የባቢሌ ዝሆኖች መጠለያ ዳግም ክለላ ሊካሄድ ነው

0
632

በባቢሌ የሚገኙ ዝሆኖች ላይ የሚደርሰውን ሕገ ወጥ አደን እና በጫካው ላይ የሚደርሰውን ሕገወጥ ተግባራት ለመከላከል እንዲያስችል የመጠለያውን ሕጋዊ ይዞታ ለማስጠበቅ ዳግም ክለላ ሊካሄድ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ሥራ መጀመሩን የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማት ጥበቃ ባለሥልጣን ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።
ከኦሮሚያ እና ሶማሌ ክልል የተዋቀረው ግብረ-ኃይል በመጠለያው ከገቡ አካላት ጋር መወያየት ከመጠለያው ወጥተው የሚሰፍሩበትን መንገድ በማመቻቸት የመጠለያው ሕጋዊ ይዞታውን የማስከበር ሥራ በዋነኝነት እንደሚሠራ አስታውቋል።

ግብረ ኃይሉ በመጠለያው ውስጥ በሕገ ወጥ መንገድ የሰፈሩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ሙሉ በሙሉ ማስወጣት እና ሌሎች ቦታዎች ላይ መልሶ ማስፈር ፣ በመጠለያው ክልል ውስጥ በኢንቨስትመንት ሰበብ ሕጋዊ ባልሆነ አካሄድ የገቡ አካላትን ከስፍራው ማስነሳት ፣ በአጠቃላይ መጠለያውን ከማንኛውም ሕገ ወጥ ተግባራት ማጽዳትና ዳግም ክለላ ለማካሄድ እንደታሰበም ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል።

ይህ ሕገወጥነትን የሚከላከለው ግብረ ኃይል በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ተፈጻሚ እንዲሆን እቅድ ይዞ እየተንቀሳቀሰ እንዳለም ከአንድ ወር በኋላ የተደረሰበት አፈጻጸም ተገምግሞ ቀጣይ ሌሎች መጠለያውን የሚደግፉ ሥራዎች እንደሚቀጥልም ባለሥልጣኑ ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል።

አዲስ ማለዳ በጉዳዩ ላይ ያነጋገራቸው የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን የኮሚውኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር ጌትነት ይግዛው እንደተናገሩት፤ በሕገ ወጥ ዝውውር ከፍተኛውን ቦታ ከሚይዙት ነገሮች መሀከል የእንስሳት ሕገወጥ ዝውውር አንዱ ነው።

በተለይም በሕገወጥ መልኩ የዝሆን ጥርስ በዓለም ላይ በውድ ገንዘብ የሚሸጥ እንደሆነ እስከ መካከለኛው ምስራቅ የሚደርስ የገበያ ትስስር እንዳለ ይታወቃል›› ሲሉ ተናግረዋል።

ባቢሌ በምስራቅ አፍሪካ ጥቁር ዝሆኖች የሚጠለሉበት ብቸኛ መጠለያ ሲሆን እንደ ሌሎቹ ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሚገኙ ፓርኮች ሁሉ ሰው ሠራሽ ችግሮች ጉዳት እያደረሱበት ነው። በዚህም የዱር እንስሳት ሀብቱ እና የደን ሀብቱም እየተመናመነ እንዳለም ጨምረው ተናግረዋል።

ደን የሚጨፈጭፉ በሕገወጥ መልኩ ከሰል የሚያከስሉ ሰዎች እንዳሉ የተናገሩት ጌትነት ፤ ለረጅም ዘመናት የሰላሙ ሁኔታ አስቸጋሪ የነበረበት አካባቢ እንደነበር በማውሳት ፤ አሁን ጫካው ላይ ሕገወጥ ሰፈራዎች ፣ ሕገወጥ ግጦሽ ፣ሕገወጥ እርሻዎች ፣ ሕገወጥ አደን በዋናነት የመጠለያው ችግር እንደሆኑ አስታውቀዋል።
በእነዚህ ሕገ ወጥ ችግሮች ምክንያት ብዙ ዝሆኖች በተወሰኑ ዓመታት ውስጥ 40 የሚሆኑ እንደተገደሉ እንዲሁም በቅርቡ የታጠቁ ሰዎች ኤልሞሌ (የዝሆን ግልገል) ይዘው ወደ ሀረማያ ዩንቨርሲቲ በመሄድ ግዙን ብለው እንደነበርና ዩንቨርስቲውም ይህ ሕገ ወጥ ነው አልገዛም ሲላቸው መንገድ ላይ በጥይት መተው ኤልሞሌዋን እንደገደሏት ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ከፍተኛ የሆነ ከሰል እየተመረተ ወደ ውጪ ሶማሌ ላንድ ይላካል፤ ይህም የደኑን ሕልውና ችግር ይከታልም ብለዋል።
የዚህ ግብረ ኃይል መቋቋም ለደኑም ሆነ ለእንስሳቱም ከፍተኛ ጥቅም አለው ተብሎ ታምኖበት እንደሆነ ነገር ግን እርሱን ለማስፈፀም ችግር ሊሆን የሚችለው የታጠቁ ሰዎች በብዛት መኖራቸው እንደሆነም ጠቁመዋል።

የባቢሌ ዝሆኖች መጠለያ በዓፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ-መንግሥት፣ በ 1962 የተመሠረተ እንደሆነ መረጃዎ ያሳያሉ።
ከአዲስ አበባ ወደ ጅጅጋ መስመር 550ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል።
ይህ መጠለያ በቆዳ ስፋት 6 ሺሕ 982 ካሬ-ሜትር የሚረዝም ሲሆን፣ ከጠቅላላ ስፋቱም ውስጥ 77 ከመቶ ያህሉ በአሁኑ አጠራር ”በሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት”ሥር ሲካለል፤ ቀሪው ሀያ ሦስት ከመቶ ያህሉ ደግሞ “በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት” ሥር ይገኛል።
በመጠለያው ውስጥ ከዝሆኖች በተጨማሪ 31 አጥቢ እንስሳት እና ከ191 በላይ አእዋፋት እንደሚገኙ አዲስ ማለዳ ካየቻቸው መረጃ ለማወቅ ችላለች።

ቅጽ 2 ቁጥር 111 ታህሳስ 10 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here