አዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት ቢሮ እና የአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ በጋራ በመሆን መንገድን ለተጠቃሚው ምቹ ከማድረግ አንፃር የመንገድ ደህንነት ኦዲት ማስተግበሪያ ሕግጋት እየተዘጋጀ መሆኑን አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው አዲስ አበባ የትራንስፖርት ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ ሀብታሙ ንጉሤ አስታወቁ።
የመንገድ ደህንነት ኦዲት ማስተግበሪያ ማለት መንገዶች ከዲዛይን ጀምሮ እስከሚጠናቀቅ ድረስ የመከታተል ሂደት ነው ያሉት ሀብታሙ እነዚህ ሕግጋት እንዲዘጋጁ የተፈለገው በዋነኝነት የመንገድ ተጠቃሚዎችን ደህንነት ለማረጋገጥ የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ ታስቦ እንደሆነ አሳውቀውናል።
ሕግጋቱ የሚያካትቱት አንደኛው የመንገዶችን ጥራትን ማረጋገጥ ሲሆን ኹለተኛ ደግሞ ተቋማዊነትን ማረጋገጥ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።
ተቋማዊነትን ማረጋገጥ ሲባል በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አንድ መንገድ ሲሠራ ሙሉ በሙሉ ከዲዛይን ጀምሮ እስከ መጠናቀቁ ድረስ የሚሰሩት በአንድ ተቋም ወይም በመንገዶች ባለሥልጣን እንደሆነ እና አሁን የሚዘጋጁት ሕግጋቶች ይህንንም ያሻሽላል ተብሎ ይታመናል።
ተቋማዊ ማድረግ ሲባል ደግሞ የመንገድ ደህንነት ማስተግበሪያ ኦዲት ከመንገዱ የመጀመሪያ ሥራ ጀምሮ ወይም ከእቅዱ ጀምሮ ያዋጣል አያዋጣም ምን ችግር ያመጣል ከሚለው አንስቶ ተቋማዊ መሆን አለበት ብሎ እንደሚያስቀምጥ መመሪያዎቹ እና ደንቦቹ ወይም ሕግጋቶቹ ሲወጡ ማን ምን ይሥራ የሚለውንም ምላሽ የሚሰጥ ይሆናል።
መንገድ ሲሠራ ዲዛይን ይደረጋል፣በግንባታ ሂደት ላይ እያለ ጥራት ቁጥጥር ይደረጋል፣ተሠርቶ ሲጠናቀቅ ለአገልግሎት ክፍት ከመሆኑ በፊት ኦዲት ይደረጋል ፣መንገዱ ተሰርቶ ካለቀ በኋላም አገልግሎት እየሠጠ እንዴት ነው አገልግሎት እየሠጠ ያለው በሚል የቅኝት ሥራ ይካሄዳል፣ ይህን ሁሉ ታዲያ ሢደረግ በአንድ ተቋም ብቻ መሆኑ እንደሌለበት የሚያሳይ ነው ብለዋል።
ሕግጋቶቹን በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ ኢንስቲትዩት ኦፍ ቴክኖሎጂ በኩል እንደሚሠራ እና ለሥራውም ኹለት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ብር እንደተመደበለት ለማወቅ ችለናል።እነዚህንም ሕግጋቶች ሠርቶ ለማጠናቀቅ አምስት ወር ጊዜ እንደሚፈጅ እና ከአ ምስት ወር በኋላ ተጠናቆ ለአዲስ አበባ ለትራንስፖርት ቢሮ እንደሚያስገባ አዲስ ማለዳ ለማወቅ ችላለች።
በአሁኑ ሰዓት በአብዛኛው በከተማው ያሉ መንገዶች ለተሸከርካሪ ብቻ ወይም አሽከርካሪ ታሳቢ ያደረጉ መንገዶች እንደሆኑ ተናግረው ወደፊት የሚገነቡ መንገዶች እግረኛውን አካል ጉዳተኛውን የብስክሌት አሽከርካሪውን መኪና የሚነዳውን ታሳቢ ያደረጉ መንገዶች መሥራት እንዳለባቸውም ጭምር የሚያሳይ ነው።
መንገዶች ባለሥልጣን ከገንዘብ አንፃር አቅም የለውም እራሱ ዲዛይን ያደረገውን መንገድ እራሱ አረጋግጦ ጥራቱን እራሱ ኦዲት አድርጎ በራሱ ብቻ ሲሠራ የጥራት ጉዳይም ጥያቄ ውስጥ ሊገባ ይችላል ስለዚህም የዚህ ሕግጋት መውጣት አስፈላጊ ነው ተብሏል።
ሕግጋቶቹ በትኩረት አዳዲስ የሚሠሩት መንገዶች ላይ ተግባራዊ እንደሚደርግ በተለይም ምንምን አካተው መሠራት እንዳለባቸው እና የቆዩትንም መንገዶች እንደሚመለከት አስታውቀቃል።
ይህ ሕግጋት ተሰርቶ ሲልቅ የትራፊክ አደጋን ሚቀንስ፣በዋነኝነት የመንገዱን ተጠቃሚዎችን ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል እንደሚጠቅም እና በተለይ የመንገድ ተጠቃሚዎችን ደህንነት የሚያረጋግጥ እንደሚሆንም ታውቋል።
ለአብነትም ከጀሞ ሀይሌ ጋርመንት ድረስ ያለው፤ ከጀርምን በቄራ አዲስ የሚሠራው መንገድ የመንገድ ተጠቃሚዎችን ደህንነት ያረጋገጠ ተደርጎ እንደተሠራም እንደሆነ አዲሰ ማለዳ ለማወቅ ችላለች።
አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን ሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ የሆኑት ጥኡማይ ወ/ገብርኤል እንዳሉት ይህ መመረያ ለአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን ያለው ፋይዳ ያለውን ሥራ መከፋፈሉ ጥራት ያለው ሥራ እንዲሠራ ይረዳልም ተብሏል።
የሚደርሰውን የትራፊክ አደጋም ከመቀነስ አንፃር እግረኞችን ያማከለ መንገድ ለመሥራት መታሰቡ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ነው የተናገሩት በአሁኑ ሰዓትም በአዲስ አበባ 7000 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን መንገድ እንዳለም ለማወቅ ተችሏል ይህ ሕግ ከመንገድ ጋር ተያይዘው የሚመጡ ችግችን ያስቀራል ሲሉ ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።
ቅጽ 2 ቁጥር 111 ታህሳስ 10 2013



