የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ
ኢትዮ ቴሌኮም በሰሜን ሪጅን የቴሌኮም አገልግሎት መስተጓጎል ተከትሎ አገልግሎቱን ለመመለስ እየሰራ ቢገኝም በትክክል ግን መቼ ሙሉ በሙሉ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር እንደማይታወቅ አስታወቀ።
የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ በቅርቡ በትግራይ ክልል በህወሓት ታጣቂዎች በተሰነዘረበት ጥቃት ለብልሽት በመዳረጉ ከወር በላይ ግንኙነት እንዲቋረጥ መደረጉን ተከትሎ ከኢትዮ ቴሌኮም መግለጫ ሰጥተዋል። በተሰጠውም ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ በሰሜን ሪጅን ያለውን የቴሌኮም አገልግሎት ሙሉ በሙሉ ወደ ስሥራ መቼ እንደሚመለስ አይታወቅም ያሉት ዋና ሥራ አስፈፃሚዋ በመቀሌ እና በሽሬ የሚገኙ የቴሌኮም ዋና ጣቢያዎች ያላቸውን አማራጭ የመገናኛ መስመሮች በሙሉ በመቋረጡ እንዲሁም የኮመርሻል ኃይል አቅርቦት በመቋረጡ የተከሰተ ችግር እንደሆነ ተናግረዋል።
በመግለጫው ላይ የቴሌኮም አገልግሎቱን ያቋረጠው መንግሥት እንዳልሆነ በኮር ሳይት ካሉ የደህንነት ካሜራዎች የተገኘውን መረጃ በመግለጫው ላይ ለተሳተፉት ጋዜጠኞች እንደ መረጃ ቀርቧል።
የደህንነት ካሜራው እንደሚያሳየው ሌሊት ስድስት ሰአት አካባቢ ላይ ከተቋሙ የጥበቃ አባላት ውጪ የሆኑ አካላት ወደ ሰሜን ሪጅን ጣቢያዎች በመሄድ የጥበቃ አባላቱን በመጀመሪያ ያነጋግሯቸዋል በመቀጠል የጥበቃ ሥራ ላይ የነበሩትን ሰዎች በመገፍተር በኃይል ወደ ውጪ እንዲወጡ ያደርጓቸዋል።
የትግራይ ክልል ልዩ ኃይል ልብስ ያደረጉ የታጠቁ ሰዎች ስፍራውን ይቆጣጠሩጣል በመቀጠል ሌሎች ሰዎች ገብተው የቴሌኮም አገልግሎቱን የማቋረጥ ድርጊት ሲፈፅሙ ካሜራው ያሳያል ጠዋት ላይ ወደ አካባቢው ሰራተኞች መጥተው በር ላይ ሲቆሙ መግባት አትችሉም ተብለው ሲመለሱ በደኅንነት ካሜራው ይታያል።
በዕለቱም የሰሜን ሪጅን ቴሌኮም አገልግሎት እንደተቋረጠ የሚጠቁም መረጃ በማእከሉ ከሚገኘው የኔትዎርክ መቆጣጠሪያ ሲስተም (National Network operation center) ከለሊቱ ስድስት ሰአት ከ37 ለሚመለከታቸው አካላት ማለትም ለቴክኒክ ቡድኑና ከፍተኛ አመራሩ መልዕክት እንደደረሰ ታውቋል።
በዚህም ከፍተኛ ቡድኑና የቴክኒክ ባለሙያዎች ወዲያውኑ በቢሮ በመገኛኘት የተከሰተውን ሁኔታ በማጤን በአገራዊ ኔትዎርክ ላይ ሊከሰት የሚችለውን አደጋ ለመከላከል የሚያስችል የጥንቃቄ እርምጃ ከመውሰድ ጀምሮ በሪጅኑ ያለውን የኔትወርክ ሁኔታ ለመፈተሽና አማራጭ መንገዶችን በመጠቀም አገልግሎቱን ለማስጀመር ከፍተኛ ጥረት እንደተደረገ ፍሬህይወት ተናግረዋል።
ከዚህ ጥረት ጎን ለጎን በሕገወጥ አካላት የኔትዎርክ ሲስተሞች ላይ ያለፈቃድ በመግባት ሊቃጡ የነበሩ ጥቃቶች (cyber attacks) እና የአገልግሎት መስተጓጎሎችን የማምከን ሥራዎችን አከናውኗል።
በዚህም ከቴሌኮም አገልግሎት ማቋረጥ በተጨማሪ በመንግሥት ሲስተሞችና ድረገጾች ፣ በትምህርት እና ፋይናንስ ተቋማት ሲስተሞች ፣ በብሮድካስት ሲስተሞች እና ጣቢያዎች እንዲሁም የቴሌኮም መሰረተ ልማት እና ሲስተሞች ላይ ያነጣጠረ እጅግ ሰፊ የሳይበር ጥቃት ሙከራ እየተካሐየደ እንደነበር አሳውቀዋለል።
እነዚህን የጥቃት ሙከራዎችን በማምከን በአገራችን ደህንነት እና ኢኮኖሚ ላይ ሊደርስ የነበረውን አደጋ መከላከል እንደተቻለ ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅትም በአካባቢው የተቋረጠውን የቴሌኮም አገልግሎት ለማስጀመር በርካታ ሥዎች እተሠሩ እንዳሉ አክለው ተናግረዋል በዚህም ዳንሻ ፣ ሁመራ ፣ ማይካድራ ፣ ማይፀብሪ ፣ ኮረም ፣በከፊል የቴሌኮም አገልግሎት መስጠት የጀመሩ ሲሆን አላማጣ ደግሞ ሙሉ በሙሉ የቴሌኮም አገልግሎቶች እንደተመለሱ ለማወቅ ተችሏል።
የሰሜን ሪጅን ቴሌኮም አገልግሎት መልሶ ለማስጀመር ዋና ተግዳሮት ከሆኑ ጉዳዮች መካከል የኀይል አቅርቦት መቋረጥ የቴሌኮም መሠረተ ልማቶች መቆራረጥ (የፋይበር ኬብሎች እና ከኀይል ማስተላለፊያ ጋር የተዘጋው መስመር (OPGW) ጨምሮ) በአካባቢው የሰው ኀይል ለማሰማራት አዳጋች መሆኑ እና ሌሎች አገልግሎቱን ለማስጀመር የሚያስችሉ መሠረታዊ አቅርቦቶች አለመኖሩ መሆኑን ተናግረዋል።
በሪጅኑ ያጋጠመውን ችግር ለመፍታት እና የቴሌኮም አገልግሎትን ሙሉ በሙሉ ለማስጀምር ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ከመንግሥት የፀጥታ አካላት እንዲሁም ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር በቅንጅት እየተሠራ እንደሆነም አስረድተዋል።
ቅጽ 2 ቁጥር 110 ታህሳስ 3 2013



