የኢትዮጵያ ሥጋና ወተት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት በ2013 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ከውጪ ንግድ ያገኘው ገቢ ከባለፈው ተመሳሳይ ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ11 በመቶ ቅናሽ ማሳየቱ ተገለጸ።
የኢንስቲትዩቱ የውጪ ንግድ አፈጻጸም በበጀት ዓመቱ በመጀመሪያ ሩብ ዓመት ከንዑስ ዘርፉ ምርቶች የወጪ ንግድ 27 ነጥብ 41 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ 17 ነጥብ 25 ሚሊዮን ዶላር ወይም የዕቅዱ 62 በመቶ ገቢ መገኘቱን የኢትዮጵያ ሥጋና ወተት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲቱዩት የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ደበሌ ለማ ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።
ይህም የበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት አፈፃፀም ከባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከተገኘው 19 ነጥብ 52 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ጋር ሲነፃፀር የ2 ነጥብ 27 ሚሊዮን ዶላር ወይም 11 በመቶ ቅናሽ ማሳየቱን የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊው ገልጸዋል።
ለዕቅድ አፈፃፀም ማነስ ምክንያት የአጠቃላይ የዕቅዱን 18 በመቶ ድርሻ የነበራቸዉ ኹለት ኤክስፖርት ቄራዎች (አክሸከርና ሔልሜክስ) እና ስድስት የእርድ ተረፈ ምርት ላኪዎች (ዮንግታይ፣ ኪንግ ድራጎን፣ በላይነህ፣ ደመቀ አክሊሉ፣ ጉተማ ጉታ፣ ኃይሉ ፈዬ) በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ምንም ምርት አለመላካቸዉ እና በጥራት እና በዋጋ ተወዳዳሪ ሆኖ ከመቅረብ ጋር በተያያዘ በዓለም ደረጃ እያደገ በመጣው ውድድር እንዲሁም የአገር ውስጥ የማር ዋጋ እየጨመረ በመምጣቱ በዕቅዱ ታሳቢ ከተደረጉት የማር እና ሰም አቀነባባሪ(ላኪዎች) ምንም ምርት አለመላካቸው በዕቅድ አፈፃፀም ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ አሳድሯል ተብሏል።
ተቋሙ በ2013 በጀት ዓመት በመጀመሪያ ሩብ ዓመት ከጥቅል የወጪ ንግድ ገቢ ዕቅድ ውስጥ ከአገር ውስጥ አምራች(ላኪዎች) 19 ነጥብ 79 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ 14 ነጥብ 70 ሚሊዮን ዶላር ወይም የዕቅዱ 74 በመቶ ገቢ ያገኘ ሲሆን አፈጻጸሙም በባለፈዉ በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከተገኘዉ 13 ነጥብ 58 ሚሊዮን ዶላር ጋር ሲነጻጸር አንድ ነጥብ 12 ሚሊዮን ዶላር ወይም ስምንት በመቶ ጭማሪ አሳይቷል። በሦስት ወራት ዉስጥ ከውጪ ባለሀብቶች ሰባት ነጥብ 61 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት አቅዶ ኹለት ነጥብ 55 ወይም 33 በመቶ ማከናወን የቻለ ሲሆን፣ አፈጻጸሙ ከባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከተገኘው አምስት ነጥብ 94 ሚሊዮን ዶላር ጋር ሲነጻጸር ሦስት ነጥብ 39 ሚሊዮን ዶላር ወይም 57 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል ተብሏል።
በበጀት ዓመቱ በመጀመሪያ ሩብ ዓመት ከተገኘው አጠቃላይ የንዑስ ዘርፉ ኤክስፖርት ገቢ (17 ነጥብ 25 ሚሎዮን ዶላር) ውስጥ ከሥጋና እርድ ተረፈ ምርት የተገኘው ገቢ (16 ነጠብ 77 ሚሊዮን ዶላር) የ97 ነጥብ 21 በመቶ ድርሻ ያለው ሲሆን ቀሪው ኹለት ነጥብ 78 በመቶ (ዜሮ ነጥብ አራት ስምንት ሚሊዮን ዶላር) የሚሆን ከሌሎች የንዑስ ዘርፉ ኢንዱስትሪ ምርቶች (ማር፣ ሰም፣ ዓሳ እና ወተት ተዋፅዖ) ኤክስፖርት የተገኘ ነው።
በመጀመሪያ ሩብ ዓመት በሥጋና እርድ ተረፈ ምርት ከሳዑዲ እና ከተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ውጪ ባሉ የመካከለኛው ምስራቅና ኤዥያ አገሮች ተቋሙ ያለውን የገበያ ድርሻ ወደ 15 በመቶ ለማሳደግ አቅዶ በታቀደው መሰረት 593 ቶን የተለያዩ የበግ፣ የፍየል እና የዳልጋ ከብት ሥጋና የእርድ ተረፈ ምርቶችን ወደ ሌሎች አገራት ኤክስፖርት በማድረግ አንድ ነጥብ 33 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ወይም በአጠቃላይ ከተገኘው 16 ነጥብ 76 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ዉስጥ የስምንት በመቶ ድርሻ ያለዉ ገቢ ማግኘት መቻሉ ተመላክቷል። አፈጻጸሙ በባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከሳውዲና ዱባይ ውጪ ከተገኘው አንድ ነጥብ ዘጠኝ ሰባት ሚሊዮን ዶላር ገቢ ጋር ሲነጻጸር 32 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል። በአጠቃላይ ከተገኘው 16 ነጥብ 77 ሚሎዮን ዶላር ገቢ ዉስጥ ከተባበሩት አረብ ኤሚሬትና ሳውዲ የተገኘው የ 92 በመቶ ድርሻ ያለዉ ገቢ ማግኘት መቻሉን ደበሌ ተናግረዋል።
መተጨማሪም ኮቪድ-19 በመከሰቱ እንቅስቃሴዎች በዕጅጉ በመገታታቸው ኢንስቲቱዩቱ የሚጠበቅበትን አፈጻጸም እንዳያስመዘግብ እንቅፋት መሆኑን ደበሌ ጠቅሰዋል።
ቅጽ 2 ቁጥር 111 ታህሳስ 10 2013


