100 የዲያሊስስ ማሽኖች ወደ አገር ውስጥ ሊገቡ ነው

0
1001

በያዝነው ዓመት ከኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢዎች ጋር በመሆን 100 ለኩላሊት ዕጥበት ወይንም ዲያሊስስ ሕክምና የሚያገለግሉ ማሽኖች ወደ አገር ውስጥ እንደሚያስገባ የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

የጤና ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢዎች ኤጀንሲ ጋር በመሆን እቅድ ይዞ በዚህ የበጀት ዓመት 100 ያህል የኩላሊት ዕጥበት ሕክምና ለመስጠት የሚያስፈልጉ ማሽኖችን ለማስገባት እየሠራ እንደሆነ አባስ ሃሰን የጤና ሚንስቴር የክሊኒካል አገልግሎት ዳይሬክተር ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

የኩላሊት ሕሙማን በጎ አድራጎት ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሰለሞን አሰፋ በበኩላቸው በኢትዮጵያ የኩላሊት ዕጥበት ሕክምና ለመስጠት የሚያገለግሉ ማሽኖች በተለይ ደግሞ በመንግሥት የሕክምና ተቋማት ውስጥ የሚገኙት በአገልግሎት ረዘም ያለ ጊዜ የቆዩ በመሆናቸው ጭምር አብዛኛዎቹ በብልሽት አገልግሎት የማይሰጡ በመሆናቸው የኩላሊት ዕጥበት ሕክምና የሚያደርጉ ታካሚዎች በግል ሆስፒታሎች ሕክምናቸውን እያደረጉ ይገኛሉ ብለዋል።

ከዚህም በተጨማሪ በአገራችን ባሉ የመንግሥት የሕክምና መስጫ ተቋማት ያሉ አብዛኛዎቹ የኩላሊት ዕጥበት ሕክምናን ለመስጠት አገልግሎት ላይ ያሉ ማሽኖች በእርዳታ ወደ አገር ውስጥ የገቡ እና ዕድሜያቸውም የቆየ በመሆኑ አብዛኛቹ አገልግሎት የማይሰጡ እንደሆኑ እና ከተበላሹ በኋላም ለመጠገን ደግሞ ምንም ዓይነት የመለዋወጫ እቃ ስለማይኖራቸው አስቸጋሪ መሆኑን አባስ ገልፀዋል።

በኢትዮጵያ የሚሰጠው የሕክምና ትምህርት በአብዛኛው የንድፈ ሐሳብ በመሆኑ እና የሕክምና መስጫ መሣሪያዎችን የማወቅ ውሱንነት ስለሚኖር ለኩላሊት ዕጥበት ሕክምና መስጫ የሚያገለግሉ ማሽኖች እና ባለሙያዎቹ በቀላሉ ተዋውቀው መሥራት ካልቻሉ ማሽኖቹ የመበላሸት ዕድል ይኖራቸዋል ብለዋል።

ሰለሞን በበኩላቸው በግል የሕክምና መስጫ ተቋማት የሚገኙ ማሽኖች ሲበላሹ በፍጥነት ተጠግነው ሥራ ላይ ሲውሉ በመንግሥት የሕክምና መስጫ ያሉት ግን ከ 20 እና ከ 30 ማሽኖች በብልሸት ምክንያት ቁጥራቸው እስከ ሦስት እና አራት ድረስ ዝቅ ሲል በቸልታ ይታለፋል የኀላፊነት መገፋፋቶች ይታያሉ ሲሉ ተናግረዋል።

አክለውም ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ የኩላሊት ዕጥበት ሕክምና ለመስጠት የሚያገለግሉ ማሽኖች አሁን ያለውን ችግር ለመፍታት እንደ ትልቅ መፍትሄ ነው ሲሉም ይገልጻሉ። አንድ የኩላሊት ዕጥበት ታካሚ ለሦስት ወይንም ለአራት ሰዓታት ሕክምናውን ለማድረግ ማሽኑን ይጠቀማል፤ ከዚያም ማሽኑ ተፀድቶ ለሌላ ታካሚ አገልግሎት እስኪሰጥ ያሉት ሰዓታት ተደማምረው በቀን አንድ ማሽን ከኹለት ታካሚዎች በላይ ላያገለግል ይችላል ብለዋል። የማሽኖች ቁጥር መጨመሩ በአንድ ቀን ውስጥ ሕክምናውን የሚያገኙ ታካሚዎች ቁጥር ከፍ እንዲል ያደርገዋል ሲሉም ሰለሞን ይናገራሉ።

የውስጥ ደዌ ሐኪም የሆኑት ዶክተር ሱሌማን ሀሰን የኩላሊት በሽታ ለረጅም ዓመታት ቀስ እያለ ኩላሊታችንን እየጎዳ ከጥቅም ውጭ የሚያደርግ በሽታ ሲሆን ኩላሊት ከ 25 በመቶ በታች መሥራት ሲጀምር በበሽታው እንደተያዝን ማወቅ የሚቻል ሲሆን መሥራት ማቆሙ እየበረታ ሲሄድ ሰውነታችን ውስጥ አደገኛ መጠን ያለው ቆሻሻና ፍሳሽ ይከማቻል ሲሉ ገልጸዋል።

ዶክተር ሱሌማን ሽንት መቋጠር ፣ በቂ ውሃ አለመጠጣት፣ ብዙ የአልኮል መጠጥ መውሰድ፣ የስኳር መጠን መቀነስ ሲጃራ ማጨስ፣ በቂ እንቅልፍ አለማግኘት እና ከመጠን ያለፈ ውፍረት የኩላሊት ሕመም መንስዔዎች ሲሆኑ የደም ማነስ፣ ደም የተቀላቀለበት ሽንት፣ የእግርና የእጅ እብጠት፣ የድካም ስሜት እንዲሁም የእራስ ምታት ከኩላሊት ሕመም ምልክች ውስጥ ናቸው ብለዋል።

የኩላሊት ሕመምን የሚያድን መድኃኒት ባይኖርም ሕመሙን የሚያስታግሱ መድኃኒቶች ግን አሉ ይላሉ ሱሌማን ። የመጨረሻ ደረጃ የደረሰ የኩላሊት ታካሚ ሰውነቱ ውስጥ የሚከማቸውን ቆሻሻና ፈሳሽ ያለ እገዛ መቋቋም ስለማይችል ታካሚው በሕይወት ለመኖር ዲያሊስስ እንደሚያስፈልገው የሚገልጹት ሱሌማን፤ ዲያሊስስ ማለት በማሽን የሚደረግ የሰውነት ዕጥበት ሥራ መሆኑንም ያብራራሉ። ከኩላሊት መሥራት ማቆም በቀር ሌላ ኩላሊትን የሚጎዳ ሕመም ለሌላቸው ታካሚዎች የኩላሊት ንቅለ ተከላ ከዲያለሲስ የተሻለ አማራጭ ነው ሲሉ ሐኪሙ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 111 ታህሳስ 10 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here