጠር አዳጋች ይሆንብናል ብለዋል።

ለአብነትም አንድን ሰው ገጭተው ቢጠፉ ሰሌዳ ቁጥራቸው ስለማይታወቅ መያዝና ለሕግ ማቅረብ አንችልም ሲሉ ኃላፊው ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።
አዲስ ማለዳ በጉዳዩ ላይ ያነጋገረቻቸው የቶም ታዳሽ ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች አምራች ምክትል ሥራ አስኪያጅ በረከት ተስፋዬ እንዳሉት ከፌደራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን ኢትዮጵያ ውስጥ ሕግ ባለመኖሩ ምክንያት የቶም ታዳሽ ኤሌክትሪክ ብስክሌቶች ታርጋ ቁጥር ሳይለጥፉ መንቀሳቀስ ይችላሉ በሚንቀሳቀሱበት ጊዜ ተባበሯቸው የሚል ደብዳቤ እንዳላቸው ለአዲስ ማለዳ አሳውቀዋል።

ነገር ግን እኛ ከውጪ አገራት ተሞክሮ ወስደን የድርጅቱን የሰሌዳ ቁጥር እንሰጣለን ይህም ምን ያህል እንዳመረትን ፣ ለማን እንደሸጥን ፣ የትኛው ከየትኛው ቀድሞ እንደተመረተ ለመለየት እንዲያስችላቸው መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም እስከዛሬ ስንሥራ ምንም ተቃውሞ ሳይደርሰን እየሠራን ነበር አሁን ግን ምንም ምክንያትም ሆነ ሕግ መውጣቱ ሳይነገረን እንደዚህ አይነት እርምጃ መወሰዱ ተገቢ አይደለም ብለዋል።

ማንኛውንም ባለ ኹለት እግር ተሸከርካሪ ስንሸጥ ይህን ደብዳቤ አያይዘን ነው የምንሸጠው ይህ በሆነበት ሁኔታ ሳይነገረን ደንበኞቻችንን ማጉላላት አግባብነት የለውም ብለዋል።

ይህን በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሠራ ባለኹለት እግር ተሸከርካሪ ስናመርት ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት ኢትዮጵያ የምትፈልገው ነው ብለው እንደነበር ያስረዱት በረከት ከነዳጅ ቁጠባ ፣ አካባቢን ከካርቦን ልቀት ከመጠበቅ አንፃር ፣ ፍጥነታቸው ትንሽ ስለሆነ የትራፊክ አደጋን ከመቅፍ አንፃር ትልቅ ሚና እንዳላቸው አስረድተዋል።

በጣም አሳዛኝ ነገር እየተደረገ ነው። በድርጅታቸው ውስጥ 50 የሚሆኑ ሠራተኞች አሉን ለመንግሥትም ታክስ እንከፍላለን ቢያንስ ማስጠንቀቂያ ወይም አታምርቱ የሚል ነገር ሊደርሰን ይገባል፤ ይህ ባልሆነበት ሁኔታ ግን፤ እንደዚህ ዓይነት ድርጊት መፈፀሙ አግባብ አይደለም በማለት ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። አዲስ ማለዳ በጉዳዩ ላይ የፌደራል ትራንስፖርት ባለስልጣንን ለማግኘት በተደጋጋሚ ያደረገችው ሙከራ አልተሳካም።

ቅጽ 2 ቁጥር 110 ታህሳስ 3 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here