በአዲስ አበባ ከተማ የመንግሥት አገልግሎት ክፍያ ማሻሻያ ከመደረጉ ጋር ተያይዞ የአዲስ አበባ ወሳኝ ኹነት ኤጀንሲ የሚሰጣቸው አገልግሎቶች ላይ የሚያስከፍለውን የአገልግሎት ክፍያ ጭማሪ መደረጉን የአዲስ አበባ ወሳኝ ኹነት ኤጀንሲ ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።
የአዲስ አበባ ወሳኝ ኹነት ኤጀንሲ የሚሰጣቸው አገልግሎቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ እንደተደረገ ለአብነትም መታወቂያ ፣ የጋብቻ ሰርተፍኬት ፣ ያላገባ ሰርተፍኬት ፣ የልደት ሰርተፍኬት ፣ ላይ ዋጋ ማሻሻያ እንዳደረገ ኤጀንሲው ለአዲስ ማለዳ አስረድቷል።
ለዲጂታል መታወቂያ ማሳተሚያ የሚወጣው ወጪ በጣም ከፍተኛ እንደሆነ እና ከዚህ ቀደም ደንቡ ባለመሻሻሉ ምክንያት በ20 ብር መታወቂያ ሲሰጥ እንደነበር አስታውቋል።
ከዚህ በፊት የነበረው የመታወቂያ ዋጋ በወረቀት ሲሠራ የነበረ ዋጋ እንደሆነና ነገር ግን አሁን የሚሰጠው የመታወቂያ ዓይነት ዲጂታል መታወቂያ ወይም የዲጂታሉ ማንዋል ስለሆነ የነበረው ዋጋ የሚወጣውን ወጪ መሸፈን ስለማይችል ማሻሻያ የተደረገበት መሆኑን ከኤጀንሲው ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
በጉዳዩ ላይ አዲስ ማለዳ ያነጋገራቸው በአዲስ አበባ ወሳኝ ኹነት ኤጀንሲ የነዋሪዎች ዘርፍ ዳይሬክተር ዮናስ አለማየሁ እንደተናገሩት የወሳኝ ኹነት ሥራዎች የሚሰጡት አገልግሎቱ እና ለአገልግሎቱ የሚቀበሉት ክፍያ አናሳ ነው ብለዋል።
በዚህም የዲጂታል መታወቂያው የህትመት ዋጋው የሰው ኃይሉ በአጠቃላይ የሚሰጠው አገልግሎትና ክፍያው አናሳ ስለሆነ ከተማ አስተዳደሩ እየከሰረ ነበር በድጎማ ሲሰጥ የነበረው ብለዋል።
መታወቂያን ጨምሮ ሌሎች የኹነት ምዝገባዎችን የምናከናውንባቸው ካርዶች የሚታተሙት በብርሀንና ሰላም ማተሚያ ቤት ሲሆን እያንዳንዱ የሚታተሙት በውድ ዋጋ እንደሆነ እና የዋጋ ጭማሪው አግባብነት ያለው እንደሆነ አስረድተዋል።
ምንም እንኳን ዋጋው ላይ ማሻሻያ ቢደረግበትም አሁንም ቢሆን ሙሉ ለሙሉ የወጣውን ወጪ መሸፈን አይችልም በዚህም መንግሥት ለኹነት ምዝገባዎች ከፍተኛ ድጋፍ እንደሚያደርግ አሳውቀዋል።
ለአብነትም ከመታወቂያ ጋር ተመሳሳይነት ያለው የመንጃ ፍቃድ በ650 ብር ነው ሚሰጠው ይሄም ደግሞ የዲጂታል ካርዱን ውድነትና ወሳኝ ኹነት በቅናሽ እንደሚሠራ ማረጋገጫ ነው ብለዋል።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ ቀድሞ የመታወቂያ ዋጋ አናሳ ስለነበር ነዋሪው ያለ አግባብ ፣ በግድ የለሽነት ይይዘው እንደነበር እና በዚህም መታወቂያዎች እየጣሉ አዲስ ለማውጣት የሚመጡ ሰዎች ቁጥራቸው ከፍተኛ እንደሆነ ተናግረዋል።
አሁን ግን እንደ ቀድሞ ጊዜ መታወቂያ ለማውጣት ዋጋው መጨመሩ ማኅበረሰብ በጥንቃቄ እንዲይዘው ያደርጋል ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናገሩ።
ይህ ጭማሪ በቀበሌው ውስጥ ለሚታወቁ አቅመ ደካማ ለሆኑ መክፈል ለማይችሉ ሰዎች በነፃ የሚያገኙበት መንገድ እየተመቻቸ እንዳለ እና በቅርቡ ተግባራዊ ይሆናል ተብሎ እንደሚታሰብ ነግረውናል።
ጭማሪውም አዲስ የሚያወጣ ፣ የጠፋበት ፣ ትውልደ ኢትዮጵያዊ የሆነ ፣ በወቅቱ ያወጣ ፣ ጊዜ ገደቡ ያለፈበት እያለ ዋጋው እንደሚለያይ ጠቁመዋል።
ለአብነትም በአሁኑ ሠዓት መታወቂያ ለማውጣት አዲስ ዲጂታል መታወቂያ 100 ብር ፣ የዲጂታሉ ማንዋል (በወረቀት የሰፈረ ነገር ግን ደግሞ የራሱ መለያ ቁጥር ወይም ባር ኮድ ያለው) 80 ብር ፣ ዲጂታል መታወቂያ የጠፋበት 200 ብር ፣ የዲጂታሉ ማንዋል የጠፋበት ደግሞ 150 ብር እንደሚከፈል ለማወቅ ተችሏል።
የጋብቻ ሰርተፍኬት ለማውጣት ኢትዮጵያዊ ከሆኑ ወቅታዊ ምዝገባ 120 ፣ የዘገየ ምዝገባ 200 ብር ፣ የጊዜ ገደብ ያለፈበት 250 ብር ፣ ለእርማት ለእድሳት 150 ብር ፣ ሲሆን ከተጋቢዎች አንዱ ኢትዮጵያዊ ከሆነ እና በወቅቱ ካወጣ 600 ፣ ብር ሁለቱም የውጪ አገር ዜጋ ከሆኑ አንድ ሺሕ ሀምሳ ብር ይከፈል።
ያላገባ ሰርተፍኬት ለማውጣት ኢትዮጵያውያን ከሆኑ 200 ብር ፣ እድሳት ግልባጭ 250 ብር ፣ ለትውልደ ኢትዮጵያውያን ያላገባ ለማውጣት 400 ብር እንደሆነ አዲስ ማለዳ ከወሳኝ ኹነት ኤጀንሲ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።
ቅጽ 2 ቁጥር 111 ታህሳስ 10 2013



